1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መልዕክት እና የኦብነግ መግለጫ

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 26 2017

የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) ይህንን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ንግግር አያይዞ በ X ባወጣው መግለጫ "ሰላም ስጦታ አይደለም - የመስዋዕትነት ውጤት እንጂ" ብሏል። አክሎም በአካባቢው ሰላምን ለማስቀጠል ዋጋ የከፈሉ ያላቸው የቀድሞ ተዋጊዎቹን ማክበር እንደሚገባ ገልጿል።

https://p.dw.com/p/4oobg
Äthiopien Premierminister Abiy Ahimed Diskussion
ምስል Office of Prime minister of Ethiopia

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መልዕክት እና የኦብነግ መግለጫ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መልዕክት እና የኦብነግ መግለጫ


ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ትናንት በሶማሌ ክልል ባደረጉት ጉብኝት "ሙሉ ትኩረታችን ልማት ብቻ እንዲሆን አደራ ማለት እፈልጋለሁ" ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሶማሌ ክልል ሸበሌ ዞን የጎዴ መስኖ መሠረተ ልማትን ትናንት አርብ ሲያስመርቁ የሶማሌ ክልል ለአካባቢው ሕዝቦችም በረከት መሆን የሚችል ነው ብለዋል።

በዚሁ ሥነ-ሥርዓት ላይ "በትንሹም በትልቁም ግጭት አያስፈልግም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "ኢትዮጵያ የጦርነት ሳይሆን የሰላም ምድር እንድትሆን" በትብብር እንሥራ ሲሉ ጠይቀዋል።

የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) ለዚህ በሰጠው ምላሽ ሰላም በመስዋዕትነት የሚገኝ መሆኑን በመጥቀስ፤ በአካባቢው ሰላም እንዲገኝ መስዕዋትነት ከፍለዋል ያላቸው የቀድሞ ተዋጊዎቹ እንዲከበሩ ጠይቋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ በሶማሌ ክልል ሸበሌ ዞን የጎዴ መስኖ መሠረተ-ልማት ግንባታን ትናንት ሲያስጀምሩ በክልሉ የሚለማው መሬት ማደጉን በዐወንታ አወድሰዋል። አያይዘውም የሰላም መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን "ሀብታም" ያሉት የሶማሌ ክልል መልማት የኢትዮጵያን ዕድገት የሚበይን ስለመሆኑም ገልፀዋል።

"የሶማሌ ክልል ለማደግ፣ ለመበልፀግ፣ ኢትዮጵያን ፣ ምሥራቅ አፍሪካን ለመመገብ የሚያስችል ሀብታም ክልል ነው። በትንሹም በትልቁም ግጭት አያስፈልግም፤ ተረጋግተን፣ ተወያይተን፣ በተደመረ መንፈስ የጀመርነውን የልማት ሥራ ማጠናከር ይኖርብናል"።


ኦብነግ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ንግግር የሰጠው ምላሽ


የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) ይህንን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ንግግር አያይዞ በ X ባወጣው መግለጫ "ሰላም ስጦታ አይደለም - የመስዋዕትነት ውጤት እንጂ" ብሏል። አክሎም በአካባቢው ሰላምን ለማስቀጠል ዋጋ የከፈሉ ያላቸው የቀድሞ ተዋጊዎቹን ማክበር እንደሚገባ ገልጿል።

የኦብነግ ተዋጊዎች "ለበርካታ አሥርት ዓመታት የዘለቀውን ግጭት በማስቆም ረገድ ወሳኝ ሚና ቢኖራቸውም ባለፉት ለስድስት ዓመታት ግን ቸል ተብለዋል" ሲልም ከሷል።

"ፍትሕ እስከ መቼ ቸል ሊባል ይችላል?" ሲል የጠየቀው ኦብነግ "በቸልተኝነት ላይ የተገነባው ሰላም ደካማ ነው" በማለት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ አሳስቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ የሰላም ምድር እንድትሆን ጥሪ አድርገዋል።

"ኢትዮጵያ ለማኝ ሳትሆን ረጂ እንድትሆን፣ የጭቅጭቅ የጦርነት ምድር ሳትሆን የሰላም ምድር እንድትሆን ሁላችን በተባበረ ክንድ፣ በተደመረ መንፈስ አብረን እንድንሠራ አደራ እላለሁ" 

"የሶማሌ ክልል ለማደግ፣ ለመበልፀግ፣ ኢትዮጵያን ፣ ምሥራቅ አፍሪካን ለመመገብ የሚያስችል ሀብታም ክልል ነው።"
"የሶማሌ ክልል ለማደግ፣ ለመበልፀግ፣ ኢትዮጵያን ፣ ምሥራቅ አፍሪካን ለመመገብ የሚያስችል ሀብታም ክልል ነው።"ምስል Seyoum Getu/DW

የኦብነግ የአዲስ ዓመት መልዕክት 


ያለፈው የጎርጎረሳዊያን ዓመት በጠቅላላው ኢትዮጵያ ውስጥ ከነበረው ሁኔታ አንፃር በሶማሌ ክልል አንፃራዊ ሰላም ነበር ያሉት የኦብነግ ሊቀመንበር አብዱራሕማን ማሐዲ በክልሉ አሰቃቂ ግጭቶች፣ መፈናቀል፣ ውድመት እያደረሰ መሆኑን ከቀናት በፊት ባወጡት መልዕክት ገልፀዋል።

ከራስ ገዝ ሶማሌላንድ አስተዳደር በኩል ያለው "ያልተፈቀደ ተሳትፎ እና ጣልቃ ገብነት" በሶማሌ ክልል ችግር ማስከተሉንም ጠቅሰዋል። 

ከሳምንት በፊት በሶማሊላንድ የፀጥታ ኃይሎች እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፖሊሶች መካከል ግጭት ተከስቶ እንደነበር ያረጋገጡት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ጉዳዩ በዘላቂነት መፍትሔ እንዲያገኝ በሀገር ሽማግሌዎች እየታየ መሆኑን ትናንት አርብ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

"የተከሰተ ግጭት እንደነበር በሚዲያዎች ላይ ያየነው ነገር ነበር። ይህንን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በአጎራባች ክልሎች ባሉ የሀገር ሽማግሌዎች ጉዳዩ የተያዘ ነው"።

የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) ሊቀመንበር ራስን በራስ የማስተዳደር እና የመወሰን መብትን ለማስከበር  የሰላማዊ ትግል ጥሪ ያደረጉ ሲሆን ኤርትራ ውስጥ በድርጅቱ እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት አሁንም ሳይፈጸም በመቆየቱ "በመንግስት ቅንነት እና በዘላቂ ሰላም ላይ ትልቅ ጥርጣሬ ፈጥሯል" ብለዋል።
ሰሎሞን ሙጬ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር