የዕጣን ደን እና ምርት ይዞታ
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 8 2017የልዩ ልዩ የተፈጥሮ ጸጋዎች መገኛ የሆነው አብዛኛው የምዕራብ ኢትየጵያ ክፍል የዕለት ተዕለት እንቀስቃሴን በሚያውኩ ግጭቶች እና የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት የውጪ ሀገር ምንዛሪ የሚያስገኙ ማዕድናት በሥራ ላይ ሳይወሉ መቆየታቸውን በዘርፍ የተሰማሩ ወጣቶች ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ የዕጣን ምርት ከሚገኝባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ የሆነው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሺህዎች የሚቆጠር ኩንታል ዕጣን ከክልሉ ለመካከለኛ ገበያ በመቅረብ ላይ ይገኛል። በአሁኑ ውቅት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የዕጣን ምርት ከወርቅ ምርት ባልተናነሰ መልኩ በዘርፉ በርካታ ወጣቶችና ባለሀብቶች አሶሳ ዞን ኩርሙክ እና ሸርቆሌ የተባሉ ወረዳዎች፤ ከመተከል ዞን ደግሞ በጉባ ወረዳ ውስጥ ተሰማርተው እንደሚገኙ የክልሉ አካባቢ ጥበቃ ቢሮ መረጃ ያስረዳል።
በ2011 እና 2012 ዓ.ም በክልሉ ይስተዋል በነበረው ግጭት ምክንያት ተቀዛቅዞ የነበረው የዕጣን ምርት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን ኩርሙክ እና ሸርቆሌ የተባሉ ወረዳዎችም ከ2014 ዓ.ም ወዲህ የምርቱ መጠን መጨመሩን በዘርፍ የተሳተፉ ያነጋርናቸው ሁለት ወጣቶች ተናግረዋል።
አንድ ኩንታል ዕጣን በ30ሺህ ብር ወደ መካከለኛ ገበያ ይላካል
በአሶሳ ዞን ኩርሙክ በተባለው ወረዳም በዘርፉ ከተሰማሩት አንዱ የሆኑት አቶ ምትኩ ተመስገን ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ዘርፉ የሚቀላቀሉ ሰዎች ቁጥር መበራከቱን እና ምርቱም በተመሳሳይ በየጊዜው መጨመሩን አመልክተዋል። እንደ አቶ ምትኩ ገለጻ በወረዳው በሚገኘው የዕጣን ምርት እሳቸው ጨምሮ በሚሰሩበት አንድ ማኅበር 57 ሰዎችን የሚደርሱ ግለሰቦች የተሰማሩ ሲሆን ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በዘርፍ መሰማራታቸውን አስታውቋል። በማኅበራቸው ብቻ በ2015 ዓ.ም ከ300 በላይ ኩንታል የዕጣን ምርት ወደ ማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን በመግለጽ በ2016 ዓ.ም ደግሞ የዕጣን ምርታቸው በእጥፍ መጨሩን አብራርተዋል።
በክልሉ ሸርቆሌ በተባለ ወረዳ «ጊዘን» በሚባል ሱዳን ድምር አካባቢ በዕጣን ምርት ላይ የተሰማሩት አቶ ደረጀ አበበ በዚህ ስፍራ ደግሞ ከሁሉም የምርት ቦታዎች የተሻለ ዕጣን ባለፉት ሁለት ዓመታት ዕጣን ምርት ለገበያ መቅረቡን ተናግረዋል። በአንድ ማኅበር ከ1300 ኩንታል በ2016 ዓ.ም መሰብሰቡንና ለገበያ መቅረቡን አንስተው ለገበያ ለማድረስ በሚደረገው በሂደት ላይ ግን የሚከፈለው የግብር መጠን ከፍተኛ እንደሆነም ገልጸዋል።
ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችም በሚገኙባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለእርሻ ሲባል የዕጣን ዛፎች መቆረጥ በምርቱ ላይ ተጽእኖ ማሳደሩም ይነገራል። በየወረዳዎቹ የዕጣን ምርት ለማሳደግ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ትኩረት አንዳልተሰጠው በዘርፉ የተሰማሩ ሁለቱ ወጣቶች አስታውቀዋል። አቶ ምትኩን ጨምሮ በአካባቢው በዕጣን ምርት ላይ ተሰማርተው የሚገኙት ማሕበራት በዕጣን ምርት ላይ ለረጅም ዓመት የተሰማሩ እና ልምድ ያላቸው ባለሙያዎችን ለማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ተናግረዋል። የዕጣን ምርት ላይ በዘልማድ የሚሠሩ ሥራዎችየዕጣን ዛፍ ለማድረቅ አጋጣሚያዎችን የሚፈጥር መሆኑ በጥንቃቄ መሠራት እንዳለበት ጠቁመው በዘርፍ ያለውን ሥራ ጫናዎችም አብራርተዋል።
