1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓርብ ሰኔ 7 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የዓለም ዜና

ዓርብ፣ ሰኔ 7 2016

አርዕስተ ዜና፦ ሽንሌ፥ ኢሰመኮ በአፋር እና ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት ማገርሸቱ አሳስቦኛል አለ፤ የሩስያ ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ከዩክሬን ጋ ለመደራደር ሀገራቸው በቁጥጥሯ ስር ካዋለቻቸው ግዛቶች የዩክሬን ጦር ሙሉ ለሙሉ መውጣትን እንደ ቅድመ ሁኔታ አስቀመጡ፤ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) ዋና ጸሐፊ ዬንስ ስቶልተንበርግ በዩክሬን ፍትሐዊ እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ሩስያ የመስፋፋት ፍላጎቷን ልትገታ ይገባል አሉ፤ የአውሮጳ ሃገራት እግር ኳስ ዋንጫ የመክፈቻ ጨዋታ ዛሬ ማታ ሙይንሽን ውስጥ የዘንድሮ አዘጋጇ ጀርመን ስኮትላንድን ትገጥማለች

https://p.dw.com/p/4h3de

አርዕስተ ዜና

*ሽንሌ፥ ኢሰመኮ በአፋር እና ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት ማገርሸቱ አሳስቦኛል አለ

*የሩስያ ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ከዩክሬን ጋ ለመደራደር ሀገራቸው በቁጥጥሯ ስር ካዋለቻቸው ግዛቶች የዩክሬን ጦር ሙሉ ለሙሉ መውጣትን እንደ ቅድመ ሁኔታ አስቀመጡ ።

*የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) ዋና ጸሐፊ ዬንስ ስቶልተንበርግ በዩክሬን ፍትሐዊ እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ሩስያ የመስፋፋት ፍላጎቷን ልትገታ ይገባል አሉ ።  የዩክሬን ጦርነት አብቅቶ ሰላም እንዲሰፍን በሚል በሩስያ ፕሬዚደንት ዛሬ የቀረበውን ሐሳብም፦ «የዳግም ወረራ ዕቅድ» ሲሉ ኮንነውታል ።

*የአውሮጳ ሃገራት እግር ኳስ ዋንጫ የመክፈቻ ጨዋታ ዛሬ ማታ ሙይንሽን ውስጥ የዘንድሮ አዘጋጇ ጀርመን ስኮትላንድን ትገጥማለች ።  ባለፉት ሦስት ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ በሁለቱ ከምድብ ማጣሪያ ማለፍ ያልቻለችው ጀርመን የ2006ቱን የዓለም ዋንጫ የደጋፊዎች ደማቅ ድባብ ለመመለስ ዛሬ ብዙ ይጠበቅባታል ።

ዜናው በዝርዝር

ሽንሌ፥ ኢሰመኮ በአፋር እና ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት ማገርሸቱ አሳስቦኛል አለ

በቅርቡ በሚያዚያ ወር የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት በመጣስ በሶማሊ ክልል ሽንሌ ዞን እና አፋር ክልልል አዋሳኝ ያገረሸው ግጭት እንዳሳሰበው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)ዐስታወቀ ። ግጭቱ ለሰላማዊ ሰዎች ግድያ እና መፈናቀል ምክንያት ሆኗል ብሏል ኮሚሽኑ ። በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የጅግጅጋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር ሰኢድ ደመቀ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፦ የአሁኑ ግጭት የተጀመረው ከግንቦት 29 ቀን 2016 ዓ.ም 2024 ወዲህ ነው ።

«በዚያ ግጭት የተወሰኑ ሰዎች ሞት፤ መፈናቀል እና የአካል ጉዳት፤ የንብረት መውደም እንደደረሰ ነው ያለው መረጃ በእኛ በኩል ግጭቱ እንዳገረሸ ። በትክልል ስንት ሰው ሞተ፤ ቆሰለ የሚለውን ገና በምርመራ የምናጣራው ሆኖ በአሁኑ ወቅት ግን ጠቅለል ባለ መልኩ የሰው መፈናቀል፤ ሞት እና ጉዳት እንዳለ ነው ።»

ኢሰመኮ ከሁለቱ ክልሎች የመንግስት አስተዳዳሪዎች ተረዳሁት ባለው መሠረት፦ በሁለቱም ክልሎች በኩል የሰላማዊ ሰዎች ግድያ እና መፈናቀሎች ተፈጽሟል ። በቅርቡ በኢትዮጵያ ፌዴራል እስልምና ጉዳች ከፍተኛ ምክር ቤት ለተገኘው አዎንታዊ የሰላም ማስፈን ሂደት ሁለቱ ክልሎች ያሰጡትን አዎንታዊ ምላሽ ያደነቀው ኢሰመኮ፤ የተጀመረው የሰላም ጥረት እንዲቀጥል የፌዴራልም ሆነ የሁለቱ ክልሎች መንግስታት የቀጠለውን ግጭት እንዲያስቆሙት ጥሪውን አቅርቧልም ። የኢትዮጵ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ የፌዴራል መንግስት አስቸኳይ የግጭት ማስቆም ጥረት እንዲያስደርግ ጥሪ ቀቅርበዋል ።  የሁለቱ ክልሎች አስተዳዳሪዎች በቀጣይ ሕዝበ ሙስሊሙ ከሚያከብረው የኢድ አል-አደሃ በዓል አስቀድሞ ሰላም እንዲሰፍን ጥረት እንዲያደርጉም ጠይቀዋል ። ዜናውን የላከልን የአዲስ አበባ ወኪላችን ሥዩም ጌቱ ነው ።

