1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግብፅና ኤርትራ ወዳጅነት፤ የደባርቁ ጦርነት፤ የቱርክ የድርድር ጥረት

ዓርብ፣ መስከረም 10 2017

ኢትዮጵያና ሶማሊያ የገጠሙትን ፍጥጫ በድርድር ለማስወገድ የምትጥረዉ ቱርክ የሃገራቱን ባለሥልጣናት በድጋሚ በተናጥል ለማነጋገር ማቀዷ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ጦርና የፋኖ ታጣቂዎች በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ ዉስጥ በገጠሙት ዉጊያ፤ ግብፅና ኤርትራ የጠበቀ ትስስራቸዉን ለማጠናከር የያዙት እቅድ ላይ የተሰጡ አስተያየቶች።

https://p.dw.com/p/4ktgN
መቃዲሾ፤ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ወደብ ለመኮናተር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረሟ ተቃዉሞ
መቃዲሾ፤ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ወደብ ለመኮናተር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረሟ ተቃዉሞ ምስል Farah Abdi Warsameh/AP/picture alliance

በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሰጡ አስተያየቶች

በኢትዮጵያና ሶማልያ መካከል የቱርክ የድርድር ጥረት   

ኢትዮጵያና ሶማሊያ የገጠሙትን ፍጥጫ በድርድር ለማስወገድ የምትጥረዉ ቱርክ የሁለቱን ሐገራት ባለሥልጣናት ዳግም ግን በተናጥል ለማነጋገር ማቀዷን ያስታወቀችዉ ከቀናት በፊት ነዉ። ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የመንግሥትነት ዕዉቅና ከሌላት ሶማሊላንድ ጋር ወደብ ለመኮናተር የመግባቢያ ስምምነት በፈራረሟ የአዲስ አበባና የሞቃዲሾ ጠብ ተካርሯል። ግብፅ ለሶማሊያ ጦር መሳሪያ ማስታጠቅ መጀመሯና ሶማሊያ ዉስጥ ወታደር ለማስፈር ማቀዷ ደግሞ አዲስ ግጭት ሊያስከትል ይችላል የሚል ሥጋት አሳድሯል። ጠቡን ለማርገብ ቱርክ ከዚሕ ቀደም የሁለቱን ሐገራት ባለሥልጣናት አንካራ ዉስጥ ሁለቴ በተዘዋዋሪ አነጋግራለች። በቱርክ ሸምጋይነት የሚደረገዉ ይህ በተዘዋዋሪ የተባለዉ ድርድር በዚሁ ሳምንት ለሦስተኛ ዙር ይቀጥላል ተብሎ ነበር። ይሁንና ቀጠሮዉ ተሰርዟል።  

ችኮ ቬራ የተባሉ የተባሉ የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚ ፤ ቱርክ እራሱ ታሪካዊ ጠላታችን ናት በጀግናዉ አፄ ቴወድሮስ ጊዜ ለመውረር ሞክራ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥታ ነው የተመለሰችው፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል። ታደለ ላምቢሶ በበኩላቸዉ፤ ቱርክ ባለዉለታችን ናት እናመሠግናታለን። ጭቅጭቆች በሠለጠና ፤ ለስለስ ባለ ዲፕሎማሲ መፈታት አለባቸው፤ ሲሉ በፊስቡክ ላይ አስተያየታቸዉን  አጋርተዋል።

ሲሳይ በቀለ የተባሉ ደግሞ፤ ከኢንርናሽናል መድረክ ለጉድ ነው የወረድነው። በታሪክ እንደዚህ ወርደን አናውቅም። አፍረቃ ህብረት እንኳ አልሰማችሁም ብሎ ግብፅን ሱማሊያ ላይ ሲያስገባ ያኔ ነው ደረጃችንን ያወቅነው። የኢሜሬት ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አስፈፃሚ ሳተላይት ስቴት መሆናችን በዓለም ላይ መሳለቅያ አርጎናል ሲሉ አስተያየታቸዉን ፅፈዋል። ሄጤ ተሰማ በፊስቡክ ላይ ባጋሩት አስተያየት ደግሞ፤ ከታረቀች ትታረቅ፤ ካልታረቀች ታቀናለች።  የ 1969 ዓመተ ምህረቱን ዱላ ትቀምሳለች። ከሷ ጋር የቆሙትንም፤ ዋ ብለናል። አትንኩን፤  ከነኩን ግን ልክ ማሳየት ከአባቶቻችን የተማርነው ሃቅ ነው፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን ቋጭተዋል።

