1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጃራ ካምፕ ተፈናቃዮች እሮሮ

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 17 2016

ከኦሮሚያ እና ቤኒሻንጎል ጉሙዝ ክልሎች በተለያዩ ጊዜያት ባጋጠማቸው ግጭቶች ተፈናቅለው ወደ ሰሜን ወሎ ዞን ሃብሩ ወረዳ ጃራ የመጠለያ ካምፕ የተጠለሉ ተፈናቃዮች በተለያዩ ጊዜያት በሚደርስብን የጸጥታ ችግር ተማረናል ሲሉ ለዶይቸ ቬለ ገለፁ።

https://p.dw.com/p/4Y9Th
Alamata Flüchtlingsunterkünfte Jara in Region Amhara
ምስል Alamata City Youth League

የጃራ ካምፕ ተፈናቃዮች እሮሮ

ከዚህ በፊት ከምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ በተከተሰ ግጭት ተፈናቅለው አሁን ላይ በጃራ ተፈናቃዮች ካምፕ መጠለላቸውን የገለጹት አንድ ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን ተፈናቃይ፤ የከትናንት በስቲያ ሃሙሱ ጥቃት የተደጋገሙ ጥቃቶች አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ “ከዚህ በፊትም በሚያጋጥሙን የጸጥታ ችግሮች ሶስት ሰዎች ሞተውብናል፡፡ መኃል ላይም የሰዎች እገታ ተፈጽሞ ያውቃል፡፡ ሰሞኑን ሃሙስ በተፈጠረው ጥቃት ደግሞ አንድ ሰው ሞቶ ሌላኛው ተጠቂ በሆስፕታል በህክምና ላይ ይገኛል፡፡ በእለቱ እዚሁ አጎራባች አከባቢ ጭፍራ ከሚባል ጫካ ውስጥ የመጡ ታጣቂዎች ናቸው ተውክስ ከፍተው ጠጄ የምትባል የ23 ዓመት ወጣት ሴት እና አወቀ የሚባል የስድስት ዓመት ልጅ በጥይት መትተው ወጣቷ ሴት ወዲያው ሆስፒታል እንደደረሰች ህይወቷ አለፈ፡፡ የ6 ዓመት ልጁ ደግሞ አሁንም ድረስ በህክምና ላይ ነው፡፡”
በዚሁ ተፈናቃዮችን ባሰጋው የጸጥታ ተግዳሮት ላይ ሌላኛውም አስተያየት ሰጪ ተፈናቃይ ሃሳባቸውን ቀጠሉ; “መጀመሪያ ጥር 30 ሁለት ሰዎች በጥይት ተመተው ቆሰሉ፡፡ ከዚያን ግንቦት 8 አንድ 70 ዓመት አዛውንት እጁን በጥይት ተመተው ቆስለዋል፡፡ ሰኔ 20 ማሞ አውራሪስ የሚባል ሰባት ቤተሰቦች የሚያስተዳድር ደሃ እንጨት ለቅሞ ሽጦ ዳቦ ለልጆቹ ለማጉረስ ሲል ተመቶ ተገድሏል፡፡ በቅርቡ መስከረም ላይ አንድ ወጣት ታግቶ ተወስዶ መከላኬ መልሶታል፡፡ አሁን ደግሞ የ23 ዓመት ወጣት ከቤተሰቦቿ ጋር ለእንጨት ለቀማ እንደወጣት በሁለት ጥይት ተመታ ተገድላለች፡፡ የ6 ዓመት ታዳጊ ደግሞ ከቤት እያለ ነው በጥይት ቆስሎ ሆስፒታል የገባው፡፡”
መሰል ጥቃቶችን ተፈናቃይ ዜጎች ላይ በማነጣጠር የሚፈጽመው ማን ይሆን የተባሉት ተፈናቃዮቹ የታጣቂዎቹን ማንነት እንደማያውቁ ያስረዳሉ፡፡ ይሁንና በሚደርሰው ጥቃት ተፈናቃዮቹ ላይ የሚደርስ ጥቃቱ ሁሌም እንደሚያሳዝናቸው ይገልጻሉ፡፡
እንደ ተፈናቃዮቹ አስተያየት በጃራ ተፈናቃዮች ካምፕ ከ10 ሺህ በላይ የሚሆኑ በተለያዩ ጊዜያት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እንዲሁም ምእራብ ኦሮሚያ ከምስራቅ ወለጋ እና ምእራብ ወለጋ ዞኖች በተከሰቱ ግጭቶች ተፈናቅለው የመጡ ናቸው፡፡ “እዚህ ያሉት ተፈናቃዮች በቁጥር ወደ 10 ሺህ 439 አከባቢ ናቸው፡፡” 
ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ውስጥ ከ 400 በላይ ሰዎች ያለቁበትን ጥቃት ተከትሎ አለመረጋጋቱን ሸሽተው ወደ መጠለያ ካምፑ መግባታቸውን የሚገልጹት ሌላኛው ተፈናቃይም የጸጥታ ስጋቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መጥቷል ነው የሚሉት፡፡ “እዚህ ባለንበት ጃራ ካምፕ በተለያዩ ጊዜያት በሚፈጸም ጥቃት የሚሞት ተፈናቃይ አሳሳቢ ሆኖብናል፡፡”
ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ 42 ከሚባል ሰፈራ ካምፕ መፈናቀላቸውን የገለጹልን አስተያየት ሰጪም፡ “አሁን ሰሞኑን ድንገት በተከፈተው ተኩስ እህታችንን አጥተናታል፡፡ እዚህ የደረስነው ወንዝ አቋርጠን በብዙ መከራ ነው፡፡ አሁንም ያለነው በስጋት ነው፡፡”
ተፈናቃዮቹ ይደርስብናል ካሉት ከጸጥታ ስጋቱ በተጨማሪ፤ የሚደርሳቸው የእርዳታ አቅርቦትም አመርቂ ያልሆነ ነው ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ “ከካምፑ ላይ የሚመጣ እርዳታ ምንም ያህል በቂ ባለመሆኑ አቅመ ደካሞች በተለይም በጣም እየተጎዱብን ነው፡፡ ከሰሞኑ የተወሰነ እርዳታ ደርሶናል፡፡ በብዛት ሰው እየተሳሰበ ነው ቀኑን እየገፋ ያለው” ብለዋል፡፡
ስለተፈናቃዮቹ እሮሮ አስተያየትና ምላሽ ለማግኘት ለአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተማመሪያ ኮሚሽን እና ለሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊዎች ብንደውልም ስልካቸው አይሰራም፡፡ ለክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መንገሻ ፋንታው ስንደውልም ስብሰባ ላይ መሆናቸውን ገልጸው አስተያየታቸውን ሳያጋሩን ቀርተዋል፡፡

እናቶች እና ህፃናት
በጃራ ካምፕ የተጠለሉ እናቶች እና ህፃናትምስል Alemenw Mekonnen/DW
ተፈናቃዮች
ከኦሮሚያ እና ቤኒሻንጎል ጉሙዝ ክልሎች በተለያዩ ጊዜያት ባጋጠማቸው ግጭቶች ተፈናቅለው ወደ ሰሜን ወሎ ዞን ሃብሩ ወረዳ ጃራ የመጠለያ ካምፕ የተጠለሉ ተፈናቃዮችምስል Alemnew Mekonnen/DW

ሥዩም ጌቱ

ልደት አበበ