1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችኢትዮጵያ

የግጭት ዳፋ ባገረሸበት ሰላሌ የነዋሪው ሰቆቃ

ሥዩም ጌቱ
ዓርብ፣ ጥር 23 2017

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሰዎች ለቅሶ እና ገበያ ሲሔዱ ጭምር እየታገቱ እንደሚገኙ ነዋሪዎች ተናገሩ። ከሣምንት በፊት ከደብረ ሊባኖስ አካባቢ ወደ ያያ ጉለሌ ለገበያ ሲጓዙ ታፍነው የተወሰዱ 50 ገደማ ሰዎች አሁንም አልተመለሱም። ነዋሪዎች እንደሚሉት የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች “ለኦፕሬሽን” ወደ አካባቢው ቢያቀኑም ወዲያው ተመልሰዋል።

https://p.dw.com/p/4ptdR
በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ነዋሪዎች ግጭት እንዲፈታ በአደባባይ ሲማጸኑ
በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ያለው ግጭት እንዲፈታ ነዋሪዎች አደባባይ ወጥተው ቢማጸኑም ችግሩ ተባብሶ እገታ መበርታቱን ይናገራሉ። ምስል Seyoum Getu/DW

የግጭት ዳፋ ባገረሸበት ሰላሌ የነዋሪው ሰቆቃ

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የደብረጽጌ ከተማ ነዋሪ አስተያየት ሰጪ እያገረሸ በመጣው የጸጥታ ችግር ስጋት ከገባቸው ውስጥ ናቸው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት አደባባይ ወጥተው ተፋላሚዎች ሰላም እንዲያወርዱ በአከባቢቸው ህዝቡ መማጸኑን የሚስታውሱት ነዋሪ አሁን ላይ ያ ሁሉ ተማጽኖ መና ቀርቶ አስገድዶ ስወራ እና እገታዎች በታጠቁ አካላት ስለሚፈጸሙ የአከባቢው ነዋሪዎች ገቢያ እና ለቅሰው ለመውጣት የሚሰጉበት አስቸጋሪ ያሉት ሁኔታ መፈጠሩን አስረድተዋል፡፡

“ታጣቂዎች በየቦታው ሰው ይወስዳሉ” የሚሉት አስተያየት ሰጪዋ በተለይም ሰው ገቢያም ሆነ ለቅሶ እንኳ ለመሄድ ስጋት እንደሚገባው አስረድተዋል፡፡ 

እገታና ስወራው

ከአንድ ሳምንት በፊት ከደብረልባኖስ አከባቢ ወደ ያያ ጉሌሌ ለገቢያ ስጓዙ የነበሩ አንድ ተሽከርካሪ ሙሉ 50 ሰዎች ግድም የሚሆኑ ነጋዴዎች ሳዲኒ ብዮ በሚባል የያያ ጉሉለ ወረዳ ታፍነው እንደተወሰዱ እስካሁን አለመመለሳቸውን ለዶቼ ቬለ የገለጹት ሌላው በዞኑ የያያ ጉሌሌ ፊታል ከተማ አስተያየት ሰጪ የፀጥታ ችግሩ ፋታ እንደማይሰጥ ያስረዱን ማሳያውን በማቅረብ ነው፡፡

“ወደ ገቢያ ስሄዱ የነበሩ አንድ ሙሉ መኪና አብዛኞቻቸው ነጋዴዎች የሆኑና ገቢያተኞችም የሚገኙባቸው ያለፈው ማክሰኞ ሳምንት ወደ ጉሌሌ ለገቢያ እየመጡ ሳለ ነው ሳዲኒ በሚባል ቀበሌ በታጣቂዎች ታፍነው የተወሰዱት፡፡ ይህ ቦታ ከአንድ ወር ግድም በፊት አምስት የዞን ባለስልጣናትን ጨምሮ የመንግስት ሰራተኞች የተገደሉበትም ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ የተወሰዱት ወደ 50 የሚሆኑት ገቢያተኞቹ እስካሁን አልተመለሱም፡፡ ሾፈርም አብሮ እንደተወሰደ ነው” ብለዋል፡፡

የተስፋ ጭላንጭል የታየበት የሰላሌ ሰላም ዳግም መደፍረስ

አስተያየት ሰጪው አክለው በዚህን ወቅት ከከተማ በመራቅ መንቀሳቀሱ ስጋት እንደሚፈጥር አስረድተው ማህበረሰቡ እለት በእለት ስጋት ወሮት እንደሚኖርም ገልጸዋል፡፡ “እዚሁ ከተማ አከባቢ ካልሆነ በስተቀር ወዴትም መንቀሳቀስ ስጋት አለው፡፡ ህዝቡ በስጋት ነው ዛሬ አደርኩ እያለ ህይወቱን የሚመራው፡፡ በቅርቡ ኦፕሬሽን እናካህዳለን በሚል ከዞን የመጣው የመንግስት ሰራዊትም ወዲያው ስለሆነ የተመለሰው ምንም ለውጥ አልታየም፡፡ ከዚህ ከተማ ውጪ ታጣቂዎች አይገኙበትም የሚያስብል አንድም የገጠር ቀበሌ አታገኝም፡፡ በፊት በፊት በቆላማ ቀበሌያት ስወሰኑ ነበር አሁን ግን የትም ብትንቀሳቀስ ሸማቂዎች ያገኙኛል የሚል ስጋት ይኖራል፡፡ ታጣቂዎቹ እየተንቀሳቀሱ የመንግስት ሰራተኛ የሆነውን ንብረት በሙሉ ይወስዳሉ፡፡ ህዝቡ ፈጽሞ አይቶ የማያውቀውን ስቃይ ነው እያየ ያለው” ብለዋል፡፡

የተራዘመሰው ግጭት ተጽእኖ

ህብረተሰቡ አላቧራ ባለው የተራዘመ ግጭት መሰቃየቱን የገለጹት የያያጉሌለ ወረዳ ነዋሪው ከተማ እንኳ ተኝቶ ማደር አስጊ እየሆነ ነው ሲሉ ያለባቸውን አስከፊ ሉት የጸጥታ ስጋት አብራርተዋል፡፡

የሰላሌ አካባቢ ነዋሪዎች አደባባይ ወጥተው በመንግሥት እና በታጣቂዎች መካከል በመካሔድ ላይ የሚገኘው ግጭት እንዲፈታ ሲጠይቁ
የሰላሌ አካባቢ ነዋሪዎች አደባባይ ወጥተው በመንግሥት እና በታጣቂዎች መካከል በመካሔድ ላይ የሚገኘው ግጭት እንዲፈታ ጠይቀው ነበርምስል Seyoum Getu/DW

“ተቸግረናል፡፡ ከተማ ውስጥ እንኳ ቢሆን ተኝቶ የሚያድር ሰው አታገኝም፡፡ ሰው እየተደበቀ ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሰ ነው ቀን የሚገፋው፡፡ ሰው ከመደበኛ ህይወቱ ተበታትኗል፡፡ ህዝቡ ያለበት ህይወት ኑሮ አይደለም፡፡ ሁለቱ ተፋላሚዎች ብዙ ጊዜ ፊትለፊት ስዋጉ አታይም፡፡ የመንግስት ጦር ስመጣ ጫካ ያለው በደፈጣ ነው የሚጠብው፡፡ በዚህ ውስጥ ሁለቱ ተፋላሚዎች ተነጋግረው መግባባት ስችሉ በመሃል የመጨረሻ ስቃይ እያየ ያለው ህዝቡ ነው፡፡ በገጠር እውነት ለመናገር እንጀራ እንኳ መሶቡ ውስጥ የሚድርለት ሰው ማግኘት ይከብዳል፡፡ የትኛውም ጉልበተና ይገባል በልቶ ይወጣል፡፡ ምንግስት ግብር እንዲከፈል ገበረውን ስያስገድድ ያለው ምርጫ እህሉን ወደ ገቢ አውጥቶ መሸጥ ነው፡፡ እዛ ያለው የሸመቀ ታጣቂ ቡድን ግን አንድም ፍሬ እህል ወደ ገቢያ አታወጣም እያለ ያስፈራራዋል፡፡ ጋግሮ ልጆቹን እንዳይመግብ ሌማቱን ገልብጦ ባዶ የሚያስቀረው አካል ስላለ ይህን ሁሉ ስቃይ ህዝቡ የሚናገርበት መድረክም ሆነ ቦታ የለውም፡፡ ከዚህ የተነሳ በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ስቃይ ነው ህዝቡ እያሳለፈ ያለው” በማለትም አስረድተዋል፡፡

በኦሮሚያ የጸጥታ ፈተና ባለባቸው አከባቢዎች የበዓል ይዞታ

በመንግስት የጸጥታ ሃይልም ሆነ በአማጺው ታጣቂው ሃይል ስልክ ስለሚለቀም ስልክ ይዞ የሚንቀሳቀስ ሰው በገጠር አይገኝም ያሉት አስተያየት ሰጪው መረጃ እንኳ መለዋወጥ አዳጋች ሆኖ ህዝቡ ከዚህ በፊት ስኖር ከነበረው ሃምሳ ኣመት ወደ ኋላ ተመልሶ እየኖረ ነው ብለዋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ህዝቡ መንግስት ደህንነቱን እንዲያስጠብቅ ብማጸንም አልሆነለትም ነው ያሉት፡፡ 
ዶቼ ቬለ የነዋሪዎቹን አስተያየት ዞ በዚህ ላይ ማብራሪያ ለመጠየቅ ለዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ከፋለ አደሬ ብደውልም ምላሻቸውን ባለማግኘታችን ጥረቱ አልሰመረም፡፡ 

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አቶ ሽመልስ አብዲሳ በፕሬዝደንትነት የሚመሩት የኦሮሚያ ክልል ባለፉት ዓመታት ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር በሚደረግ ውጊያ ብርቱ ችግር ውስጥ ወድቋል። ምስል Seyoum Getu /DW

የተናፈቀው መጨረሻ

ነዋሪዎቹም ይላሉ፡፡ ከእንግዲህ የተሸለውን ከፈጠሪ እንጠብቃለን፡፡ “ፈጣሪ ይወቅልን እንጂ የሰው ታክቶናል” ያሉን የደብረጽጌ ነዋሪ “ብጨኛው አማራጫችን ፈጣሪን መማጸን ነው” በማለት የህብረተሰቡ ተስፋ መሟጠጥን ገልጸዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ጸጥታ እጦት የተማረረው ኅብረተሰብ እና የሰላም ጥሪው

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከአንድ ሳምንት በፊት “በኢትዮጵያ በግጭት ዐውድ ውስጥ ያሉ አካባቢዎች የሰብአዊ መብቶች ይዞታ”  በሚል ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ ኦሮሚያን ጨምሮ ግጭት ባለባቸው የአገሪቱ አከባቢዎች ሰፋፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በስፋት እየተስተዋሉ መሆኑን በዝርዝር አመልክቶ ለእልባቱም ለተፋላሚዎች ትሪ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡
ሥዩም ጌቱ
እሸቴ በቀለ
ጸሀይ ጫኔ