1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ኢትዮጵያው ድርቅ እና የመቋጫው ተስፋ

ማክሰኞ፣ የካቲት 14 2015

በደቡብ ኢትዮጵያ በተለያዩ አከባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን እና ሶማሌ ክልል ደቡባዊ ክፍሎች የከፋው ድቅር አሁንም መቋጫ አላገኘም፡፡ በነዚህ አከባቢዎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አርብቶ አደሮች ለድጋፍ እጃቸውን ያዘረጋው ድርቁ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ የቀንድ እና የጋማ ከብቶችንም ጭምር ገድሏል አስከፊነቱም ቀጥሏል፡፡

https://p.dw.com/p/4NniZ
Äthiopien | Dürre in Borena
ምስል Firaol Wako/PHD

በድርቁ ምክንያት ሰው የካፋ ችግር ውስጥ ነው ያለው

በደቡብ ኢትዮጵያ በተለያዩ አከባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን እና ሶማሌ ክልል ደቡባዊ ክፍሎች የከፋው ድቅር አሁንም መቋጫ አላገኘም፡፡ በነዚህ አከባቢዎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አርብቶ አደሮች ለድጋፍ እጃቸውን ያዘረጋው ድርቁ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ የቀንድ እና የጋማ ከብቶችንም ጭምር ገድሏል አስከፊነቱም ቀጥሏል፡፡

በተለይም በቦረና በርካታ ከብቶችን በማርባት ለሌሎች ይተርፉ የነበሩት አርብቶ አደሮች አሁን ለድጋፍ ፍለጋ እጃቸውን ሰጥተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሜትሮሎጂ እንደሚለው ግን ለአምስት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች በድርቅ የቀጠሉት የደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢዎች እየመጣ ባለው የዘንድሮ የበልግ ወቅት ለመደበኛ የቀረበ ዝናብ በማግኘት ድርቁ መቋጫ ሊያገኝ ይችላል፡፡

Südostäthiopien | Dürre in Borena
በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን እና ሶማሌ ክልል ደቡባዊ ክፍሎች የከፋው ድቅርምስል Seyoum Getu/DW

ማሊቻ ሞሌ ነዋሪነታቸው በቦረና ዞን ተልተሌ ወረዳ ነው፡፡ በዚህ አከባቢ የሃብትም የኑሮም መገለጫ የሆነው በርካታ ከብቶችን አሰማርቶ መዋል የሳቃቸው ምንጭ የደስታቸውም ጥግ ቢሆንም አሁን ያ ቀርቶ ታሪክ ሆነ ይላሉ፡፡ ምክኒያቱ ደግሞ ከተቋረጠ ወደ አምስተኛ ዙር የዝናብ ወራት እየሄደ ያለው የከፋው ድርቅ አሁንም ድረስ አለማቧራቱ ነው፡፡“ድሮ ባለን መሬት የሆነ ነገር ዘርተን ቢያንስ ለቀለባችን አናጣም ነበር፡፡ አሁን የሚታረስ የለም፡፡ መሬቱ ደርቋል እህል አያበቅልም፡፡ ከከብቶቻችን ቀረን ምንለው የለም፡፡ አሁን ተስፋ ቆርጠን የችግር የመጨረሻ ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ ካሉኝ የበተሰብ አባላት ያልተራበ ማንም የለም፡፡ እንደውም ሶስቱ የቤተሰቦቼ አባላት በዚሁ ተማረው እግራቸው ወዳመራቸው ሄደዋል፡፡ አሁን ሰው በርሃብ ወደ መሞቱ ነው፡፡ አሁን እዚሁ ጎረቤተ ርሃብ በሚመስል መልኩ ሰው ሞቶ እዛ እያስተዛዘን ነው” ሲሉም ድርቁ እያደረሰባቸው ያለውን የማይገፋ አደጋ በሃዘኔታ ያብራራሉ፡፡

አርብቶ አደር ማሊቻን ጨምሮ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የቦረና ነዋሪዎቹ በተራዘመው ድርቅ አሁን አቅማቸው ተንኩታኩቷል፡፡ ዴንጌ ዋሪዎም በዚሁ ወረዳ ነዋሪ ሲሆኑ አሁንስ ተስፋችን ጨልሞ ሰማይ ብናይ ምንም ጠብ ያለ ነገር አጥተናል ከሚሉ ናቸው፡፡

