1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የድርቅን ተጽዕኖ ለመቋቋም የቅድመ ትንበያ ሚና

ማክሰኞ፣ የካቲት 15 2014

በአፍሪቃው ቀንድ አካባቢ በሚገኙ ሃገራት ለሦስት ተከታታይ ዓመታት በተስተጓጎለ የዝናብ ምክንያት በረዥም ዓመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ የተባለ ድርቅ ተከስቷል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ድርቁ በተለይ እንስሳትን እየፈጀ ነው። 13 ሚሊየን የሚሆን ሕዝብ ኬንያ፣ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውስጥ ለከፋ ረሃብ መጋለጡም ተነግሯል።

https://p.dw.com/p/47OyJ
Dürre in Somali Region
ምስል Michael Tewelde/World Food Programme/REUTERS

ጤና እና አካባቢ

የዓለም የምግብ መርሃግብር WFP ባወጣው መረጃ መሠረት ዘንድሮ በአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ ሃገራት የተከሰተው የድርቅ ኹኔታ ከ40 ዓመታት በኋላ ነው ዳግም የታየው። በድርቁ መዘዝ ሰብሎች ለፍሬ ሳይበቁ ጠፍተዋል እንስሳትም ክፉኛ ተጎድተዋል። ድርቁን ለአየር ጠባይ መለዋወጥ መንስኤ ከሆኑት ኤሊኖ እና ላኒኛ ከሚባሉት ክስተቶች ጋር የሚያገናኙ እንዳሉ ሁሉ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ መገለጫ መሆኑን የሚናገሩ ጥቂት አይደሉም። የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪና የዘርፉ ባለሙያ የሆኑት አቶ ያለምሰው አደላ ምክንያቶቹ በርከት ያሉ መሆናቸውን ይናገራሉ።

ድርቅ የተከሰተባቸው አካባቢዎች እንዳሉ ሁሉ በከባድ ዝናብ እና ጎርፍ የሚቸገሩ ስፍራዎችም ጥቂት አይደሉም። በያዝነው ዓመት የአውሮጳ የክረምት ወራት ለወትሮ ይታይ ከነበረው በረዶ ይልቅ ኃይለኛ ዝናብ እየተደጋገመ የሚከሰትባቸው ሃገራት በርክተዋል። ኃይለኛ ንፋስ እና ሞገድም እንዲሁ የአየር ጠባዩ ላይ ጫና አሳድረዋል።

Somalia | Dürre
የድርቁ ተጽዕኖ በሶማሌ ክልል ምስል Messay Teklu/DW

በተቃራኒው ድርቅ በሚደጋገምባቸው ኬንያ፣ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የዝናብ እጥረት ከ1,5 ሚሊየን በላይ እንስሳትን ፈጅቷል። በአፍሪቃ ቀንድ ሃገራትም ከ80 እስከ 90 በመቶ የሚሆን የውኃ ክምችቶች እና ግድቦችን ሳይቀር አድርቋል ነው የሚባለው። ኢትዮጵያ ውስጥ ድርቅ እንደሚከሰት አስቀድሞ ማስጠንቀቂ እንደሚሰጥ ይነገራል። እንዲያም ሆኖ ድርቁ የሚያደርሰው የጉዳት መጠን ለመቀነስ አለመቻሉ ለብዙዎች ጥያቄ ሆኗል።

በዚህ ረገድ ትርጉም ያለው ሥራ ለመሥራት አቶ ያለምሰው እንደሚሉት መረጃን ወስዶ ጥቅም ላይ የማዋሉ ጉዳይ ግንባር ቀደሙ ነጥብ ነው። መረጃው ሊጠቅመው ለሚችለው ማኅበረሰብ የመድረሱ እና እራሱን ይመጣል ተብሎ ከተገመተው ችግር ተጽዕኖ ለመከላከል ሊወስድ የሚገባውን ርምጃ ለመወሰን አቅምም ሌላው ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነም አጽንኦት ሰጥተዋል።

Äthiopien | Folgen von Dürre - Totes Vieh
የድርቁ ተጽዕኖ በደቡብ ኢትዮጵያምስል Hamar Woreda Government Communication Affairs Office

የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ከሌሎች ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ጋር የሚያገናኘው የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራ ይሠራል፣ የዝግጁነት አቅም ያጠናክራል፣ ለደረሱ ችግሮች ምላሽ ይሰጣል እንዲሁም የተጎዱትን የማቋቋም ተግባር ያከናውናል። የተፈጥሮ አደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ከብሔራዊ ሚቴሬዎሎጂ ተቋም እንደሚገኝ የገለጹልን የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደበበ ዘውዴ ወትሮ በየ10 ዓመቱ ይከሰት የነበረው ድርቅ አሁን በየዓመቱ መደጋገሙን ይናገራሉ። 

Äthiopien | Vereilung von Hilfsgütern
ምስል Mulugeta Ayene/AP/picture alliance

በክልሎች ደረጃ ሳይቀር የመረጃ ለውውጡ ከስልክ ያለፈ ሊሆን ይገባል የሚሉት አቶ ደበበ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ ላይ ተመርኩዞ የሚሠራው፤ ችግር ከተፈጠረ በኋላ ለምላሹ የሚያስፈልገውን ወጪ ጭምር እንደሚቀንስም ነው ያመለከቱት። አቶ ያለምሰውም በበኩላቸው የአየር ንብረት ለውጡ በመላው ዓለም ያስከተለው የክስተት መለዋወጥ ቀጣይ መሆኑን አመላካች ነገሮች በመኖራቸው በዘላቂነት ከለውጡ ጋር ተላምዶ ለመኖር አስቀድሞ የማኅበረሰቡን የአኗኗር ሁኔታ በመለወጥ ተጽዕኖውን ለመቋቋም ሊረዳ እንደሚችል  ሊታሰብበት ይገባል የሚለውን ሃሳብ ይጋራሉ። ባለሙያዎቹ ድርቅ መከሰቱ እንደሚደጋገም እየታየ በመሆኑ ያንተቋቁሞ ሕይወትን ለመግፋት ዘላቂ የሆነ መፍትሄ በጋራ በመፈለግ ተግባራዊ ለማድረግ ከዚህ የተሻለ ጊዜ እንደሌለም በድጋሚ አሳስበዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