1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጋዛ እልቂትና የሰላም ጥሪ

ዓርብ፣ ጳጉሜን 1 2016

እስራኤል ባሻት ጊዜ ሲሻት ጋዛ ሠርጥን ሲፈልጋት ምዕራባዊ ዮርዳኖስ ዳርቻን፣ ካሰኛት በቦምብ፣ሚሳዬል፣ መድፍ ካስፈለጋት በቦልዶዞር ትደፈልቃለች።የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊዎች ይፎክራሉ።የፍልስጤም ባለሥልጣናት እንዳሉት ካለፈዉ መስከረም 26 ወዲሕ ጋዛ ሰርጥ ዉስጥ የተገደለዉ ፍልስጤማዊ 40,878 ደርሷል።የቆሰለዉ ደግሞ 94 ሺሕ 454 ነው።

https://p.dw.com/p/4kMsx
ለጋዛ ሕፃናትና ወጣቶች ትምሕርት ቀርቶ ቤትና ምግብ ማግኘት አስቸጋሪ ነዉ
ለጋዛ ሕፃናትና ወጣቶች ትምሕርት ቀርቶ ቤትና ምግብ ማግኘት አስቸጋሪ ነዉምስል Ramadan Abed/REUTERS

የጋዛ እልቂትና የሰላም ጥሪ

 

እስራኤል ጋዛ ሠርጥና ምዕራባዊ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ በሚኖሩ ፍልስጤማዉያን ላይ የምትፈፅመዉ ግድያና የንብረት ጥፋት እንዲቆም የሚደረገዉ ጥሪ እንደቀጠለ ነዉ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ባለፈዉ ሮብ ባ,ደረገዉ ሥብሰባዉ የፍልስጤማዉያን እልቂት እንዲቆም የተለያዩ ሐገራት ዲፕሎማቶች ጠይቀዋል።ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ እስራኤል ጋዛ ሰርጥ የሚገኙ የፍልስጤሞች ቤቶችንና የእርሻ ማሳዎችን ማወደሟን ከጦር ወንጀል የሚቆጠር  ብሎታል።እርምጃዉ እንዲጣራ ጠይቋልም።

የእስራኤል ጥቃትና የፍልስጤሞች እልቂት
                           
እስራኤል ባሻት ጊዜ ሲሻት ጋዛ ሠርጥን ሲፈልጋት ምዕራባዊ ዮርዳኖስ ዳርቻን፣ ካሰኛት በቦምብ፣ሚሳዬል፣ መድፍ ካስፈለጋት በቦልዶዞር ትደፈልቃለች።የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊዎች ይፎክራሉ።የፍልስጤም ባለሥልጣናት እንዳሉት ካለፈዉ መስከረም 26 ወዲሕ ጋዛ ሰርጥ ዉስጥ የተገደለዉ ፍልስጤማዊ 40,878 ደርሷል።የቆሰለዉ 94 ሺሕ 454።አብዛኞቹ ሕፃናትና ሴቶች ናቸዉ።ለጋዛ ሕፃናትና ወጣቶች ትምሕርት ብርቅ ነዉ።ለአዛዉንቶች ሕክምና፣ ምግብ፣ ንፁሕ የመጠጥ ዉኃ ቅንጦት ነዉ።ከቤት ንብረቱ ቢያንስ አንዴ ያልተፈናቀለ፣ ያልተራበ፣ ያልታረዘ ፍልስጤማዊ ማግኘት ሲበዛ ከባድ ነዉ።

ጋዛ ዉስጥ ጋዜጠኞች ለመዘገብ፣ የሕክምና ባለሙያዎች ነብስ ለማዳን፣ የርዳታ ሠራተኞች እሕል ዉኃ ለማቅረብ ካሰቡ ሕይወት-አካላቸዉን ለመገበር መወሰን አለባቸዉ።ዓመት ሊደፍን ወር ቀረዉ።
የፍልስጤሞች እልቂት፣ ስቃይ ሰቆቃዉ እንዲያበቃ ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ የተለያዩ ሐገራት ሕዝብ፣ ተማሪዎች፣ የመብት ተሟጋቾች፣ ማሕበራት፣ የዓለም ፍርድ ቤቶች ይጠይቃሉ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፖለቲካና የሠላም ግንባታ ጉዳይ ምክትል ዋና ፀሐፊ ሮዝሜሪ ዲካርሎ ሮብ ቀን ደገሙት።
                          