 

የመንግሥት ጦርና ፋኖ ደባርቅ ዉስጥ  በገጠሙት ዉጊያ በትንሹ 9 ሰዎች ተገደሉ

የኢትዮጵያ መንግሥት ጦርና የፋኖ ታጣቂዎች በያዝነዉ ሳምንት መጀመሪያ ላይ አማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ ዉስጥ በገጠሙት ዉጊያ በትንሹ ዘጠኝ ሰዎች ተገድለዋል፤ 35 ደግሞ መቁሰላቸዉ ተሰምቷል። የደባርቅ ሆስፒታል ምንጮችና የመግሥት ባለሥልጣናት ስለተገደሉት ሰዎች ብዛትና ዉጊያዉ ስለተደረገበት ዕለት የሰጡት መረጃ ግን የተለያየ ነዉ። አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ የጠቀሰዉ የደባርቅ ሆስፒታል ምንጭ እንዳስታወቀዉ ዉጊያዉ የተደረገዉ በያዝነዉ ሳምንት ማክሰኞ ነዉ። በዉጊያዉ ሲበዛ 10 ሲያንስ 9 ሰዎች ተገድለዋል ብሏል። 35 ሰዎች ደግሞ በዉጊያዉ ቆስለዉ ሆስፒታል ሕክምና እንደተደረገላቸዉ ወይም እየታከሙ ነዉ ሲል ዘግቧል። አንድ የአካባቢዉ ባለሥልጣን  ግን «ጥቃት« ያሉት ዉጊያ የተደረገዉ ባለፈዉ ሰኞ ነበር።የሞቱት ሰዎች ቁጥርም 20 ነዉ።ሁለቱም ምንጮች እንዳሉት በግጭቱ በአብዛኛዉ የተገደሉና የቆሰሉት ሠላማዊ ሰዎች ናቸዉ።

የፋኖ ታጣቂዎች
የፋኖ ታጣቂዎችምስል Mariel Müller/DW

ኩሴ ካፋአፓ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ ወገኖቼ አንጃጃል ሲሉ አስተያየታቸዉን ይጀምራሉ። ወገኖቼ አንጃጃል። ታጥቆ የወጣ ሰላማዊ ሰው የሚባል ይኖራል ብዬ አላምንም። ከቻልን ትጥቁን ፈተን ወደ ሰላማዊ ኑሯቸው መመልስ መቻል አለባቸዉ። እባካችሁ እስከ መቼ በዘር ፖለቲካ እርስ በርስ እንተላለቅ? ወደ እግዘብሔርን እንመለስ እንጅ ሲሉ አስተያየታቸዉን ቋጭተዋል።

ባርች ያዘዉ የተባሉ የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚ፤ ጦርነት እስካለ ድረስ እሄን ያህል ሰው ሞተ፤ ሰላማዊ ሰው ሞተ ምናምን የሚባል ነገር አይሰራም፤ ሁለቱ ተቀናቃኝ ቡድኖች እንዲታረቁ ጫና መፍጠር እንጂ ብለዋል። ህይወት ወልዴ የተባሉ አስተያየት ሰጭ፤ ግልፅ እድርጉት፤ ፋኖ ማለት ህዝብ ነው። ህዝቡ ደግሞ ዐብይ ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ ሲፈናቀል ሲገደል ተው ብለዉ ማስጠንቀቃያ ስጥታል? ሲሉ ይጠይቃሉ ። ስለዚህ ይላሉ ስለዚህ ጦርነቱ በመኖር እና ባለመኖር የህልውና ትግል ነው፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል።

ልጅ ረታ የተባሉ ሌላ አስተያየት ሰጭ፤ የአማራ ህዝብ ነቅቶ ሰላሙን ከልጠበቀ በስተቀር፤ እየተፈናቀለ እርስ በርስ እየተበላ ይኖራል። ሌላ ማንንም አይጎዳም። ባይሆን ከሌሎች ክልልሎች ማማር ያስፈልጋል ፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል። ማምና በረሀ የሚል የፌስቡክ ተጠቃሚ ፋኖ በፍፁም አማፂ አይደለም። በማንነቱ ለሚፈናቀለው ለሚገደለው የቆመ የአማራ ልጅ ፋኖ ነው፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል።

የግብፅና ኤርትራ የጠበቀ ትስስር

ግብፅና ኤርትራ የጠበቀ ትስስራቸዉን ለማጠናከር በሚጥሩበት በአሁኑ ወቅት ወታደራዊ ትብብር እና የመረጃ ልውውጥ ስምምነት ሊፈፅሙ እንደሚችል የግብፅ የዜና ምንጮች የዘገቡት በዚሁ ሳምንት መጀመርያ ላይ ነበር። የካይሮ መንግሥት ህወሓት እና ኤርትራን ማደራደር እንደሚፈልግም ተመልክቷል። ግብፅና ኤርትራ ይፈጽማሉ የተባለዉ ስምምነት በጋዛዉ ጦርነት ምክንያት ከኢራን ድጋፍ የሚያገኙ የየመን አማፅያን በቀይ ባህር ላይ የሚስተጓጎሏቸዉን መርከቦች ለመጠበቅ የሚያስችል እርምጃዎችን ያካትታልም ተብሏል።

የግብፅና ኤርትራ የጠበቀ ትስስር
የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና የግብፅ ፕሬዝዳንት አብደል ፈታህ አልሲሲምስል Egyptian President Office//APAimages/IMAGO

አንዋር አብደፋር የተባሉ አስተያየት ሰጭ፤ ከግብፅ እስከ ኤርትራ ከሶማልያ እስከ ጅቡቲ መንግስታት በፍርሀት ቆፈን ዉስጥ ሆነዉ ስናይ ኢትዮጵያ ምን ያህል አቅም እንዳላትና ቀይባህር ላይ ልትነግስ መሆኑን ያሳያል። ወደኋላ የለም! ከሠራዊቱ ውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ተጠባባቂ ጦር መሆኑን ጠላትም ወዳጅም ያውቃል፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን አጋርተዋል።

ተካልኝ በቀለ በበኩላቸዉ፤ ግብፅ ኢትዮጵያን በከበባ ለማሸበር የማትፈነቅለው ድንጋይ፥ የማትቧጥጠው ዐለት የለም፡፡ የሆነው ሆኖ ነፍሳቸውን ይማረውና ጠ/ር አቶ መለስ ዜናዊ እንደተናገሩት ግብፅ ለምታደርገው ማስፈራሪያ እርምጃዎች መፍትሔው አለመሸበር ብቻ ነው፡፡ ያ ሲባል ግን ኢትዮጵያ በበቂ ሁኔታ መዘጋጀት እንዳለባት መረሳት የለበትም፡፡ ዋናው ነገር ግን የጠ/ሚ ዐቢይ አገዛዝን መቃወምና ኢትዮጵያን ማፍረስ ልዩነቱ የጠፋባቸው፤ ፓለቲካን በቅጡ ከማይረዱ መጠንቀቅ ያሻል ሲሉ አስተያየታቸዉን አብቅተዋል።

ግብፅ ኤርትራን እና ህወሃትን ለማደራደር ሲሉ አስተያየታቸዉን የሚጀምሩት፤ ኢሳያስ ዘነበ ናቸዉ። ምቀኛ አያሳጣኝ ይባል የለ። ህወሓትንና ኤርትራን እናደራድራለን ማለታቸው ይበልጥ ትኩረት የሚስብ ቀልድ ነው፤ ሲሉ ኢሳያስ ዘነበ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል። ማቱሳል መሲ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ፤ የውሰጥ ክፍፍልና ጥላቻ ብኖረንም እኛ ኢትዮጵያዉያን  አንድ ነን፣ለውጭ ጠላት አንበረክክም ። ሠላም፣ ድል፣ ፍቅር ለኢትዮጵያ ይሁንላት! ሲሉ አስተያየታቸዉን በቃል አጋኖ ደምድመዋል።

ሙሉዉን ዝግጅት የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ!

አዜብ ታደሰ

ፀሐይ ጫኔ