የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሰላም ጥሪ
ሰኞ፣ ኅዳር 23 2017የኢትዮጵያ መንግሥት በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ለሚገኙ ታጣቂዎች የሰላም ጥሪ አቅርቧል። መሰል የሰላም ጥሪዎችን በተለያዩ መድረኮች የሚያቀርቡት ጠቅላይ ሚኒስይር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ሳምንት በፓርቲያቸው ብልጽግና 5ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይም ደግመውታል። እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እምነት ታጣቂዎች አንድ ሺህ ዓመት ቢዋጉ እንኳን ማሸነፍ አይችሉም። በዐቢይ የሰላም ጥሪ ላይ የተለያዩ የሰላም፣ የውይይት እና የድርድር ጉዳይ የሚመለከታቸው፣ ጥረት የሚያደርጉ፣ በተቋማት ውስጥ የሚሠሩ እና የፓርቲ ተዋናይ ግለሰቦችን እና የድርጅት መሪዎችን አሰተያየት ጠይቀናል።የብልጽግና ፓርቲ ጉባዔና የአማራ ክልል ነዋሪዎች አስተያየት
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ "የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ 50፣ 60 ዓመት ገደማ የፈጀ ነው" መሆኑን ገልጸው የደርጉን ኢሠፓን፣ የደርጉን ተቃዋሚ ኢሕአፓን፣ ለሁለት አሥርት ዓመታት ኢትዮጵያን በኢሕአዴግ ጥላ ሥር የመራውን ሕወሓትን እና ላለፉት 50 እና በላይ ዓመታት የትጥቅ ትግል፣ በቅርቡ ደግሞ መከፋፈል የታየበትን ኦነግን በኮሙኒስትነት ፈርጀው ተናግረዋል።
"ባልፉት ስድስት ዓመታት ከአንድም ጎረቤቶቻችን ጋር አንዲት ጥይት አልተቀያየርንም" በማለት በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ቢወራም "እውነታው ይህ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል። "ፈተናዎቻችን በሪፎርም፣ በንግግር፣ በተሃድሶ ኮሚሽን ፣ በሽግግር ፍትሕ፣ ሰጥቶ በመቀበል መርህ፣ እየተፈቱ እንደሚሄዱ ተስፋ አደርጋለሁ። ዛሬም ደጋግሜ እንዳነሳሁት በአማራ ክልል፣ በኦሮሚያ ክልል ያሉ ወንድሞቻችን አንድ ሺህ ዓመት ቢታገሉ ስለማያሸንፉን፣ አንድ ሺህ ዓመት ቢወድቁ ቢነሱ ለውጥ ስለማያመጡ ያኛውን መንገድ [የትጥቅ ግጭቱን] ጥለው ወደ ሰላም እንዲመጡ በድጋሚ ጥሪ አቀርብላቸዋለሁ" በማለት የሰላም ጥሪ ያስተላለፉት ዐቢይ "ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ሰላም ነው" ብለዋል።«ከብልጽግና ፓርቲ ጋር የውህደት ውይይት አልጀመርኩም» ህወሓት
"ክላሽ [AK 47 የጦር መሣሪያ] እንዲበቃ ፣ ክላሽ ያነገባችሁ በዚያም ድል ይገኛል ብላችሁ ያሰባችሁ ወንድሞቻችን ይበቃችኋል፤ ሞክራችኋል አልሆነም፤ ወደፊትም ስለማይሆን በሰላም፣ በውይይት በጋራ ሀገራችንን እንድናበለጽግ ጥሪ ላቀርብላችሁ እወዳለሁ" በማለት ዘለግ ባለው ንግግራቸው ጠቅሰዋል።
በዚህ ላይ የተሰጡ አስተያየቶች
"እንዲሁ ዝም ተብሎ በአዋጅ የሚመጣ ጉዳይ [የሰላም ጥሪው] አይደለም። ይሄን ጉዳይ እሳቸው [ጠቅላይ ሚኒስትሩ] ጭምር ያውቃሉ"።
"የታጣቂዎቹ ጥያቄ ምንም ይሁን ምንም መደራደር ራሱን የቻለ ማሸነፍ ስለሆነ መደራደር መሸነፍ እንዳልሆነ መመን አለባቸው። ድርድር አያስፈልግም የሚሉ ካሉ። ቁርጠኝነት ከብልጽግና በኩል ግን በፍፁም አላየንም"።
"መዋቅራዊ ችግሮች ነው ያሉት። ሁላችንንም ጠፍንገው የያዙን። አንዱ ጠብመንጃ ነው። የጠብመንጃ እሥረኛ ነን ኢትዮጵያውያን ። የጠብመንጃ እሥረኛ የሆንነው ተቋም ስለሌለን ነው። ወጣቶች ለምንድን ነው ጫካ የገቡት? እነሱን የሚያሳትፏቸው ሰፊ የፖለቲካ ተቋማት ስለሌሉን ነው"።የብልጽግና ፓርቲ ውጤታማ ባልሆኑ አመራሮች ላይ እየወሰደ ያለው ርምጃ
"ሰላምን በሚዲያ ከመስበክ የዘለለ ብዙ በግራ ቀኝ የሚሠሩ ሥራዎች አሉ የምንታዘበው። መሬት ላይ የነኩ ጥረቶች ያስፈልጋሉ። እኛ [የአማራ ክልል የሰላም ምክር ቤት] የገጠመን ችግር እስካሁን እስካሁንም ገጥሞን የቆየው በሁለቱም ወገን [መንግሥት እና ፋኖ] ያለው አለመተማመን የከፋ ነው"።