« ሁከት አራማጆች በሙሉ እስራኤሎች ሆኑ ፍልስጤሞች ተጠያቂ መሆን አለባቸዉ።በቅርቡ የተሰጡ አደገኛ ጠብና ጠብ ጫሪ እርምጃና መግለጫዎች ሁኔታዉን ይበልጥ እያቀጣጠለዉ ነዉ።»
ጥሪ ጥያቄዉን የሰማ እንጂ ገቢር ያደረገዉ የለም።ከዓለም ብቸኛዋ ልዕለ ኃያል ሐገር ከዩናይትድ ስቴትስና ከተባባሪዎችዋ ዙሪያ መለስ ድጋፍ የሚሰጣት እስራኤል  ወታደራዊ ዘመቻዋን ምዕራባዊ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ዉስጥም አጠናክራለች።ምዕራባዊ ዮርዳኖስ ዉስጥ የተገደለዉ ፍልስጤማዊ ቁጥር 661 ደርሷል።አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበዉ ከመስከረም 26 ወዲሕ ምዕራባዊ ዮርዳኖስ ዉስጥ ብቻ  23 እስራኤላዉያን ተገድለዋል።ገሚሱ የእስራኤል ወታደሮች ናቸዉ።

ጋዛ ዉስጥ ከተገደሉት 41 ሺሕ ያክል ሰዎች አብዛኞቹ ሕፃናትና ሴቶች ናቸዉ
የጋዛ ሕፃናት ሕክም፣ ክትባትና በቂ ምግብ ማግኘት አይችሉምምስል Ramadan Abed/REUTERS

የእስራኤል ባለሥልጣናት አቋምና ፍልስጤሞች

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእስራኤል አምባሳደር ዳኒይ ዳኖን ባለፈዉ ሮብ እንዳሉት ግን እስራኤል የምታደርገዉን ሁሉ የምታደርገዉ ሐማስን ለመበቀል ነዉ።
                                     
«ጥረታችንን እንድናቆም፣ ጠመንጃችንን እንድንፈታና ጋዛ ዉስጥ የምንዋጋዉ ለምን እንደሆነ የሚጠይቁ ብዙ ድምፆች እንሰማለን።መስከረም 26 የተፈፀመዉን ጭፍጨፋ፣እገታና ጋዛ ዉስጥ አሁን ታጋቾች ያሉበትን ሁኔታ መገንዘብ አይቻልም።ጋዛ የዘመትንበትን ምክንያት ብዙዎቻችሁ ረስታችሁታል።ምናልባት እናንተ ረስታችሁት ይሆናል።እኛ ግን አንረሳዉም።»

እስራኤል፣ ዩናይትድ ስቴትስ የአዉሮጳ ሕብረት፣ ብሪታንያና ተባባሪዎቻቸዉ በአሸባሪነት የፈረጁት ሐማስ ባለፈዉ መስከረም 26፣2016 ደቡባዊ እስራኤልን ወርሮ 1200 ያክል የእስራኤልና የሌሎች ሐገራትን ዜጎች መግደሉን የእስራኤል ባለስልጣናት አስታዉቀዋል።ሐማስ ካገታቸዉ ሰዎች መካካል ከ100 የሚበልጡት እስካሁን እንደታገቱ ነዉ።በዓለም አቀፉ ድርጅት የፍልስጤም አማባሳደር ሪያድ መንሱር እንደሚሉት ግን የእስራኤል እርምጃ ሐማስን ከመበቀል ያለፈ ነዉ።
                                 
«እስራኤል በፍልስጤም ሕዝብ ላይ ሙሉ ጦርነት ከፍታለች።እስራኤል ሐገር በማጥፋት ግጭቱን በወታደራዊ ኃይል ለመፍታት እየጣረች ነዉ።ይኽን እዉነት መካድ አይቻልም።እስራኤል የቅኝ ገዢነት ዓላማዋን ከግብ ለማድረስ ከዘር ማጥፋት ወንጀል እስከ ዘር መድሎዎ ርምጃ በመዉሰድ በጣም ከፍተኛ ጥፋት ለማድረስ እንደምትፈልግና መዘጋጀቷንም ለዓለም እያሳች ነዉ።»

በብዙ ሺሕ የሚቆጠር የእስራኤል ሕዝብ ሐማስ ያገታቸዉ ሰዎች እንዲፈቱ ባደባባይ ሰልፍ እየጠየቀ ነዉ
በብዙ ሺሕ የሚቆጠር የእስራኤል ሕዝብ ሐማስ ያገታቸዉ ሰዎች እንዲፈቱ ባደባባይ ሰልፍ እየጠየቀ ነዉምስል Mostafa Alkharouf/Anadolu/picture alliance

አለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ እስራኤል ከግዛትዋ ጋር በሚዋሰነዉ የጋዛ ሠርጥ ጠረፎች የሚገኙ መኖሪያ ቤቶችን፣ ማሳዎችን፣ትምሕርት ቤቶችና መሳጂዶችን እያፈራረሰች ነዉ።ድርጅቱ ይፈፃማል ያለዉ የጦር ወንጀል እንዲጣራ ጠይቋልም።

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ ተክሌ