አዲሱ የአውሮጳ ኅብረት የስደተኞች አቀባበል ስምምነትና ተቃውሞው
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 16 2016አዲሱ የአውሮጳ ኅብረት የጋራ የስደተኞች አቀባበል ስምምነት
የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት የጋራ የስደተኞች አቀባበል ስርዓት ለመዘርጋት ባለፈው ሳምንት የመጀመሪያ ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ይህ ትልቅ መሠረታዊ ለውጥ የተባለው ስምምነት በራሱ በአውሮጳ ኅብረትና በኅብረቱ ምክርቤት አድናቆት ተችሮታል። ስምምነቱ በጥቅሉ 27 ቱ የኅብረቱ አባል ሀገራት ስደተኞችን የሚከፋፈሉበትን ስልት ፣ ተጨማሪ የስደተኞች ማቆያ ማዕከላትን ፣ የተፋጠነ ጥረዛንና ሌሎች እቅዶችም ያካትታል። የዛሬ 8 ዓመት በተለይ ከሶሪያ የመጡ የሚያመዝኑባቸው ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ወደአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት ከገቡ በኋላ ኅብረቱ የጋራ የስደተኞች አቀባበል ስርዓት ለመዘርጋት በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ደረጃዎች ጥረቶች ቢያደርግም መስማማት ተስኖት ቆይቷል።
ያም ሆኖ ኅብረቱ የውጭ ድንበሮቹን ጥበቃና የተገን አሰጣጥ ሕግጋቱን በማጠናከር እና የስደተኞች መተላለፊያ ከሆኑ ከመካከለኛው ምሥራቅና ከሰሜን አፍሪቃ ሀገራት ጋር ውል በመፈረም ሕገ ወጥ የሚላቸው ተገን ጠያቂዎች እንዳይገቡበት ሲከላከል መቆየቱም ግን አልቀረም። ታዲያ ለዓመታት የጋራ የስደተኞች አቀባበል ስምምነት ላይ መድረስ ተስኖአቸው የቆዩት 27ቱ የኅብረቱ አባል ሀገራት በጎርጎሮሳዊው 2023 መገባደጃ ላይ እንዴት ተሳካላቸው? ትኩረታችን ወደ አዲሱ የጋራ የስደተኞች አቀባበል ስናደርግ በአሁኑ ስምምነት የተካተቱ አዳዲስ የአሰራር ስልቶች አሉ። የብራሰልሱ ዘጋቢያችን ገበያው ንጉሴ ስምምነቱን በሦስት ጉዳዮች ላይ አንድ ዓይነት አሰራር ለመከተል የሚያስችል ስምምነት ሲል ገልጾታል።አደገኛው የባሕር ላይ ስደትና እልቂት
እነዚህም ስደተኞችን መቆጣጠሪያ ስልት ፣ ስደተኞች በ27ቱ የኅብረቱ አባል ሀገራት የሚዘዋወሩበት መንገድ እንዲሁም ስደተኞችን እንዴት ወደ ሦስተኛ ሀገር መላክ እንደሚቻል የሚመለከቱ ናቸው። ገበያው እንደሚለው አዲሱ ስምምነት በተለይ የኅብረቱ ድንበር ለሆኑ ሀገራት ተጨማሪ ሥልጣን የሚሰጥ ነው። ስደተኞች ቢቻል እንዳይገቡ መከከላከል ፣ከገቡም በኋላ ለማባረር የሚያስችላቸው ስልጣን ነው የተሰጣቸው።ጣልያንን የመሳሰሉ ሀገራት ስደተኞችን ማስተናገድ ያለባቸው በጄኔቫው ስምምት መሠረት ነው ።ይሁንና አህሁን የአውሮጳ ኅብረት ድንበር የሆኑ ሀገራት ድንበር የሚቆጣጠሩበትን አቅም በጋራ ማጎልበት ለስደተኞቹም የማሠሪያ ካምፕ በማዘጋጀት እዚያ ከዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ አጣርተው ተገን ማግኘት ይችላሉ የተባሉትን ተገን ሰጥተው ተቀባይነት ያላገኙትን ደግሞ ወደ ሦስተኛ አገር እንዲልኩ ሥልጣን የሚሰጥ ነው።ሦስተኛው ሀገር ደግሞ ለምሳሌ ጣሊያን ስደተኞችን ለመውሰድ የተስማማችበት ቱንዝያ ወይም ሌሎች ሀገራት ሊሆኑ ይችላሉ
በከዚህ ቀደሙ የኅብረቱ አባል ሀገራት ውል መሠረት ስደተኞች ተገን መጠየቅ ያለባቸው መጀመሪያ እግራቸው በረገጠበት የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገር ነው። ይህ አሁንም እንዳለ ሆኖ በአዲሱ ሕግ የስደተኞቹ ቁጥር ከበዛ ወደ ሌሎች ሀገራትም ሊላኩ ይችላሉ፤ የስደተኞች ማመልከቻዎችም በገቡባቸው ሀገራት ከቀድሞው ባጠረ ጊዜ መልስ እንዲያገኙ ይደረጋል ፣ ተቀባይነት ያላገኙትንም በፍጥነት ማባረር ይቻላል። በእነዚህ አዳዲስ አሰራሮች ስደተኞች እንደቀድሞው ይግባኝ የሚሉበትንና ሌሎንችም እድሎች ላያገኙ ይችላሉ። በስደተኞች ቀውስ ላይ የመከረው የአውሮጳ ኅብረት ኅብረቱ ለዓመታት ሳይስማማበት ቆይቶ አሁን በጋራ የስደተኞች አቀባበል ደንብ ላይ ወደተስማማበት ምክንያት ስንመለስ ከምክንያቶቹ አንዱ የኅብረቱን አንድነት ጥያቄ ውስጥ የጣለው በኅብረቱ ውስጥ ስደተኞችን የሚመለከት ወጥ አሰራር አለመኖር ይገለፃል። አባል ሀገራት አሁን የጋራ የስደተኞች አቀባበል ሕግ ላይ እንዲስማሙ ያስገደዳቸው ከዚህ የገዘፈ ሌላ ዐቢይ ምክንያትም አለ። ይኽውም በአባል ሀገራት የሚሰጣቸው ድጋፍ እየጨመረ የሄደው የብሔረተኞች ጉዳይ ነው። ብሔረተኞች ምርጫ በተቃረበ ቁጥር መራጮችን ለመሳብ የሚጠቀሙበት አንዱ ዘዴ የስደተኞችን ጉዳይ አጀንዳ አድርጎ ማንሳት በመሆኑ ለዚህ ጥያቄ የበኩላቸውን መፍትሄ ቀድመው ለህዝቡ ለማቅረብ ነው።
የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት በእነዚህ ምክንያቶች የተስማሙበት የጋራ የስደተኞች አቀባበል ከመብት ተሟጋቾችችና ስደተኞችን ከሚረዱ በርካታ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ተቃውሞ ተነስቶበታል። የአውሮጳ ኅብረት የፍልሰትና የጥገኝነት አሳጣጥ ፖሊሲ ማሻሻያኦክስፋም የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት አዲሱን ደንብ ከቀድሞው የባሰ፣ ሰብዓዊ መብቶችንና የስደተኞች ሕግን ቁልፍ መርኆች የሚያፈርስ ሲል ተቃውሞታል። በጀልባ የሚሰደዱ ሰዎችን ከመስጠም የሚታደገው ሲ ዋች የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት ስምምነቱ በርካታ ስደተኞች ህይወታቸው በባህር ላይ እንዲያልፍ የሚያደርግ ነው ሲል ተችቷል።ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናልም ስምምነቱን በጥብቅ ከተቃወሙት መካከል አንዱ ነው።
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት