1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን እና የእስራኤል ግንኙነት

ማክሰኞ፣ ግንቦት 28 2010

በአይሁዳውያን ላይ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ጀርመን እና እስራኤልን በልዩ መንገድ አስተሳስሯቸዋል። ሁለቱ ሀገራት የናዚ አገዛዝ ካበቃ ከ70 ዓመት በኋላ ዛሬ ከሞላ ጎደል መደበኛ የሚባል ግንኙነት ጀምረዋል።

https://p.dw.com/p/2yyOi
Deutschland Benjamin Netanjahu, Premierminister Israel & Angela Merkel in Berlin
ምስል Reuters/A. Schmidt

« የጀርመን ቦታ ሁሌ ከእስራኤል ጎን ነው።»

እርግጥ፣ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ትናንት በጎበኙዋት ጀርመን እና በሀገራቸው መካከል በፖለቲካው ዘርፍ ስምምነት እንዳለ ሁሉ ልዩነትም አልጠፋም።  

ስድስት ሚልዮን አይሁዳውያን በናዚ ጀርመን የተጨፈጨፉበት ወንጀል በጀርመን እና በእስራኤል ግንኙነት ላይ የማይረሳ  ታሪክ እንደሆነ ይቆያል።  ያም ቢሆን ግን የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት፣  በጎርጎሪዮሳዊው 1965 ዓም ዲፕሎማቲክ ግንኙነት ከጀመሩ ወዲህ፣ በጀርመን መንግሥት በኩል ጉልህ እድገት ታይቶበታል።  ሁለቱ ሀገራት ፈጥነው እርቅ ላወረዱበት ድርጊት የእስራኤል የመጀመሪያ ጠቅላይ ሚንስትር የነበሩት ዴቪድ ቤንጉርዮን ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።  እስራኤል ሌላኛዋን ጀርመን እንድትመለከት ጥረት አድርገዋል። ት ቤን ጉርዮን እና የመጀመሪያው የጀርመን መራሔ መንግሥት ኮንራድ አድናወር  በ1960 እና 1966 ዓም ሁለት ጊዜ ብቻ ቢገናኙም፣ የሩቅ ወዳጆች ያህል ነበር የሚቆጠሩት። ጀርመን እና እስራኤል ዛሬ በአጋርነት ላይ ያተኮረ ግንኙነት መስረተዋል። አላቸው። ከጥቂት ወራት በፊት እስራኤልን የጎበኙት የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሀይኮ ማስ ጀርመን ሁሌም ከእስራኤል ጎን መቆሟን ተናግረዋል።
« በዓላማዎቻችን ላይ ከሞላ ጎደል በሁሉም የምንስማማ ይመስለኛል። እነዚህን ዓላማዎች ከግብ ከማድረሱ ላይ በምንከተለው መንገድ ላይ እርግጥ ልዩነት አለ። ይሁንና፣ በነዚህ ጥያቄዎች ላይ በጠቅላላ የጀርመን ቦታ ከእስራኤል ጎን ነው። »
 በአይሁዳውያን ላይ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋን ማስታወስ ትልቅ ቦታ ቢይዝም፣ ሁሉ ነገር በዚያ ብቻ የሚወሰን መሆን እንደሌለበት እስራኤላዊው አሳታሚ ሚሻኤል ቮልፍዞን በማመልከት፣ የዘር ማጥፋቱ ጭፍጨፋ ብቻውን ለእስራኤል ምስረታ ምክንያት ነው በሚል የሚሰማው  አባባል ሊስተካከል እንደሚገባው አሳስበዋል።
«  እዚህ ላይ እርማት ማድረግ አለብን፣ እስራኤል ካለዘር ማጥፋቱ ጭፍጨፋም ቢሆን ልትመሰረት በቻለች ነበር፤ ስድስት ሚልዮን አይሁዳውያንንም በሕይወት መቆየት በቻሉ ነበር። »
ጀርመን እና እስራኤል ዛሬ በብዙ ጉዳዮች ላይ ይስማማሉ። ይሁንና፣ የሚያጣሏቸው፣ ለምሳሌ፣ እስራኤል በያዘችው የፍልስጤማውያን ግዛት የሚካሄደው የሰፈራ ግንባታን የመሳሰሉ ጥያቄዎችም አሉ። በሰፈራ ግንባታው ላይ የሚነሳውን ጥያቄ በተመለከተ  ብዙ እስራኤላውያን ጀርመናውያንን እና አውሮጳውያን  ሁኔታውን በብዛት በጠላት ሀገራት በተከበበች እስራኤል ቦታ ሆነው አልተመለከቱትም በሚል ይወቅሷቸዋል።  እስራኤል ከፍልስጤማውያን ጋር ያላት ውዝግብ ከመቶ ዓመት በላይ እንደሆነው የምትናገርበት አባባል  ባንድ በኩል ትክክል ቢሆንም፣ የምታነሳውን የፀጥታ ስጋት አውሮጳውያኑ ሊረዱት እንደማይችሉ በበርሊን የሚገኘው የፖለቲካ ጥናት ተቋም ተንታኝ ፔተር ሊንትል አስረድተዋል። ሆኖም፣ እንደ ተንታኙ ትዝብት፣ ጀርመን ከእስራኤል ጋር የምታሳየው ትብብር የጀርመን መንግሥት የሚከተለው መርህ አካል መሆኑን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በ2008 ዓም በእስራኤል ምክር ቤት ባሰሙት ንግግር አረጋግጠዋል።
« እያንዳንዱ የጀርመን መንግሥት እና ከኔ በፊት የነበሩት  መራሕያነ መንግሥት  ሁሉ ለእስራኤል ፀጥታ ልዩ ታሪካዊ ኃላፊነት ነበራቸው። » 
እስራኤላውያን በአሁኑ ጊዜ በጀርመን እና በአውሮጳ ከግራ፣ ከቀኝ እና ከሙስሊም አክራሪ ቡድኖች በኩል እየተስፋፋ የመጣውን ፀረ ሴማዊነት በቅሬታ እየተከታተሉት ነው፣ በሌላ በኩል  ጀርመናውያን በእስራኤላውያን እና በፍልስጤማውያን መካከል ሰላማዊ መፍትሔ ሊመጣ የሚችልበት ጠቋሚ ምልክት እንደተጓደለ ነው የሚሰማቸው። ይህ በዚህ እንዳለ፣  ከብዙ ጊዜ ጀምረው ሁለቱ የእስራኤል ዋነኛ የንግድ አጋሮች የሆኑት ጀርመን እና ዩኤስ አሜሪካ ለእስራኤል በተደጋጋሚ ባህር ሰርጓጅ መርከቦች አቅርበዋል። በርካታ የጋራ ምርምር ፕሮጀክቶችም አሏቸው። ይሁን እንጂ፣ የሀገራቱ ፖለቲካዊ ግንኙነት ባጠቃላይ  ከውጥረት ነፃ አለመሆኑ ይታያል። 

Angela Merkel in Israel
ምስል picture-alliance/dpa/S. Scheiner
Kommentarbild Michael Wolffsohn
ሚሻኤል ቮልፍዞን ምስል picture-alliance/dpa/K. Schindler

 አርያም ተክሌ/ክሪስቲን ክኒፕ

ሂሩት መለሰ