በምርቱ ላይ የተደቀኑ ስጋቶች
በእጣን ምርት ላይ የተሰማሩ አቶ ምትኩም ሆነ አቶ ደረጃ በተሰማሩት አካባቢ በእጣን ምርት ላይ ሊደርስ ይችላል ያሉትን ስጋትም ገልጸዋል፡፡ በተለይም የእርሻ መሬት በሚገኝባቸው እንደ ጉባ እና ሴዳል የተባሉ አካባቢዎች የእጣን ዛፎች በተደጋጋሚ ተቆርጦ ማየታቸውን አንሰተዋል፡፡ እነዚህ የእጣን ዛፎች የተፈጥሮ ዛፎች እንደመሆናቸው መጠን የእጣን ዛፎች እዳይጠፉ ልዩ የአካባቢ ጥበቃ እና ተጨማሪ ዛፎች መተከተል አለባቸው በማለት አብራርተዋል። ተጨማሪ የዕጣን ዛፍ በየጊዜው አለመተከሉ ከጊዜ በኋላ በዕጣን ምርት ላይ ስጋት ስለሚፈጠር ትኩረት ቢሰጠው የሚል ሀሳብም ይነሳል።
ረጅም ዓመት በዕጣን ዘርፍ የተሰማሩ እና ልማድ ያላቸውን ባለሙያዎች በሥራው ለማሳተፍ በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች የመጓጓዣ አገልግሎት ችግሮችና እና ከየአካባቢው ሠራተኞችን በብዛት ሲጓጓዙ ከወቅታዊ የክልሎቹ የሰላም ሁኔታ ጋር በማገናኘት ለመቀሳቀስ ፈቃድ አለማግኘታቸው በሥራዎቻቸው ላይ ተጽእኖ እያሳደረ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
የዕጣን ዛፍ እንዳይቆረጥ ክትትል ማድረግ እንጀምራለን
የዕጣን ሀብትን ጥበቃን አስመልክቶ መረጃዎችን የጠየቅናቸው የክልሉ የአካባቢ ጥበቃ ኃላፊ አቶ ሉቁማን አብዱልቃድር በጉዳዮ ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል። የዕጣን ምርት በክልሉ ከዚህ ቀደም በስፋት በኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በተባለ የልማት ድርጅት ሲሰራ መቆየቱን የተናገሩት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአከባቢ ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሉቁማን አብዱል ቃድር ለዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶት ወደ ምርት የተገባውም በቅርቡ መሆኑን አብራርተዋል። በክልሉ የዕጣን ዛፍ በሚገኝባቸው እንደ ኩርሙክና ሽርቆሌ የተባሉ ወረዳዎች አካባቢው በማዕድን ሥራ የሚታወቅና እንደሌሎች አካባቢዎች የእርሻ ኢንቨስትመንት ባለመኖሩ የዕጣን ዛፎች ከሌሎች ቦታዎች የተሻለ እንክብካቤ እንዳላቸው ተናግረዋል።
መተከል ዞን ጉባ ወረዳ እና በካማሺ ዞን ሴዳል በተባሉ ወረዳዎች ለእርሻ ኢነቨስትመንትም ሲባል የዕጣን ዛፎች ይቆረጣሉ መባሉን አስመልክቶ ተቋማቸውን የደረሰው መረጃ አለመኖሩን በመግለጽ ጉዳዩን ቢሯቸውን በቀጣይ እንደሚከታተል ገልጸዋል። በዘርፍ ፍቃድ የሚወስዱ በማሕበር ሆነ በግል ባለሀብቶች የተሰማሩ ግለሰቦች፣ በሚያመርቱባቸው አካባቢዎች ዛፉን በዓመት አንድ ጊዜ እንዲተክሉ የተባሉ ቢሆን በሁለት ዓመታት ውስጥ በዘርፍ ከተማሩት መካከል በአንድ ወረዎች ብቻ የተወሰነ የዕጣን ዛፍ መተከሉን አክለዋል።
በጸጥታ ችግር ወደ ምርት ሳይገቡ የቆየት እንደ ጉባ ወረዳ ያሉት አካባቢዎች በዚህ 2017 ዓ.ም ሥራ የጀመሩ ሲሆን ሸርቆሌ ከተባባለ ወረዳ ቀጥሎ ከፍተኛ የዕጣን ምርት የሚገኝበት አካባቢ ነው።
በምዕራብ ኢትዮጵያ ወለጋ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እምነበረድ፣ ዕጣን፣ ድንጋይ ከሴልና ከፍተኛ የወርቅ ክምችት የሚገኝባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡ በ2014 ዓ.ም ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ከፍተኛ የተባለው 23 ኩንታል ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ መግባቱም የማዕድን ምርት በተለያዩ ዘርፍ ማደጉን ያመለክታል።
ነጋሳ ደሳለኝ
ሸዋዬ ለገሠ