1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፈረንሳዩ አመጽ መንስኤ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 4 2015

«ይኸ ለረዥም ጊዜ ሲብሰለሰል ለቆየ እና ከቅኝ አገዛዝ ጋር ለተሳሰረ የፈረንሳይ ዘረኝነት የተሰጠ ምላሽ ነው። ለዘመናት የዘለቀ የዘር ጭቆና፣ አናሳዎችን እና ቅኝ ተገዢዎችን መግፋት የነበረ ቢሆንም ሁለቱ ጉዳዮች ግን በፈረንሳይ ባለሥልጣናት እና ፖለቲከኞች ሲስተባበሉ የነበሩ ናቸው። የፈረንሳይ መንግሥት ራሱን ዘረኛ እንዳልሆነ ያቀርባል። »

https://p.dw.com/p/4Tk4i
Frankreich I Ausschreitungen in Paris
ምስል Jean-Francois Badias/AP/picture alliance

የፈረንሳዩ አመጽ መንስኤ፤ ዘረኝነትና የቅኝ ግዛት ታሪክ

አንድ ወጣት በፓሪስ ዳርቻ በሚገን አካባቢ በፖሊስ በመገደሉ ሰብብ በመላ ፈረንሳይ ተቀጣጥሎ የነበረው ተቃውሞ ካለፈው ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ በርዷል።  ቁጣውን ግን ፈጽሞ አልጠፋም።መንስኤው ከፈረንሳይ የቅኝ ግዛት ታሪክ ጋር የተያያዘው ዘረኝነት በፈረንሳይ አሁንም መፍትሄ ያላገኘ ጉዳይ ሆኖ ዘልቋል። ከአንድ ሳምንት በፊት በተካሄደው የፈረንሳይ አመጽ  በመላ ሀገሪቱ ከታዩ ክስተቶች ውስጥ የተሰባበሩ መስታወቶች ፣የተቃጠሉ መኪናዎች የአንድ የፈረንሳይ ከንቲባ ቤት ላይ የደረሰ ጥቃት ጥቂቶቹ ናቸው። የአልጀሪያ ዝርያ የለው የ17 ዓመቱ ናሄል መኪና እየነዳ ሳለ ፖሊስ ካስቆመው በኋላ ተተኩሶበት በመገደሉ በመላ ፈረንሳይ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች በየጎዳናው ወጥተው አንዳንዴም ኃያል በመጠቀም ቁጣቸውን በተከታታይ ቀናት ሲገልጹ ነበር። ወጣቶች የሚያመዝኑባቸው ተቃዋሚዎች ከፖሊስ ጋር በተጋጩበት ወቅት የታየው ግልጽ አመጽና በዘፈቀደ የተፈጸመው የንብረት ውድመት ጥያቄዎችን ማስነሳቱ እንዳልቀረ የዶቼቬለዋ የማሪና ስትራውስ ዘገባ ያስታውሳል።ወጣቱ ናሄል ሰኔ 20 ቀን 2015 ኖንቴር በተባለ ከፓሪስ በስተሰሜን ወጣ ብሎ በሚገኝ አካባቢ በፖሊስ ከተገደለ በኋላ በተነሳው አመጽ በሺህዎች የሚቆጠሩ መኪናዎች ጋይተዋል። ትምህርት ቤቶች፣ማዘጋጃ ቤቶች ፣ፖሊስ ጣቢያዎች ፣ባንኮች ልዩ ልዩ የንግድ ድርጅቶች ጥቃት ደርሶባቸዋል። ወደ ሺህ የሚጠጉ ህንጻዎች እሳት ተኩሶባቸዋል። ሌይ ለ ሮዝ በተባለው ከፓሪስ ወጣ ብሎ በሚገኝ አካባቢ፣የአንድ ከንቲባን ቤት ጥሶ እንዲገባ የተረደገ የሚነድ መኪና በከንቲባው ባለቤትና  ልጃቸው ላይ ጉዳት አደርሷል።  በወጣቱ ግድያ ሰበብ በተነሳው አመጽ በአጠቃላይ የደረሰው ጉዳት መጠን 1.1 ቢሊዮን ዶላር ተገምቷል። በዚህ የተነሳም ፖሊስ በሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን አስሮ ነበር።በአመጹ ወቅት አነጋጋሪው የነበረው ይህ ብቻ አልነበረም። ይልቁንም የናሄል ግድያና ግድያውን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ቁጣ በፈረንሳይ ማኅበረሰብ ውስጥ ከሚታየው ሆነ ተብሎ ከሚፈጸም ዘረኝነትና ከሀገሪቱ የረዥም ጊዜ የቅኝ ግዛት ታሪክ ጋር መያያዙም ጭምር እንጂ።

