ሶማሌላንድ፤ በዚህ ሳምንት ረቡዕ ምርጫ ታካሂዳለች
ራስ ገዝዋ ሶማሌላንድ የፊታችን ረቡዕ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደምታካሂድ ተነገረ። በጎርጎረሳዉያኑ 1991 ዓ.ም ነጻነትዋን ያወጀችዉ እና በሰሜን ምዕራብ ሶማልያ ክልል ግዛት የምትገኘው ሶማሌላንድ፤ ከተቀረው የሶማልያ ክፍል እጅግ የተረጋጋና ሰላማዊ ሆና የዘለቀች መሆኑ ተዘግቧል። እራሷን ሶማሌላንድ ሪፐብሊክ ስትል የምትጠራዉ ራስ ገዝዋ የአፍሪቃ ቀንዷ ግዛት፤ የራሷ የመገበያያ ገንዘብ፤ ፓስፖርትና መከላከያ ሠራዊት ያላትም ነች። ሆኖም ሶማሌላንድ እስካሁን ከየትኛውም የዓለም ሀገር እውቅናን አላገኘችም። የራስ ገዝዋ ሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ፤ በቀይ ባህር ዳርቻ 20 ኪሎ ሜትር ላይ ለኢትዮጵያ የባሕር ኃይል እና የጦር ሠፈር በኪራይ የሚሰጥ ሥምምነት፤ ታህሳስ 22 ቀን 2016 ከኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ፤ ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ያሳሰበ በሶማልያ ቁጣ እና ንዴትን መቀስቀሱ ይታወቃል። ኢትዮጵያ ከሶማሊያ በተገነጠለችው በሶማሌላንድ የባህር ኃይል ጦር ሰፈር ለመገንባት የያዘችዉን እቅድ ሶማሊያ መቼም እንደማትቀበል በተደጋጋሚ ስትገልፅ እና መቆየትዋ ይታወቃል። የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ስምምነቱን ከተፈራረሙ በኋላ፤ ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ የአገርነት እዉቅናን ትሰጣለች ሲሉም ተናግረዉ ነበር። ከጎርጎረሳዉያኑ 2017 ጀምሮ በስልጣን ላይ የሚገኙት የ76 ዓመቱ የሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት፤ «ኩልሚዬ» የተሰኘዉ ፓርቲያቸዉ በድጋሚ ቢመረጥ ራስገዝዋ ሶማሌላንድ፣ ከኢትዮጵያ ጋር የገባችዉ ስምምነት ይሻሻላል ሲሉ ቃል ገብተዋል። የፕሬዚዳንት ቢሂ ተቀናቃኝ ሆነዉ ለምርጫዉ የቀረቡት ሁለቱ ተቃዋሚዎቻቸዉ አብዲራህማን ሞሃመድ አብዱላሂ እና ፋይሳል አሊ ዋራቤ የኢትዮጵያን እና የሶማሌላንድ ስምምነትን አልነቀፉም።
ስዊድን ፤ ትዉልደ ኤርትራዊዉ የስዊድ ዜጋ ዳዊት ይህሳቅ የስዊድንን የመብት ሽልማት አሸነፈ
በኤርትራ እስር ቤት ያለምን ፍርድ ከ 23 ዓመታት በላይ የታሰረዉ ትዉልደ ኤርትራዊ የስዊድ ዜጋ ዳዊት ኢሳቅ፤ ለሃሳብ ነጻነት ላደረገዉ ትግል ኤድልስታም የተባለዉን የስዊድንን የመብት ከፍተኛ ሽልማት አሸነፈ። በስዊድን የሚገኘዉ ኤልድልስታም ፋዉንዴሽን የተባለዉ ሸላሚ ድርጅት ዛሬ እንዳስታወቀዉ፤ ጋዜጠኛ ዳዊት ኢሳቅ « ይህን ሽልማት ያሸነፈዉ፤ ለሀሳብ ነጻነት፣ ለአመነበት ለሰብአዊ መብቶች ጥበቃ በመቆም ላበረከተው የላቀ አስተዋፅኦ እና ላሳየዉ ለየት ያለ ድፍረት" ነዉ፤ ብሏል። ትዉልደ ኤርትራዊዉ ዳዊት ኢሳቅ በጎርጎረሳዉያኑ መስከረም ወር 2001 በኤርትራ መንግሥት ባለስልጣናት ተይዘዉ እስር ቤት ከተወረወሩ፤ የኤርትራ ከፍተኛ የካቢኔ አባላት ሚኒስትሮች፣ የፓርላማ አባላትና ጋዜጠኞች እንዲሁም ሁለት ደርዘን ከሚሆኑ ኤርትራዉያን መካከል አንዱ ነዉ። አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጋዜጠኛ ዳዊት ኢሳቅ የኅሊና እስረኛ መሆኑን ገልጿል። ድምበር የለሹ የፕሪስ ነጻነት ቡድን ሪፖርተር ዊዝአውት ቦርደርስ (RSF) ጋዜጠኛ ዳዊት ኢሳቅ እና በተመሳሳይ ጊዜ የታሰሩ የሥራ ባልደረቦቹ፤ በዓለም ላይ ለረጅም ዓመታት ታስረዉ የሚገኙ ጋዜጠኞች መሆናቸዉን አስታዉቋል። የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ምሁራን «የአስመራዉ መንግሥት ጋዜጠኛ ዳዊት ኢሳቅ ን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲለቀቅ ሲሉ ለተደጋጋሚ ጊዜ ጠይቀዋል። ኤርትራ እስር ላይ ስለሚገኘዉ ጋዜጠኛ ዳዊት ኢሳቅ እስካሁን ምንም አይነት መረጃን ይፋ አላደረገችም። ዘንድሮ 60 ዓመት የሚሆነዉ ትዉልደ ኤርትራዊዉ ዳዊት ኢሳቅ ምናልባትም በህይወት ላይኖር ይችላል የሚል ስጋት እንዳለም፤ በተለያዩ ጊዜያቶች ተዘግቧል።
ፓሪስ፤ በገንዘብ እጥረት የመዘጋት እጣ የተደቀነበር የኤርትራዉያን ሬድዮ
ጨቋኝ መንግሥታት ናቸዉ ከሚባልባቸዉ ሃገሮች አንዷ በሆነችው በኤርትራ ከፓሪስ መኖርያ አፓርትመንት የሚሰራጨዉ የኤርትራዉያን የብርሃን ተስፋ የተባለዌ ኤሬና ሬድዮ የገንዘብ እጥረት እንደገጠመዉ ተነገረ። ከፓሪስ 13ኛ ክፍለ ከተማ ዉስጥ ሆኖ የሚያሰራጨዉ ራድዮ ኤሪና፤ ላለፉት 15 ዓመታት እምነት የሚጣልበት ብቸኛ ነፃ የኤርትራዉያን መረጃ ማግኛ ጣብያ መሆኑም ተመልክቷል። ይሁን እና ሬድዮ ጣብያ ኤሬና በአሁኑ ወቅት በገንዘብ እጥረት ምክንያት ስርጭቱን ለአድማጮቹ ለማድረስ አደጋ እንደተጋረጠበት የፈረንሳዩ ዜና አገልግሎት አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዛሬ ዘግቧል። በዘገባዉ መሰረት ሬድዮ ጣብያዉ በገንዘብ እጥረት ምክንያት፤ በጣብያዉ የሚሰረቱን ሰራተኞች ከስድስት ወደ ሦስት ቀንሷል። ኤሪና ሬድዮ በቀን ሁለት ሰዓታት በትግርኛ እና በአረብኛ ዝግጅቶቹን ከፓሪስ ኤርትራን ጨምሮ በዓለም ዙርያ ለሚገኙ አድማጮቹ እንደሚያደርስም ተመልክቷል።
ሳዑዲ አረቢያ፤ የአረብ ሊግ እና የሙስሊም መሪዎች የእስራኤልን ጥቃት አወገዙ
የሳዑዲ አረቢያዉ ልዑል ማሐመድ ቢን ሰልማን በጋዛ እና በሊባኖስ አፋጣኝ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠየቁ። ቢን ሳልማን ይህን ጥሪ ያቀረቡት በሳውዲ አረቢያ ሪያድ በአረብ ሊግ እና በእስልምና ትብብር ድርጅት የጋራ ጉባዔ ላይ ነው። በጉባኤዉ መክፈቻ ላይ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እስራኤል በፍልስጤም ላይ የምትሰነዝረዉን ጥቃት እንድታቆም ቢን ሰልማን ጠይቀዋል። ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረዉ የእስራኤል-ሃማስ ጦርነትን እና አካባቢዉ ላይ እየተባባሰ የመጣዉን ቀዉስ በተመለከተ ሪያድ ላይ የተሰበሰቡት የአረብ እና የሙስሊም መሪዎች አዲስ ለተመረጡት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ መልዕክት ለመላክ እድል እንደሆነም ተደርጎ ታይቷል። «ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እስራኤል በፍልስጤምና በሊባኖስ ወንድሞቻችን ላይ የምትፈፅመዉን ጥቃት በአፋጣኝ ታቁም። እንዲሁም እስራኤል የኢራንን እስላማዊ ሪፐብሊክ ሉዓላዊነት እንድታከብር እና ግዛቶቿን ከማጥቃት እንድትቆጠብ እንዲያደር እና ዓለም አቀፍ ሰላምና ደህንነትን የማስጠበቅ ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪያችንን እናሰማለን።» የአረብ ሊግ ከዓመት በፊት ተመሳሳይ ስብሰባዎችን በሪያድና በጅዳ ያካሄደ ሲሆን እስራኤል በጋዛ ላይ የፈፀመችው ጥቃት በጽኑ አውግዟል።
ትራምፕ ስለ ዩክሬኑ ጦርነት ከሾልዝ እና ፑቲን ጋር ተወያዩ
