1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተነቃቃችው ጅማ በኦሮሚያ ክልል የሰላም ደሴት

ሐሙስ፣ ጥር 16 2016

ጅማ ከአንጋፋዎቹ የኢትዮጵያ ከተሞች በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀስ ከተማ ናት። የአካባቢው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው ተቀዛቅዞ የታሪኳን ያህል ወደፊት ያልተጓዘች ከተማና አካባቢ ሆና ሰንብታለች። አሁን አሁን ግን በተለይም ከበርካታ የኦሮሚያ አካባቢዎች እጅጉን የተሻለ አንጻራዊ ሰላም የሚታይበት ይህ አካባቢ በኢኮኖሚውም ቢሆን የተነቃቃ መስሏል።

https://p.dw.com/p/4bfjB
ጅማ ከተማ
ጅማ ከተማ ምስል Seyoum Getu/DW

ጅማ እና ሰላም

 

ጅማ ከአንጋፋዎቹ የኢትዮጵያ ከተሞች በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀስ ከተማ ናት። ለዘመናት ግን የአካባቢው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው ተቀዛቅዞ የታሪኳን ያህል ወደፊት ያልተጓዘች ከተማና አካባቢ ሆና ሰንብታለች። አሁን አሁን ግን በተለይም ከበርካታ የኦሮሚያ አካባቢዎች እጅጉን የተሻለ አንጻራዊ ሰላም የሚታይበት ይህ አካባቢ በኢኮኖሚውም ቢሆን የተነቃቃ መስሏል። 

የጅማ ታሪካዊ ስኬቶች

«አባ ጂፋር ብልህ ዲፕሎማት ናቸው ሲባልላቸው በይበልጥ ሰላም ከሁሉም ይበልጣል በሚል አባባላቸው ይታወቃሉ። ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ጀምሮ እስከ 1933 ጅማን ባስተዳደሩበት በሳቸው የአስተዳደር ዘመን ጅማለተከታታይ 20 ዓመታት ቡናን ቀጥታ ወደ ውጪ የላከች ሃብታም አካባቢ ነበረች። ጦርነትም በደጃቸው ቢመጣ በሰጥቶ መቀበል መርህ የአካባቢውን አስተዳደር አስጠብቀው በሰላም መርተው አልፈዋል።» ይህን አስተያየት ለዶይቼ ቬለ ያጋሩ የጅማው ቤተ መጽሐፍት የሚባሉት አብዱልከሪም አባገሮ ናቸው። በወጣትነታቸው በነበራቸው የእግር ኳስ ጫዋታ ብቃት «አብዱልከሪም ፔሌ» በሚል ቅጽል ስም የሚወደሱት አብዱልከሪም እውቅናን ካተረፉበት እግር ኳሰ ጨዋታ ባሻገር በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ ባላቸው የታሪክ አዋቅነታቸውንም ሁሉም ይናገርላቸዋል።

ጅማ
«አባ ጂፋር ብልህ ዲፕሎማት ናቸው ሲባልላቸው በይበልጥ ሰላም ከሁሉም ይበልጣል በሚል አባባላቸው ይታወቃሉ።» ይላሉ ታሪክ አዋቂው የከተማ ነዋሪ አብዱልከሪም አባገሮ። ምስል Seyoum Getu/DW

ጅማ እና ሰላም

የአካባቢው ታሪክ እንዲጠበቅ፣ የቱሪስት መስዕብ እንዲሆን እና ለእድገቱም ተቆርቋሪ ይሏቸዋል።  አብዱልከሪም አሁን የለውጥ አመቻች በእንግሊዝኛ ምህጻሩ (FC) በተባለ ግብረሠናይ ድርጅት ውስጥ በመሥራት ላይ ይገኛሉ።

ስለትናንቷ ጅማ አውርተው የማጠግቡት አብዱልከሪም ጅማ ቡናው እንኳ ለሰላም እና ለአብሮነት የሚጠጣ ነው ይሉታል። በተለይም በስምንተኛው የሸነን ጊቤ ንጉሥ አባጂፋር ዳግማዊ ዝናዋ ናኝቶ ትልቅ ስነለበረችው ጅማ ሲያወጉም ጥልቅ ሃሴት ከፊታቸው ይነበባል። ግን ደግሞ ይላሉ፤ «በደርግ ዘመነ መንግሥት መጨረሻ በጅማ ላይ የተናደው የፖለቲካ ቀውስ እስካሁንም ያልሻረ ቁስል ጥሎ አልፏል» ይላሉ። «ያ ወርቃማ አገር በደርግ ጊዜ ተጎዳ ተሰበረ፡፡ ሥራ ፈጣሪ ነጋዴና ብልህ ልጆቿን አጣች» ሲሉማ ቁጭታቸውን ከጅማ ታሪካዊ ማሽቆልቆል ጋር አያይዘው አነሱ። «በዚያን ዘመን ስድስት በረራ በቀን የነበራት ጂማ ያረጀች ከተማ ተባለች» ሲሉም ቁጭታቸውን ይገልጻሉ።