ጄኔቫ፥ ስዊዘርላንድ ጥገኝነት ጥያቄያቸው ውድቅ የሆኑ የኤርትራ ስደተኞችን

የስዊዘርላንድ ምክር ቤት ጥገኝበት ጥያቄያቸው ውድቅ የሆኑ የኤርትራ ስደተኞችን ከሀገር ለማባረር የቀረበውን ዕቅድ እንደሚደግፍ ዐስታወቀ ። ምክር ቤቱ በዚህ ሳምንት መግቢያ ላይ ባሳለፈው ውሳኔ፦ ጥገኝነት ያላገኙ የኤርትራ ስደተኞች ወደ ሦስተኛ ሃገር ይዛወራሉ ብሏል ። ሦስተኛው ሀገር ግን የት እንደሆነ አልተጠቀሰም ። በስዊዘርላንድ ምክር ቤት የግራ እና የመሀል ፓርቲዎች እቅዱን ተቃውመዋል ። ዕቅዱ ስኬታማ የመሆን ዕድሉ አናሳ ከመሆኑም በላይ እጅግ ወጪ ያስወጣል ብለዋል ። የስዊዘርላንድ መንግሥት በበኩሉ የጥገንነት ጥያቄያቸው ውድቅ ተደርጎ ወደ ሦስተኛ ሀገር የሚዛወሩ ስደተኞችን የሦስተኛ ሀገሩ ውስጥ የሚገኘው የኤርትራ ተወካይ ሠነድ ላይሰጣቸው ይችላል ሲሉም ስጋታቸውን ገልጠዋል ። 

ሞስኮው፥ፑቲን ከዩክሬን ጋ ለመደራደር ቅድመ ዝግጅት አስቀመጡ

የሩስያ ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ከዩክሬን ጋ ለመደራደር ሀገራቸው በቁጥጥሯ ስር ካዋለቻቸው ግዛቶች የዩክሬን ጦር ሙሉ ለሙሉ መውጣትን እንደ ቅድመ ሁኔታ አስቀመጡ ። ፕሬዚደንቱ ይህን የተናገሩት ስዊትዘርላንድ ውስጥ ቅዳሜ ከሚካሄደው የዩክሬን ሰላም ጉባኤ ቀደም ብለው ዛሬ ሞስኮ ከተማ የሚገኘው የሩስያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትርን በጎበኙበት ወቅት ነው ።

«ዩክሬን ይህን ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን እንደተናገረች ፤ በእርግጥም ጦሯን ማስወጣት እንደጀመረች እና የኔቶ አባል የመሆን ዕቅዷን በይፋ እንዳወገዘች በዚያች ቅጽበት የተኩስ አቁም እንዲደረግ እና ንግግር እንዲጀምር ትእዛዝ እናስተላልፋለን።»

ፕሬዚደንቱ ዛሬ ይህን ባሉበት ወቅት በአብላጫ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) አባል ሃገራት የተዋቀረው በኤኮኖሚ የበለጸጉት የቡድን 7 አባል ሃገራት መሪዎች ስብሰባ ጣሊያን ውስጥ እየተካሄደ ባለበት ነው ። የዶኒዬትስክ፤ ሉሃንስክ፤ ዛፖሪዢያ እና ኬህርሶን ግዛቶች ጉዳይም በዩክሬን በኩል ከእንግዲህ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም ብለዋል ፕሬዚደንት ፑቲን ። የፕሬዚደንቱን ቅድመ ሁኔታ ዩክሬን፤ ናቶ እና ዩናይትድ ስቴትስ ውድቅ አድርገዋል ።  

ብራስልስ፥ ኔቶ የሩስያን የሰላም ሐሳብ «የዳግም ወረራ ዕቅድ» ሲል ኮነነ

የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) ዋና ጸሐፊ ዬንስ ስቶልተንበርግ በዩክሬን ፍትሐዊ እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ሩስያ የመስፋፋት ፍላጎቷን ልትገታ ይገባል አሉ ።  ዋና ጸሐፊው ይህን ያሉት የኔቶ አባል ሃገራት የመከላከያ ሚንስትሮች ለሁለት ቀናት ያደረጉትን ጉባኤ ዛሬ ቤልጂየም ብራስልስ ውስጥ ባጠናቀቁበት ወቅት ነው ።  የዩክሬን ጦርነት አብቅቶ ሰላም እንዲሰፍን በሚል በሩስያ ፕሬዚደንት ዛሬ የቀረበውን ሐሳብም፦ «የዳግም ወረራ ዕቅድ» ሲሉ ኮንነውታል ።

