1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ውሳኔ እና የሚጠበቁት አዳዲስ ክልሎች ጉዳይ

እሑድ፣ ነሐሴ 8 2014

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ከተቋቋመ ከ29 ዓመታት ገደማ በኋላ ሙሉ በሙሉ ታሪክ ለመሆን እየተዘጋጀ ነው። የአስራ ስድስቱ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ምክር ቤቶች ውሳኔ አንድምታ ምንድነው? የክላስተር አወቃቀርን ያልተቀበለው የጉራጌ ዞን ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል? ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ባለሙያዎች ለውይይት ጋብዘናል።

https://p.dw.com/p/4FThw
Äthiopien Gurage Streik
ምስል privat

እንወያይ፦ የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ውሳኔ እና የሚጠበቁት አዳዲስ ክልሎች ጉዳይ

በ1985 የተቋቋመው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ሌሎች ሁለት መስተዳድሮች ወልዶ ታሪክ ለሚያደርገው ተጨማሪ ሒደት በዝግጅት ላይ ይገኛል። የክልሉ አስራ ስድስት ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች በተናጠል ነገር ግን በተመሳሳይ ቀን ሌሎች ሁለት ክልሎች የሚያቋቁም የውሳኔ ሐሳብ አጽድቀው ሐምሌ 28 ቀን 2014 ለኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርበዋል። ከዚህ ቀደም የዞን ምክር ቤቶች ያሳለፏቸው ውሳኔዎች ለደቡብ ክልል ምክር ቤት ቀርበው ሕዝበ ውሳኔ ከተካሔደ በኋላ የሲዳማ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ተቋቁመዋል። 

ለኢትዮጵያ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ አዎንታዊ ምላሽ ካገኘ የወላይታ፣ ኮንሶ፣ የደቡብ ኦሞ፣ ጎፋ፣ ጋሞ እና ጌዲዖ ዞኖች ከአማሮ፣ አሌ፣ ቡርጂ፣ ባስኬቶ እና ደራሼ ወረዳዎች በመጣመር አንድ ክልል ያቆማሉ። የሐድያ፣ ሐላባ፣ ከምባታ ጠምባሮ እና ስልጤ ዞኖች ከየም ልዩ ወረዳ ጋር በመሆን ሁለተኛውን ክልል ለማቆም የወሰኑ ናቸው። ሐድያ፣ ከምባታ፣ የቀድሞዎቹ አላባ እና ጠምባሮ እንዲሁም ስልጤን ይጨምር የነበረው የጉራጌ ዞን እና የም ወረዳ የአሁኑ የደቡብ ክልል ከመቋቋሙ በፊት ክልል ሰባት ተብለው በአንድ የተደራጁ ነበሩ። 

የጉራጌ ዞን ምክር ቤት በአንጻሩ ሐሙስ ነሐሴ 5 ቀን 2014 ባካሔደው አስቸኳይ ስብሰባ በክላስተር ከሚቋቋሙት ክልሎች በአንዱ እንዲካተት የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ውድቅ አድርጓል። እንዲህ አይነት ውሳኔ በማሳለፍ የጉራጌ ዞን የመጀመሪያው ነው። የዞኑ ምክር ቤት በጉራጌ ዞን የሚገኙ ሶስት ብሔሮች የራሳቸውን ክልል እንዲያቋቁሙ የሚጠይቅ ውሳኔ ያሳለፈው በ2011 ነበር። 

ይኸ ውይይት የተካሔደው ሐሙስ ነሐሴ 5 ቀን 2014 ነው። ውይይቱ በተካሔደ በሁለተኛው ቀን ማለትም ቅዳሜ ነሐሴ 7 ቀን 2014 በጉራጌ ዞን ውስጥ የሚገኙ አራት ወረዳዎች እና አንድ የከተማ አስተዳደር ከሌሎች ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ጋር በመጣመር አዲስ ክልል ለመመስረት የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ አጽድቀዋል። የውሳኔ ሐሳቡን ያጸደቁት የማረቆ፣ ቀቤና፣ የመስቃን፣ የምስራቅ መስቃን ወረዳዎች እንዲሁም የቡታጅራ ከተማ ምክር ቤቶች ናቸው። 

ይኸ የውይይት መሰናዶ አስራ ስድስቱ የደቡብ ክልል ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ያሳለፉትን ውሳኔ አንድምታ እና የጉራጌ ዞንን ጉዳይ ይዳስሳል። በዚህ ውይይት የጉራጌ ዞን ክልል ለመሆን ያቀረበውን ጥያቄ በቅርበት የሚከታተሉት አቶ መሐመድ አብራር እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፌዴራሊዝም እና አስተዳደር የፒኤችዲ ዲግሪያቸውን በማጥናት ላይ የሚገኙት የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር አቶ ኩሌ ኩርሻ ተሳትፈዋል።

የደቡብ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሰናይት ሰለሞን ለመሳተፍ ፈቃደኝነታቸውን ገልጸው የነበረ ቢሆንም ውይይቱ በሚካሔድበት ወቅት ስልካቸውን ሳያነሱ ቀርተዋል። የብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ክልል ጽህፈት ቤት ተወካዮች እንዲሳተፉ ያቀረብንው ግብዣ ተቀባይነት አላገኘም። 

ሙሉ ውይይቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