የጋዜጠኞች እና የብዙኃን መገናኛ ባለሙያዎች እሥር
ሐሙስ፣ ኅዳር 27 2016የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ለሳምንታት ያለምንም ማብራሪያ በእሥር ላይ ይገኛል ያለውን ኢትዮ ኒውስ የተባለውን የበይነ መረብ መገናኛ ዐውታር ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ በላይ ማናዬን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ኮሚቴ ከሰሞኑ ጠይቋል።
ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ፍርድ ቤት እንዳልቀረበ እና ለእሥር ሊዳርገው የሚችል ምንም የሙያ ጥሰት የታየበት ሥራ አለማከናወኑን ባልደረባው ለዶቼ ቬለ ተናግሯል።የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ኮሚቴ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጋዜጠኞች እና በመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ላይ የሚደርሰው እሥር እና እንግልት እንዲቆምም ጠይቋል።
የጋዜጠኞች እና የብዙኃን መገናኛዎች ፈተና በኢትዮጵያ
በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት ተመዝግበውና ፍቃድ አውጥተው የሚሰሩ የብዙኃን መገናኛ ተቋማት ጋዜጠኞችና የሕትመት ውጤቶት በፀጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጪ መታገታቸው እንዳሳሰበው ከዚህ በፊት የጠየቀው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት እርምት እንዲደረግ መጠየቁ ይታወሳል።
በኢትዮጵያ አሁን ላይ ስላለው የጋዜጠኞች የሥራ ነፃነት እና ድባብ የጠየቅናቸው ሁለት ጋዜጠኞች መገናኛ ብዙኃን የሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ የሚፈጥረው ጫና ቀጥተኛ ተጠቂ በመሆናቸው የጋዜጠኝነት ሥራን መሥራት የሚያስችል ዐውድ እንደሌለና ይልቁንም ብዙዎች ለእሥር እና ሥደት መዳረጋቸውን ገልፀዋል።
የጋዜጠኞች የመታሰር ፣ የመፈታት ሁኔታ
ኢትዮጵያ ውስጥ በሀገሪቱ ሕግ መሠረት ተመዝግበውና ፍቃድ አውጥተው የሚሰሩ የብዙኃን መገናኛ ተቋማት ጋዜጠኞችና የህትመት ውጤቶት በፀጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጪ መታገታቸው ፣ መያዛቸው ፣ መለቀቃቸውና ዳግም መታሰራቸው ተደጋግሞ ታይቷል።
በተለይ የበይነ መረብን በመጠቀም በፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ መረጃ የሚተነትኑ ፣ ዘገባዎችን የሚሠሩ ግለሰቦችም ይሁን ድርጅቶች በደረሰባቸው ማስፈራራት፣ ቢሮ ተሰብሮ ዘረፋ ፣ ዛቻ እና መሰል ጉዳዮች ወይ ከሙያው ርቀዋል፣ ወይ ታሥረዋል አልያም ሀገር ጥለው ተሰደዋል።
የኢትዮ ኒውስ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ በፖሊስ በቅርቡ ከተያዙ ጋዜጠኞች አንደኛው ነው። ባልደረባው በለጠ ካሳ እንደሚለው በላይ ሊታሰር የሚችልበት የምለው የሰራው ዘገባ የለም ።
የጋዜጠኞች ስደት፣ ከሙያቸው የመራቅ ፈተና
ኢትዮጵያ ውስጥ ቀደም ሲል በአማራ ክልል ከተፈጠረው የፀጥታ ቀውስ ጋር በተገናኘ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ከተያዙት ጋዜጠኞች በተጨማሪ፣ የማህበራዊ መገናኛ ዐውታሮችን ተጠቅመው በመንግሥት ላይ ትችት የሚሰነዝሩ ፣ በመረጃ ትንተና የሚሳተፉ፣ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ዘገባ የሚሠሩ ግለሰቦች በተደጋጋሚ ሲታፈኑ፣ ሲታሰሩ እና ሲፈቱ ታይቷል። ይህ ድርጊት እንዲቆም በያገባናል ባዮች የሚሰጡ መግለጫዎች፣ ውትወታዎች ውጤት ሲያመጡም አልታየም። ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ አንድ ጋዜጠኛ አሁን ያለው የዘርፉ እውነታ ፈታኝ መሆኑን ጠቅሷል።
በቅርቡ አምስት ያህል ጋዜጠኞች ሀገር ጥለው መሰደዳቸውን አስታውቀው ነበር። የኢትዮ ኒውስ ዋና አዘጋጅ በለጠ ካሳ በባልደረባውም ይሁን በሌሎች የሙያው ሰዎች ላይ የሚደርሰው እንግልት ለዚህ ችግር መነሻ መሆኑን ይጠቅሳል። የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ኮሚቴ እየደረሱ ያሉ ተመሳሳይ ችግሮችን የመንግሥት ባለሥልጣናት እንዲፈቱ ጠይቋል
ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