«ይህ እቅድ በቀና መንፈስ የመነጨ አይደለም ። ይህ በእውነቱ እንደውም ሩስያ የጦርነት ጨዋታዋን ይበልጥ ለማሳካት ያቀደችበት ነው ማለት ይቻላል ። ሩስያ አሁን መቆጣጠር ከቻለችው በላይም ሌሎች ግዛቶችን ዩክሬን ታስረክባለች ብላ ነው የምትጠብቀው ። ስለዚህ ይህ የሰላም ዕቅድ አይደለም ።  ይህ ይበልጥ የሞገደኝነት እና ይበልጥ የወረራ ዕቅድ ነው ።»

ኔቶ በዩክሬን ጉዳይ ከአንድ ወር ግድም በኋላ ዳግም ለመምከር ዋሽንግተን ውስጥ ቀጠሮ ይዟል ። በኤኮኖሚ የበለጸጉት የቡድን 7 አባል ሃገራት በበኩላቸው፦ አውሮጳ ውስጥ  በእገዳ ከተያዘው የሩስያ መአከላዊ ባንክ ሐብት 50 ቢሊዮን ዶላር ብርድ ለዩክሬን ለማበደር መስማማታቸውን ዐሳውቀዋል ። ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን የቡድን 7 አባላት ድርጊትን ምንም አይነት ስያሜ ይሰጠው « ስርቆት ስርቆት ነው» ሲሉ ኮንነዋል ። ከ260 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሩስያ ሐብት ከዩክሬን ጦርነት በኋላ እንዳይንቀሳቀስ በምዕራባውያን መታገዱ ይታወቃል ።

ሙይንሽን፥ በአውሮጳ እግር ኳስ መክፈቻ ጀርመን ዛሬ ስኮትላንድን ትገጥማለች

ዛሬ ማታ ሙይንሽን ውስጥ በሚጀምረው የዘንድሮ የአውሮጳ ሃገራት እግር ኳስ ዋንጫ የመክፈቻ ጨዋታ አዘጋጇ ጀርመን ስኮትላንድን ማሸነፏ «እጅግ ወሳኝ ነው» ተባለ ። የቀድሞው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተጨዋች እና የዩሮ 2024 ውድድር ኃላፊ ፊሊፕ ላም የጀርመን ማሸነፍ ደጋፊዎችን ለማነቃቃት እጅግ አስፈላጊ ነው ብሏል ። ጀርመን ከዚህ ቀደም በሦስት ዋና ዋና ዓለም አቀፍ ውድድሮች መክፈቻ ጨዋታዎች ላይ አንዱንም አለማሸነፏንም አስታውሷል ።  ጀርመን በ2018 እና በ2022 የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ እንዲሁም በዩሮ 2020 የመክፈቻ ፉክክሮች ላይ ሽንፈት ገጥሟታል ። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ዩሊያን ናግልስማን በዛሬው ጨዋታ የተቻላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ትናንት ማምሻውን ተናግረዋል። 

«ጨዋታው እኪጀምር ጓጉቻለሁ ። ለቡድኑ ብቻ ሳይሆን ለእኔም ጭምር የተለየ ቅጽበት ነው ። እንደሚመስለኝ ለዚህች ሀገር ልዩ አጋጣሚ ነው ። በነገው ጨዋታ የተቻለንን ለማድረግ እንሞክራለን ። ደጋፊዎችን በመላ ከተወዳዳሪ ምርጥ ቡድኖቹ መካከል አንዱ የእኛ መሆኑን ለማሳመን እንጥራለን ። እናም እስከ መጨረሻው የተቻለንን ለማድረግ እንጥራለን ።»

ጀርመን ከ18 ዓመት ወዲህ የወንዶች እግር ኳስ ዓለም አቀፍ ውድድር ስታዘጋጅ ይህ የመጀመሪያዋ ነው ። በዓለም ዋንጫ ወቅት የነበረውን የስፖርት ደጋፊዎች አስደማሚ ድጋፍ መልሶ ለማምጣት ጀርመን በቀጣይ የምታደርጋቸውን ጨዋታዎች የግድ ማሸነፍ ይጠበቅባታል ። የዛሬ ምሽቱን ውድድር ለመከታተል 150,000 ግድም የስኮትላንድ ደጋፊዎች ወደ ሙይንሽን አቅንተዋል ። የአሸባሪ ጥቃት እንዳይከሰት በሚልም 20 ሺህ ግድም ፖሊሶች ለጥበቃ መሰማራታቸው ተዘግቧል ። ጀርመን በምትገኝበት ምድብ «ሀ» ሐንጋሪ እና ስዊትዘርላንድም ይገኛሉ ። ሁለቱ ቅዳሜ በኮሎኝ ከተማ ይጋጠማሉ ። በምድብ «ለ» የሚገኙት ስፔን እና ክሮሺያም የሚጋጠሙት ነገ ነው ። የባለፈውን የአውሮጳ እግር ኳስ ዋንጫ በፍጻሜው ዌምብሌይ ውስጥ እንግሊዝን አሸንፋ የወሰደችው ጣሊያን እና አልባኒያም ቅዳሜ ይጋጠማሉ ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።