“ታውቃለህ በድርቁ ሰው የካፋ ችግር ውስጥ ነው ያለው፡፡ ያላቸው ከብቶች በግ እና ፍየል እንኳ ሳይቀር አልቀዋል፡፡ ጠብ ያለ ዝናብ ባለመኖሩ የሚወጣ እህል የለም፡፡ የሚሸጥ ከብት በሙሉ በድርቁ አልቀዋል፡፡ አሁን ሰው በችግሩ በህይወት እስከማለፍ ደርሷል፡፡ የሚቀመስ በመጥፋቱ በዚሁ ዓመት ብቻ በዚህች ቀበሌያችን አራት ሰው የሚደርስ ተጎሳቅለው አልፈዋል፡፡ አሁን የሞቱት መጀመሪያ ሰውነታቸው ያብጣል፡፡ ከዚያን ምንም አይነት ምግብ መውሰድ ተስኖያቸው ተጎድተው ይሞታሉ” ሲሉ አስቸጋሪ ያሉት ማህበረሰቡ ያለበትን ችግር አብራርተዋል፡፡

ላለፉት አምስት የዝናብ ወራት ቦረና ምንም አይነት ዝናብ እንዳላገኘ የዞኑ እንስሳት ሃብት መምሪያ ኃላፊ ዶ/ር ቃሲም ጉዮ ከዚህ በፊት ለዶይቼ ቬለ በሰጡት ቃለመጠይቅ በከፋ ሁኔታ ቀጥሏል ባሉት ድርቅ በዞኑ ከቤት እንስሳት ብቻ 2.3 ሚሊየን ያህሉ ማለቃቸውን አስረድተዋል፡፡

የዞኑ አስተዳደርም ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንዳመለከተው ከ800 ሺህ በላይ የቦረና ህዝብ አሁን ላይ የእለት ደራሽ ምግብን ይጠባበቃል፡፡ ከቦረና በተጨማሪም ሶማሌ ክልልን ጨምሮ በደቡብ ኢትዮጵያ በተለይም ቆላማዎቹ አከባቢዎች ላይ የከፋው ድርቅ ጉዳትን አስከትሎ በርካቶችን የምግብ ዋስትና አሳጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት ግን ይህ የደቡብ ኢትዮጵያው ድርቅ ምናልባትም በዚህ ዓመት መቋጫውን ሊያገን ይችላል የሚል ተስፋን ያጫረውን ትንቢያ እየሰጠ ይገኛል፡፡ አሳምነው ተሾመ (ዶ/ር) በኢንስቲትዩቱ የሜትሮሎጂ ትንቢያ እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ መሪ ስራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡ ከየካቲት እስከ ግንቦት ወራት የሚያጠቃልለው የዘንድሮ የበልግ ወቅት ምንም እንኳ ዘግየት ብልም ለደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢዎች በቂ ዝናብን ይዞ ይመጣል ሲሉም ይገልጻሉ፡፡ “ለደቡብ ኢትዮጵያ አብዛኛው አከባቢዎች የበልግ ወራት ዋነኛ የዝናብ ማግኛቸው ወቅት ነው፡፡ በዓመት ከ60 በመቶ በላይ ዝናብ የሚገኙም በዚሁ ወቅት ነው፡፡”

Äthiopien | Dürre in Borena
በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን እና ሶማሌ ክልል ደቡባዊ ክፍሎች የከፋው ድቅርምስል Firaol Wako/PHD

እንደ የሜትሮሎጂ ትንቢያ ባለሙያው ዶ/ር ተሾመ ማብራሪያ፤ ዓለማቀፋዊና አከባቢዊ የአየር ሁኔታዎችን ከግንዛቤ በማስገባት ተዘጋጀ ባሉት የበልግ ወራት የአየር ትንቢያ፤ ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ ዝናብ በድርቅ በተመቱቱ የደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢዎች ላይ ይኖራል፡፡ “አሁን ላይ የመካከለኛ የፓሲፊክ ውቅያኖስ መካከለኛ አከባቢዎች በላሊና ክስተት ውስጥ መሆኑ ቅዝቃዜ እንዲኖረው ያደርገዋል፡፡ የባህሩ ሙቀት ግን በሂደት ወደ መደበኛ ሁኔታ ይሄዳል፡፡ የህንድ ውቅያኖስም በተመሳሳይ ከቅዝቃዜ ወደ መደበኛ የሙቀት ደረጃ መሄዱ ከግንዛቤ ሲገባ አዎንታዊ የዝናብ መጠን ነው የሚጠበቀው፡፡ እነዚህ ክስተቶች በተለይም በበልግ ወቅት ዝናብ በሚያገኙ የአገራችን አከባቢዎች ብዘገይ ነው እንጂ መደበኛ እና ለመደበኛ የተጠጋ ዝናብ እንዲያገኙ ያስችላል፡፡”

እንደ ሜትሮሎጂ ትንቢያ ባለሙያው ከደቡብ ኢትዮጵያ በተጨማሪ በዘንድሮው የበልግ ወቅት በሰሜን እና ምዕራብ ኢትዮጵያም መደበኛ እና ከመደበኛም የላቀ ዝናብ ይጠበቃል።

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