 የጅማ ከተማ ነዋሪው አብዱልከሪም አባገሮ
የጅማ ከተማ ነዋሪው አብዱልከሪም አባገሮምስል Seyoum Getu/DW

ታሪካዊቷ ጅማ ከተማ እና አካባቢው የዓመታት እርጅና የተጫጫናቸውመሆኑ አሁንም በጉልህ ቢታይም አሁን አሁን አካባቢው ተስፋን የሰነቀ ግን መስሏል። ዶይቼ ቬለ ከሰሞኑ በጅማ ከተማ እና በጅማ ዞን ውስን ወረዳዎች ቅኝት ባደረገበት አጋጣሚም ይህንኑ ታዝቧል። በጅማ ከተማ ዕድሜ የተጫጫናቸው የመሰሉ ታሪካዊ ቤቶች እና ቅርሶች እድሳት እየተደረገላቸው፤ የተጎሳቆሉ ቤቶችም በአዳዲስ ግንባታዎች ለመተካት የሚደረጉ ጥረቶች ጎልተው ይታያሉ።

ከሰላም ጋር የሚቆራኘው የኢኮኖሚው መነቃቃት

ከከተማዋ ወጣ ወዳሉ ወረዳዎች የሚወስዱ ለዘመናት ነዋሪዎቿን ያማረሩ የጥርጊያ እና ጠጠር መንገዶችንም በዘመናዊ የአስፓልት መንገዶች የመተካት ጥረቶች ታክለውበት የአካባቢው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ተስፋ እንደሚሆኑ ለመገመት አያዳግትም። በተለይም ጅማ ዞንን ከኢሉባቦር እና ቡኖ በደሌ ዞኖች ጋር የሚያገናኘው የጅማ-አጋሮ አስፋልት መንገድ ከነበረበት ደረጃ ከፍ ብሎ እየተሠራ ነው። ምናልባት መንገዱ ደረጃውን ጠብቆ በጊዜው የሚጠናቀቅ ከሆነም ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የሚያጠያይቅም አይደለም። ከዚህም ሌላ በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚሠሩ የመንገድ ግንባታዎች እና ሌሎች የኢኮኖሚው ትሩፋቶች የጂማን መነቃቂያ ዕለት የሚያቀርቡ ይመስላል።

ጅማ ከተማ
ጥንታዊቱ ከተማ ጅማ ምስል Seyoum Getu/DW

አገሩ እጅጉን አረንጓዴ ነው። በየአቅጣጫው ደን ነው የሚታየው። በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም ኦሮሚያ ክልል በምዕራብ እና ደቡብ አቅጣጫ ነዋሪዎችን እንዲታክቱ ያደረገው የሰላም እጦት በዚህ ስጋት አይደለም። ነዋሪቿ ሌትም ይሁን ቀን እንዳሻቸው ከከተማ ከተማ ይንቀሳቀሳሉ። በጅማ ከተማም ቢሆን እንዲህ ያለ ነገር ለጊዜው ስጋት አለመሆኑን ነዋሪዎቿም አፋቸውን ሞልተው የሚናገሩት ነው።

ዶይቼ ቬለ ቅኝት ባደረገባቸው የማና፣ ጎማ፣ ሰቃ እና ሸበሶምቦ ወረዳዎችም ይህንኑን ተመልክቷል። የአካባቢው ፍጹም መረጋጋት ነዋሪዎቹ በኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ያበረታታቸው ይመስላል።

የጅማው ታሪክ ነጋሪ አብዱልቃዲር አባገሮም በትውልድ ቀዬያቸው አሁን ተስፋን ሰንቅዋል። ጅማ ትንሣኤዋ የቀረበ መስሏል ሲሉም የአካባቢውን ኢኮኖሚ የመነቃቃት ጥረቱን በአበረታች ቃል ይገልጹታል። ከጂማ ከተማ ወጣ ብሎ የሚገኘው የቱሪስት መስህቡ የአባጂፋር ቤተመንግሥት አሁን በእድሳት ላይ ይገኛል። ሰላሟን እንዲሁ ካዘለቀላት ደኖቿን ጨምሮ ጅማ የቱሪስትን ቀልብ የሚገዙ በርካታ ስፋራዎች እንዳሏት ተመልክተናል።

ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