1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጦርነት ቀናት ውጥረት እና ሥጋት ፣ የዓይን ምስክር ከደብረ ታቦር

ረቡዕ፣ ነሐሴ 10 2015

ከሐምሌ 25 ቀን ምሽት ጀምሮ በከተማው ከፍተኛ ተኩስ እንደነበር የሚያስታውሱት ያነጋገርናቸው ግለሰብ የግጭቱ መነሻ ከባሕር ዳር እና ጎንደር ተነስቶ ወደ ሰሜን ወሎ አካባቢ ደብረታቦርን አቋርጦ ይሄዳል የተባለ የመከላከያ ሠራዊት ጉዞ መጀመሩን የሰሙ «የተቆጡ ወጣቶች« ያሏቸው ታጣቂዎች መንገድ በመዝጋታቸው መሆኑን ያስታውሳሉ።

https://p.dw.com/p/4VFKG
የባሕር ዳር ከተማ የሕዝብ መጓጓዣ አገልግሎት
በሚያዝያ ወር 2015 ተስተጓጉሎ የነበረው የባሕር ዳር ከተማ የሕዝብ መጓጓዣ አገልግሎት ዳግም የሥራ እንቅስቃሴ ሲጀምር። ፎቶ ከማኅደርምስል Alemnew Mekonnen/DW

የጦርነት ቀናት ውጥረት እና ሥጋት

በአማራ ክልል በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ መካከል ጦርነት ከተደረገባቸው አካባቢዎች አንዱ ደቡብ ጎንደር ነበር። በዞኑ ዋና ከተማ ደብረታቦር ሁኔታው ምን ይመስል ነበር? በሚል በወቅቱ በስፍራው የነበረን አንድ ግለሰብ ጠይቀናል።

ከሐምሌ 25 ቀን ምሽት ጀምሮ በከተማው ከፍተኛ ተከስ እንደነበር የሚያስታውሱት ያነጋገርናቸው ግለሰብ የግጭቱ መነሻ ከባሕር ዳር እና ጎንደር ተነስቶ ወደ ሰሜን ወሎ አካባቢ ደብረታቦርን አቋርጦ ይሄዳል የተባለ የመከላከያ ሠራዊት ጉዞ መጀመሩን የሰሙ «የተቆጡ ወጣቶች« ያሏቸው ታጣቂዎች መንገድ በመዝጋታቸው መሆኑን ያስታውሳሉ።

ይህንን ተከትሎ በመከላከያ ሠራዊቱ እና በፋኖ አባላት መካከል ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ እንደናበርም ይናገራሉ። በወቅቱ የአካባቢው አመራሮች እና የመንግሥት ሠራተኞች ሥራቸውን እንዲሠሩ ፋኖዎች ትዕዛዝ ይሰጡ እንደነበርም ተገልጿል። ዝርፊያ ፣ የንብረት ውድመት እና መሰል ድርጊቶች በከተማው አለምፈፀሙን የገለፁት አስተያየት ሰጪው፣ የኑሮ ሁኔታው ግን ጣራ ነክቶ ነበር ይላሉ። የከተማዋ የሳምንቱ ሁኔታ በውጥረት የተሞላ ሆኖ ማለፉን የገለፁት እኒሁ የከተማዋ ነዋሪ «በሁለቱም ወገኖች በኩል  የሞተ፣ የቆሰለ፣ የተጎዳም» እንደነበር አክለዋል።

የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ
በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር የሚገኘው የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ሕንጻ። ደብረታቦር ከተማ ውስጥ ከቀናት በፊት በፋኖ እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል ውጊያ ተካሂዷል። አሁን ከተማዋ መረጋጋትዋን ነዋሪዎች ገልጸዋል። ፎቶ ፤ ከማኅደር ምስል Alemnew Mekonnen/DW

በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ደብረታቦር ከተማ እና በዙሪያው የነበረው የጦርነት ቀናት ሁናቴ አስጊ እና ውጥረት ያስከተለ እንደነበር ያስታወሱት ያነጋገናቸው ግለሰብ የክስተቱን አጀማመር ጭምር እንዲህ በማለት አስታውሰዋል። «በ25 [ሐምሌ] ማታ ጀምሮ የተኩስ ልውውጥ ነው ያደረው። በ26ትም በተመሳሳይ ከፍተኛ የሆነ ተኩስ ነው የነበረው።»

በከተማዋ ፋኖዎች ለቀናት አድርገውት በነበረው እንቅስቃሴ ዝርፊያም ሆነ የንብረት ውድመት እንዳልተፈፀመ ፣ ይልቁንም የመንግሥት ሠራተኞች ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ ትዕዛዝ ይሰጡ እንዳነበርም እኒሁ ሰው ገልፀዋል።

«የአካባቢው አመራሮች ሥራቸውን መሥራት እንዳለባቸው በፋኖ መሪዎች በኩል ይነገር ነበር። "ማንም አመራርና የመንግሥት ሠራተኛ ሥራውን መሥራት አለበት የሚል መግለጫ በሰጡ ማግስት አብዛኛዎቹ ቢሮዎች እንደገና ሥራ የመጀመር ነገር ታይቷል። ነገር ግን ውጥረቱ የከፋ ነበር።» ብለዋል። የመረጃ ምንጫችን በዛሬው ዕለት መከላከያ ሠራዊት ወደ ከተማዋ መግባቱን መስማታቸውንም ገልፀዋል። «አሁን ላይ የተሻለ እንቅስቃሴ አለ። አሁን ትራንስፖርት ወደ ባሕር ዳርም ፣ ወደ ጎንደርም ተጀምሯል። መከላከያ ሠራዊት በተደራጃ መንገድ ወደ ከተማው በመግባት ላይ ነው ያለው በዛሬው ዕለት።» በማለት ገልፀዋል።

ሰሎሞን ሙጬ 

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