1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ«ደህንነትና ፍትሕ ለትግራይ» ማኅበር ጥሪ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 2 2015

ተቀማጭነቱን ዩናይትድስቴትስ ያደረገው፣«ደህንነትና ፍትሕ ለትግራይ» በቅርቡ በትግራይ ተፈጸመ ባለው የጦር ወንጀል፣በኤርትራ የጦር አውሮፕላኖች አዲ ዳዕሮ በተባለ ቦታ፣ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል ብሏል። የባይደን አስተዳደር እነዚህን የሠላማዊ ሰዎች ግድያ እንዲያወገዝ ጠይቋል።

https://p.dw.com/p/4I653
የ«ደኅንነትና ፍትህ ለትግራይ»ማኅበር አርማ
የ«ደኅንነትና ፍትህ ለትግራይ»ማኅበር አርማ

የ«ደህንነትና ፍትሕ ለትግራይ» ማኅበር ጥሪ

በትግራዩ ጦርነት ኤርትራ አላት ያለውን ተሳትፎ ለማስቆም፣ የፕሬዚዳንት ባይደን አስተዳደር ፈጣን እርምጃ እንዲወስድ «ደህንነትና ፍትሕ ለትግራይ» የተሰኘው በአሜሪካ የትግራይ ተወላጆች ማኀበር ጥሪ አቀረበ። ድርጅቱ፣ለዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በላከው ግልጽ ደብዳቤ፣የአሜሪካ አስተዳደር ፣በሰላማዊ ሰዎች ላይ ይፈጸማል ያለውን ግድያ እንዲያወግዝና የኤርትራን ተሳትፎ ለማስቆም ጠንከር ያለ ፈጣን እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል። ዝርዝሩን የአትላንታው ዘጋቢያችን ታሪኩ ኃይሉ ልኮልናል።
ተቀማጭነቱን ዩናይትድስቴትስ ያደረገው፣«ደህንነትና ፍትሕ ለትግራይ»፣በትግራይ ይካሄዳል ባለው የዘር ማጥፋት ዘመቻ፣ኢትዮጵያና ኤርትራ ከበባ ፈጽመው በአየርና በምድር ጥቃት፣ እንዲሁም በረሃብ ሰባት ሚሊዮን ነዋሪዎች ላይ ግድያ እየተፈጸመ ይገኛል ብሏል። ድርጅቱ፣በቅርቡ ተፈጸመ ባለው የጦር ወንጀል፣በኤርትራ የጦር አውሮፕላኖች አዲ ዳዕሮ በተባለ ቦታ፣ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል ብሏል። ዓለም ለእነዚህና ድርጅቱ በደብዳቤው ላይ ለዘረዘራቸው ጥቃቶች ዝምታን መርጧል በማለት የወቀሰ ሲሆን፣የባይደን አስተዳደር እነዚህን የሠላማዊ ሰዎች ግድያ እንዲያወገዝ ጠይቋል።
የ«ደህንነትና ፍትሕ ለትግራይ»የድርጅት ጉዳዮች ኃላፊ አቶ የማነ ሃለፎም ለዶይቸ ቨለ እንደተናገሩት፣ለፕሬዚዳንት ባይደን የተላከው ደብዳቤ ዋነኛ መልዕክት፣በትግራይ በሚካሄደው ጥቃት ኤርትራ ታካሂደዋለች ያሉትን ተሣትፎ የተመለከተ ነው።የትግራይ ተወላጆች ጦርነት ይቁምልን ድምጽ በአዲስ አበባ

የባይደን አስተዳደር ተገቢውን እርምጃ ካልወሰደ ግን፣ድርጅታቸው በኢትዮጵያና በአካባቢው ከፍተኛ ጉዳት ይከትላል የሚል ስጋት እንዳለው አቶ የማነ አመልክተዋል።

ስለጉዳዩ ዶይቸ ቨለ ያነጋገራቸውና በኢትዮጵያ ጉዳዮች በርካታ መጽሐፍት የጻፉት በዳይተን ስቴት ዩኒቨርሲቲ መምህር ፕሮፌሰር መሣይ ከበደ በበኩላቸው፣የድርጅቱ ደብዳቤ የውጭ ኃይል ጣልቃ እንዲገባ በመሻት የተጻፈ መሆኑን ጠቅሰው፣ይህንን ማንም ኢትዮጵያዊ እንደማይቀበለው ገልጸዋል።በደብዳቤው የኤርትራ ስም መጠቀሱ፣ሆነ ተብሎ አሜሪካኖቹን ለማነሳሳት እነደሆነም ፕሮፌሰር መሣይ ጠቅሰዋል።
የኤርትራ መንግስት፣በሰሜን ኢትዮጵያ በቀጠለው ጦርነት እየተሣተፈ ነው በማለት ለሚቀርብበት ውንጀላ እስካሁን በይፋ የሰጠው ምላሽ የለም።
ታሪኩ ኃይሉ
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