አዲስ ተመራጩ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከጀርመን ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ ጋር በስልክ ባደረጉት ንግግር በአውሮጳ "ሰላምን በመመለስ" ጉዳይ ላይ ተነጋገሩ። የጀርመን መንግስት ቃል አቀባይ ስቴፈን ሄቤስትሮይት፤ ትራምፕ እና ሾልዝ ይህን ግብ ለማሳካት "ተስማምተዋል" ብለዋል። ቀደም ሲል ዋሽንግተን ፖስት እንደዘገበው፣ ትራምፕ ከሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር እንዲሁ በስልክ ባደረጉት ውይይት ትራምፕ በዩክሬን ያለዉ ጦርነት እየተባባሰ እንዳይመጣ አስጠንቅቀው ነበር። ሁለቱም ፖለቲከኞች ጦርነቱን በማብቃት ጉዳይ ላይ ለመነጋገር ተጨማሪ ውይይቶችን ማድረግ እንደሚፈልጉ መግለፃቸዉም ተመልክቷል። እንደ አሜሪካኑ ጋዜጣ ዋሽንግተን ፖስት ዘገባ፤ የዩክሬይን የወደፊት ክልላዊ ግዛት ጥያቄንም በተመለከተ ትራምፕ እና ኦላፍ ሾልዝ በአጭሩ አንስተዉ ተነጋግረዋል። ሾልዝ በቅርቡ ከፑቲን ጋር እንደሚነጋገሩም ከጀርመን ቴሌቭዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልፀዋል። ዛሬ ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበዉ ፤ ትናንት እሁድ ምሽት የተካሄደዉ የትራምፕ እና የጀርመኑ ቻንስለር የስልክ ዉይይት ለ 25 ደቂቃዎች የዘለቀ እና በጣም ወዳጃዊ ዉይይት እንደነበር የጀርመኑ ቻንስለር ተናግረዋል።
ጀርመን፤ በጀርመን ፓርላማ የመተማመኛ ድምፅ ሊሰጥ ነዉ
የጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ እስከያዝነዉ የጎርጎረሳዉያን 2024 ዓመት መጨረሻ አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ ለማስቻል በጀርመን ፓርላማ ቡንደስታግ የመተማመኛ ድምፅ እንዲሰጥባቸዉ እንደሚሰሩ አስታወቁ። የሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ አባሉ፤ የጀርመን ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ፤ ከጀርመን ከቴሌቪዥን ጣብያ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ «የፓርላማ አባላቱ አዲስ ለሚካሄዱት ምርጫዎች የጊዜ ሰሌዳ ላይ መስማማት ይኖርባቸዋል፤ ቀኑ ሲወሰን፤ በቀጣይ የሚደረጉ እቅዶች ላይ ለመስራት እችላለሁ» ሲሉ ተናግረዋል። ጀርመን በአፋጣኝ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ አዲስ ሕጋዊ መንግሥት እንደሚያስፈልጋትም ገልፀዋል። በጀርመን ሶሻል ዴሞክራቶች፤ አረንጓዴዎች እና ሊበራል ፓርቲዎች የተጣመሩበት የሦስትዮሹ መንግሥት ከፈረሰ በኋላ፣ ቻንስለር ሾልዝ ጥር 7 ቀን 2017 አዲስ የቡንዴስታግ ማለትም የጀርመን ፓርላማ የመተማመኛ ድምፅ እንዲሰጥብኝ እጠይቃለሁ ሲሉ አስታዉቀዉ ነበር። ይህን የቻንስለሩን ሃሳብ የጀርመን የተቃዋሚዎች ሕብረት ዉድቅ አድርገዉ በጀርመን ምክር ቤት የፊታችን ረቡዕ የመተማመኛ ድምፅ እንዲሰጥ፤ ጊዜ የለንም ሲሉ መጠየቃቸዉን የጀርመኑ የዜና አገልግሎት «dpa» ዘግቧል።
አዘርባጃን፤ ባኩ ላይ የአየር ንብረት ጉባዔ ተከፈተ
የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት (WMO) ዛሬ አዘርባጃን ባኩ ላይ የአየር ንብረት ጉባዔ ሲከፈት ለአየር ንብረት ለውጥ ፍጥነት ምላሽ ለመስጠት ከፍተኛ ጥንቃቄ መሰጠቱን ገለፀ። መዲና ባኩ ላይ እየተካሄደ ባለዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመሪዎች ጉባዔ ላይ የምድር ሙቀት መጨመርን ለመገደብ እና በሙቀት መጨመር እንደ ከፍተኛ የሙቀት ማዕበል፣ አውሎ ንፋስ እና ጎርፍ ባሉ አደጋዎች ተደጋጋሚ ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰባቸው ድሃ አገራት አዲስ የገንዘብ ቃል ኪዳን ማድረግ ስለሚቻልባቸው መንገዶች ይወያያል ተብሎ ይጠበቃል። ዓለም አቀፉ አካል ዓመታዊውን ዓለም አቀፍ የሙቀት መጨመር ሪፖርት ሲያቀርብ ይህን ግብ ማሳካት አጣዳፊ መሆኑን አመልክቷል።
አዜብ ታደሰ / እሸቴ በቀለ