1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አቡነ ማትያስ “በረሐብ ተቆራምደው ዕለተ ሞታቸውን” ለሚጠብቁ ዕገዛ እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ

ቅዳሜ፣ ጥር 11 2016

ጥምቀት በአዲስ አበባ ሲከበር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ “በረሐብ ተቆራምደው ዕለተ ሞታቸውን” ለሚጠብቁ ወገኖች ዕርዳታ እንዲቀርብ ጥሪ አስተላለፉ። ጥምቀት በጃንሜዳ በያሬዳዊ ዝማሬ እና በምዕምናን ምሥጋና በድምቀት ተከብሯል።

https://p.dw.com/p/4bUt2
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በጥምቀት በዓል ላይ
የጥምቀት በዓል በአዲስ አበባ ሲከበር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ባሰሙት ንግግር “በረሐብ ተቆራምደው ዕለተ ሞታቸውን” ለሚጠብቁ ወገኖች ዕርዳታ እንዲቀርብ ጥሪ አቅርበዋልምስል Solomon Muchie/DW

የጥምቀት በዓል አከባበር በአዲስ አበባ

ኢትዮጵያውያን አእምሯቸውን ከፍተው ለመረዳዳት፣ ለሰላምና ለፍቅር ፣ ለይቅርታ፣ ለአንድነት እና ለእኩልነት ተጠቃሚነት በርትተው እንዲሠሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ጥሪ አስተላለፉ።

ቅዱስ ፓርትርያርኩ በጃን ሜዳ በተከበረው የጥምቀት በዓል ላይ ባስተላለፉት መልእክት ሕፃናትን ጨምሮ በረሃብ እየሞቱ ያሉ ዜጎች መኖራቸውን ጠቅሰው "በጽኑ ረሃብ ለተጠቃው ሕዝባችን" ኢትዮጵያዊያንም ሆኑ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ እጃቸውን እንዲዘረጉ ጠይቀዋል።

በልዩ መንፈሳዊ ክንዋኔዎች ደምቆ የሚከበረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን የጥምቀት ክብረ በዓል በአዲስ አበባ የጃንሜዳውን ጨምሮ በሌሎችም 78 ባህረ ጥምቀቶች ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቱ ተጠብቆ ተከብሯል።

ብፁዕ አቡነ ማትያስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ፓትርያርክ በዛሬው የጥምቀት በዓል ላይ ጠብ ፣ ግድያ፣ መለያየት ይሽር ዘንድ የንስሐ መልእክት አስተላልፈዋል።

"በእውነት ንስሐ ከገባን ጠቡ፣ ግድያው ፣ ዘረፋው፣ መለያየቱ ይቆማል። በምትኩ ደግሞ ፍቅር፣ አንድነት እና ወንድማማችነት ይሰፍናል።

በጃን ሜዳ የጥምቀት በዓል ሲከበር የተገኙ ታቦቶች
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን የጥምቀት ክብረ በዓል በአዲስ አበባ የጃንሜዳውን ጨምሮ በሌሎችም 78 ባህረ ጥምቀቶች ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቱ ተጠብቆ ተከብሯል።ምስል Solomon Muchie/DW

ለተራቡት እንድረስላቸው - የቅዱስ ፓትርያርኩ ጥሪ

ብፁዕ አቡነ ማትያስ በጥምቀት በዓል ላይ በሰጡት ትምህርት፣ መልእክት እና አባታዊ ቃለ - በረከት ረሃብ ለሚያላጋቸው ዜጎች እንድረስላቸው ብለዋል።

"ዛሬ ብዙ ወገኖቻችን ሕፃናት፣ እናቶች፣ እህቶች እና አረጋዊያን በረሃብ ተቆራምደው እለተ ሞታቸውን እየጠበቁ ይገኛሉ። ወገኖቻችን በረሃብ እየሞቱ እንደ ባእድ ዝም ብለን የምናይ ከሆነ ክርስትያናዊነቱ ጥያቄ ውስጥ ይገባል"

የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ጥሪ

የባህል እና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ በዚሁ የጥምቀት በዓል ላይ ባቀረቡት ንግግር ከሃይማኖቱ አስተምህሮ ውጪ መልእክት የሚያስትላልፉ የሃይማኖት መሪዎችን ቤተ ክርስትያኗ እንድትገስጽ ጠይቀዋል። መንግሥት ጥምቀት በላቀ ደረጃ እንዲከበር ጥበቃ ያደርጋልም ብለዋል።

የጥምቀት በዓል አከባበር በጃንሜዳ
የባህል እና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ በዚሁ የጥምቀት በዓል ላይ ባቀረቡት ንግግር ከሃይማኖቱ አስተምህሮ ውጪ መልእክት የሚያስትላልፉ የሃይማኖት መሪዎችን ቤተ ክርስትያኗ እንድትገስጽ ጠይቀዋል።ምስል Solomon Muchie/DW

"እንዲህ ያሉ በዋጋ ሊተመኑ የማይችሉ ታላላቅ እሴቶቻችንን በሚገባ አውቀን ልንጠብቃቸው እና ልንከባከባቸው ይገባናል"

ለመሆኑ ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው ለምንድን ነው?

ይህንን ጥያቄ ለብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዱስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቅርበንላቸዋል።

"የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ተገልጦ ራሱን በትህትና ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ዮሃንስ ወዳለበት ቦታ ሄዶ የተጠመቀበት እና ትህትናውን ያሳየበት፣ ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር ያሳየበት እና የእዳ ደብዳቤያችንን የደመሰሰልን ለእኛ ልጅነታችንን የመለሰልን እለት ስለሆነ የልደታችን ቀን ነው" በማለት ክርስቶስ ለሦስት ነገር መጠመቁን ገልፀዋል።

የጥምቀት በአል ዝግጅትና የፀጥታ ቁጥጥር በአዲስ አበባ

አንደኛ "የእዳ ደብዳቤያችንን ሊደመስስልን፣ ሁለተኛ አንድነቱን፣ ሦስትነቱን ለመግለጽ እና ሦስተኛው ትንቢቱን ለመፈፀም - [ዮርዳኖስ ለምን ትሸሺያለሽ ፣ ባሕር ለምን ፈራሽ] ተብሎ የተፃፈውን ትንቢት ለመፈፀም ነው" ብለውናል።

የጥምቀት በዓል አከባበር በጃንሜዳ አዲስ አበባ
በጃን ሜዳው የጥምቀት ክብረ በዓል ላይ ያነጋገርናቸው አንድ የበዓሉ ተሳታፊ መንግሥትና ቤተ ክርስትያኗ የታየባቸው ውዝግብ መሳይ ችግር ሀገር የሚጎዳ በመሆኑ ሊታሰብበት ሊፈታም ይገባል ብለዋል።ምስል Solomon Muchie/DW

መንግሥትና ቤተ ክርስትያኗ ልዩነታቸውን እንዲፈቱ  መጠየቁ

በጃን ሜዳው የጥምቀት ክብረ በዓል ላይ ያነጋገርናቸው አንድ የበዓሉ ተሳታፊ መንግሥትና ቤተ ክርስትያኗ የታየባቸው ውዝግብ መሳይ ችግር ሀገር የሚጎዳ በመሆኑ ሊታሰብበት ፣ ሊፈታም ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን መግለጫ

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ 78 ጥምቀተ ባህራት መኖራቸው ተገልጿል። ዋናው የጃን ሜዳው ሲሆን በከተማዋ ከሚገኙት 270 አብያተ ክርስትያናት መካከል የ12ቱ ታቦታት ትናንት ከመንበረ ክብራቸው ወጥተው ጃን ሜዳ አድረዋል። ዛሬ ወደ መንበረ ክብራቸው ተመልሰዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ካሏት ዐበይት የአደባባይ ክብረ በዓላት መካከል አንዱ በሆነውና ዛሬ በተከበረው የጥምቀት በዓል ላይ በጣት የሚቆጠሩም ቢሆን የውጭ ዜጎችን ተመልክተናል።

ሰለሞን ሙጬ

እሸቴ በቀለ