France Police Shooting
ምስል Yves Herman/AP/picture alliance

በአመጹ ምክንያት የጀርመን ጉብኝታቸውን የሰረዙት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑዌል ማክሮ ግድያውን አውግዘዋል።«ይቅር የማይባልና ለመግለጽ የሚከብድ ነው። ይህ በመጀመሪያ ቤተሰቡን ለማጽናናት ሀዘኑን ለመጋራት ለቤተሰቦቹና ለወዳጆቻቸው ስሜታችንን ለመግለጽ ነው። ሁለተኛ ጉዳዩ በአፋጣኝ ለፍርድ ቤቶች ተመርቷል። ሂደቱም በፍጥነት ይከናወናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ስራው እርጋታን የሚጠይቅ ቢሆንም እውነቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊደረስበት ይችላል።»
ማክሮ ይህን ቢሉም ዶቼቬለ ያነጋገራቸው ኒውዮርክ በሚገኘው ስቶኒ ብሩክ በተባለው ዩኒቨርስቲ የማኅበረሰብ ጥናት ፕሮፌሰር ክርስቲያን ፍሌሚንግ ግን የሆነው «ለመግለጽ የሚከብድ ወይም ምስጢርም» አይደለም።ይልቁንም ዘረኝነት እንጂ ሲሉ ገልጸውታል። «ይኸ ለረዥም ጊዜ ሲብሰለሰል ለቆየ እና ከቅኝ አገዛዝ ጋር ለተሳሰረ የፈረንሳይ ዘረኝነት የተሰጠ ምላሽ ነው። ለዘመናት የዘለቀ የዘር ጭቆና፣ አናሳዎችን እና ቅኝ ተገዢዎችን መግፋት የነበረ ቢሆንም ሁለቱ ጉዳዮች ግን በፈረንሳይ ባለሥልጣናት እና ፖለቲከኞች ሲስተባበሉ የነበሩ ናቸው። የፈረንሳይ መንግሥት ራሱን ዘረኛ እንዳልሆነ ያቀርባል። ይሁንና በአሁኑ አጋጣሚ ወጣቶች መኪናቸውን በማሽከርከራቸው በጥይት ሲመቱ የሚያሳይ የቪዲዮ ምስል አለ። ይኸ ደግሞ በዚያ ሁኔታ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ከፍተኛ ሕመም እና ቁጣ አሳማኝ ምክንያት ፈጥሯል።» 
ፈረንሳይ ከትላልቆቹ ቅኝ ገዝ የአውሮጳ ሀገራት አንዷ መሆኗ ሀቅ ነው። ከ16ተኛው ክፍለ ዘመን አንስቶ እስከ 1970 ዎቹ የነበሩት የሀገሪቱ መሪዎች እንደ ሌሎቹ የክፍለዓለሙ ሀገራት መሪዎች የስልጣኔ ተልዕኮአቸውን ለማሳካት በመላው ዓለም የሚገኙ ሀገራትንና ግዛቶችን በኃይል በመበዝበዝ ያምኑ ነበር።ምንም እንኳን በጎርጎሮሳዊው 1789 የተካሄደው የፈረንሳይ አብዮት እኩልነት ነጻነት እና ወንድማማችነትን ለማስፈን ቃል ቢገባም፣ ለፈረንሳይ ቅኝ ግዛቶች ግን የእኩልነት መብት የሚያልሙት ብቻ  ነበር። የእለት ተዕለት ህይወታቸው ማሳያ ጭቆና ነበር።ወንዶችና ሴቶች የራሳቸውን ባህልና ቋንቋቸውን ትተው የፈረንሳይን ባህልና ቋንቋ እንዲይዙ ይገደዱ ነበር።በተለይ በአልጀሪያ የፈረንሳይ ሚና እስካሁን በጣም ጥንቃቄ የሚያሻው ጉዳይ ነው።ሰሜን አፍሪቃዊቷ አልጀሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ በጎርጎሮሳዊው 1830 ነበር የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት የሆነችው። ከዚያም የፈረንሳይ ብሔራዊ ግዛት አካል ሆነች።አልጀሪያ ነጻነትዋን ስትጠይቅ አስከፊ ጦርነት ተነስቶ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር ሰዎች ሕይወት ጠፋ። ከሟቾቹ አብዛኛዎቹ አልጀሪያውያን ናቸው። በስተመጨረሻም በ1962 የፈረንሳይ ቅኝ ገዥነት አከተመ።
በዚሁ ጊዜ አካባቢ የነጻነት ንቅናቄዎች እየሰመሩ ሲሄዱ ፈረንሳይ ሌሎች ቅኝ ግዛቶቿን እየለቀቀች ወጣች።ይሁንና አንዳንድ በውጭ የሚገኙ ግዛቶች ግን አሁንም በፈረንሳይ ስር ናቸው። ከዚህ ሌላ ፈረንሳይ እንደ አብዛኛዎቹ የአውሮጳ ሀገራት ሀገሪቱ በተለይም በአፍሪቃ በሚገኙት በቀድሞ ቅኝ ግዛቶቿ ላይ የኤኮኖሚ የፖለቲካና ወታደራዊ ተጽእኖዎችን ማሳደሯን ቀጥላለች።ለምሳሌ የራሷን ጥቅም ለማስጠበቅ ስትልም በነዚህ ሀገራት ለሚገኙ ፈላጭ ቆራጭ መንግሥታት ድጋፍ ትሰጣለች።የወቅቱ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑዌል ማክሮ ከሌሎቹ የፈረንሳይ መሪዎች በላቀ የሀገራቸውን የቅኝ ግዛት ዘመን ዘመን «ታሪካዊ ወንጀል» በማለት እውቅና ሰጥተዋል።ማክሮ በቅኝ ግዛት ዘመን የተዘረፉ ቅርሳ ቅርሶችን ለመመለስ እና በአልጀሪያ በደረሰው እንዲሁም በሩዋንዳው ዘር ማጥፋት የፈረንሳይ ሚናን የሚያጣራ ኮሚሽን ለማቋቋም ቃል ገብተዋል። ይሁንና እንደ ክሪስታል ፍሌሚንግ ያሉ ተችዎች ግን ይህ ብቻውን የፈረንሳይን ድርጊት በበቂ ሁኔታ አይገልጽም ሲሉ ይሟገታሉ። ለምሳሌ በተለይ በቅኝ ግዛት ዘመን  ለተፈጸሙት ሁሉ ሀገሪቱ ሀላፊነቱን ሙሉ በሙሉ እንድትወስድ ብዙዎች ይጠይቃሉ።ማክሮ ግን በአልጀሪያ የሀገራቸው ሚና ላይ ይቅርታ የመጠየቅ ሀሳብ እንደሌላቸው ተናግረዋል። ማክሮ ይህን የማያደርጉት የፈረንሳይን አጠቃላይ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ይሰብረዋል ብለው ስለሚያስቡ መሆኑንም አስታውቀዋል።

Frankreich Unruhen in Frankreich - Paris
ምስል Juan Medina/REUTERS
Frankreich | Protest für getöteten 17-Jährigen
ምስል Cyril Dodergny/picture alliance/dpa/MAXPPP

የፈረንሳይ ማኅበረሰብ አካላትና የትምህርት ቤት መጻህፍት ቅኝ አገዛዝ የራሱ በጎ ጎኖች አሉት በማለት ለረዥም ጊዜ ሲከራከሩ ቆይተዋል። በጎርጎሮሳዊው 2017 ቀኝ አክራሪዋ ፖለቲከኛ ማሪን ለፔን የፈረንሳይ ቅኝአገዛዝ ለቀድሞ ቅኝ ተገዥዎች ብዙ አበርክቷል ሲሉ ተናግረው ነበር። እናም ለፔን በ2017 እና በ2022ቱ የመለያ ምርጫዎች የፈረንሳይ ቀጣይዋ ፕሬዝዳንት ለመሆን የሚያበቃቸው እድል ማግኘታቸው ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ አሁንም ምን ያህል በሀገሪቱ የተስፋፋ መሆኑን ያሳያል ትላለች ማሪና በዘገባዋ። በተመሳሳይ ሁኔታ ፍሌሚንግ እንደሚሉት የፈረንሳይ መንግሥት አሁንም ራሱን ዘረኛ እንዳይደለ አድርጎ ነው የሚያቀርበው። ፈረንሳይ የቀለም ልዩነት እንደማታደርግም ነው የምትናገረው። ይህም በፍሌሚንግ  አባባል መንግሥት ስለ ዜጎቹ ዝርያ ምንም ዓይነት ቆጠራ እንደማያካሂድ የሚያሳይ ነው። ሮክሃያ ድያሎ ደራሲና ታዋቂ የዘር እኩልነት ተሟጋች ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት በወጣቱ ግድያ በፈረንሳይ አመጽ ያስነሱት የውጭ ዝርያ ያላቸው ብዙዎች ተቃዋሚዎች ያሳለፉት ሕይወት  መንግሥት ከሚለው በተቃራኒው ነው። 
«በፈረንሳይ ነጭ ያልሆኑ ሰዎች እንዴት በፖሊስ ግፍ እንደሚፈጸምባቸው በርካታ ሰዎችን ያስታወሰ ይመስለኛል።  በፈረንሳይ ፖሊስ ሥር የሰደደ ስልታዊ ዘረኝነት አለ። በፖሊስ የማኅበረሰቡን የተወሰነ ክፍል በመበደሉ ምክንያት በዓለም አቀፍ እና ብሔራዊ ተቋማት በተደጋጋሚ ውግዘት ደርሶባታል።»
ይሁንና የፈረንሳይ ባለሥልጣናት ክሱን በተደጋጋሚ ያስተባብላሉ።የሀገሪቱ የሰብዓዊ መብቶች እምባ ጠባቂ ጥናት እንዳለው የፈረንሳይ ፖሊስ ጥቁር ወይም አረብ ወጣት ወንዶች ከሌሎች ከ20 ጊዜ በበለጠ ያስቆማቸዋል። ከነዚህ የአብዛኛዎቹ መሠረት የቀድሞ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛቶች ናቸው። የሚኖሩትም ፓሪስ ማርሴይና ልዮንን በመሳሰሉት ትላልቅ ከተሞች ዳርቻዎች ወይም በፈረንሳይኛው አጠራር ባንልየዎች ውስጥ ነው። ናፖልዮን ሦስተኛ ፈረንሳይን በመራበት በ19ነኛው ክፍለ ዘመን ሰፋፊ መንገዶችና የተሻሻሉ የውኃ ማስተላለፊያ ቱቦዎች የተሰሩላት አዲሲቷ ፓሪስ የተገነባችው አፍሪቃ ሄደው በበለጸጉ ፈረንሳውያን የገንዘብ እርዳታ ነበር። ያኔ አነስተኛ በጀት ያላቸው ወደ ትላልቅ ከተሞች ዳርቻዎች ተገፉ። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ደግሞ የሀገሪቱ ኤኮኖሚ ሲያድግ ሰማይ ጠቀስ ፎቆች ተገነቡ። ይህም ፈላስያንን መሳብ ጀመረ ።  በሀገሪቱ ታሪክ እነዚህ የትላላቅ ከተሞች ዳርቻዎች በፈረንሳይ መንግሥት ትኩረት አልተሰጣቸውም። የቀድሞው የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኒኮላ ሳርኮዚ በጎርጎሮሳዊው 2005 ዓም የሀገር ውስጥ ጉዳይ  ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት እነዚህን አካባቢዎች በደንብ የማጽዳት ሀሳብ አቅርበው ነበር። ከዚያን ወዲህ የለተያዩ መርሃ ግብሮች ቢታቀዱም፣ ንግግሮች ቢካሄዱም ፣የተለወጠ ነገር ግን የለም። ናሄል የተገደለበት የኖንቴር ከተማ ነዋሪ ለዶቼቬለ እንደተናገረው ለዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ ተጠያቂው የፈረንሳይ መንግሥት ነው ።
«ተጠያቂው የፈረንሳይ መንግሥት ነው። ይኸን የችግር እና የድህነት ሁኔታ በብዙ አሥርት ዓመታት ፈጥረዋል። በዚያ መንገድ ያደገ ትውልድ አባል ነኝ። ድህነት እና መከራን አውቀዋለሁ። የምናስወግደውም አይመስልም »
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ
 

Frankreich | Protest für getöteten 17-Jährigen
ምስል Eliot Blondet/picture alliance/abaca