1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰኔ 21 ቀን 2016 ዓ.ም. የዓለም ዜና

Shewaye Legesseዓርብ፣ ሰኔ 21 2016

ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ምሥራቅ ቦረና በሚል አዲስ ዞን ስር የሚተዳደረው ጎሮዶላ ወረዳ እየተጓተተ በሚከፈው ደሞዝ መቸገራቸውን ሠራተኞች አመለከቱ። ሠራተኞቹ እንደሚሉት ከሚያዚያ ወር ወዲህ ደሞዝ አላገኙም። የየመን ሁቲ አማጽያን ዛሬም በቀይ ባሕር ላይ ስትጓዝ በነበረች በመርከብ ላይ አምስት ሚሳኤል መተኮሳቸው ተነገረ። የብሪታንያ የባሕር ንግድ ኮርፖሬሽን ዛሬ እንደገለጸው በመርከቧ ላይ ጉዳት አልደረሰም። የአውሮጳ ሕብረት ሃገራት መሪዎች ለሕብረቱን ኮሚሽን ፕሬዝደንትነት ዑርዙላ ፎንደር ሌይንን ለሁለተኛ ጊዜ በይፋ ሰየሙ። ጉባኤው የኢስቶኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ካያ ካሌስንም ለሕብረቱን የውጭ ጉዳይ ኃላፊነት መርጧል።

https://p.dw.com/p/4heOa

ምሥራቅ ቦረና፤ የሠራተኞች ደሞዝ መዘግየት ቅሬታ

ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ምሥራቅ ቦረና በሚል አዲስ ዞን ስር የሚተዳደረው ጎሮዶላ ወረዳ እየተጓተተ በሚከፈው ደሞዝ መቸገራቸውን ሠራተኞች አመለከቱ። አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡት የወረዳው የመንግሥት ሠራተኞች የሦስት ወር ደመወዝ እንዳልተከፈላቸውም ገልጸዋል። አንድ የወረዳው የመሬት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ሠራተኛ እንደሚሉት ምንም እንኳን ዛሬ ሰኔ 21 ቀን ቢሆንም ከሚያዚያ ወር ወዲህ የተከፈላቸው ወርሃዊ ደሞዝ የለም።

«ከባለፈው ወር ደመወዝ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ደመወዝ አልገባልንም። ደመወዝ ከተከፈለን ሁለት ወር ሊደፍን ነው። ከዚህ በፊትም ሁለት አምስት ቀን እያሳለፉ ደመወዝ ማስገባት የተለመደ ነበር።»

ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ምሥራቅ ቦረና በሚል አዲስ ዞን ስር የሚተዳደረው ጎሮዶላ ወረዳ ቀደም ሲል በጉጂ ዞን ስር ይተዳደር የነበረው አካባቢ ነው። ከአዲሱ ዞን መዋቅር በኋላ የተፈጠረውን የሕዝብ ቅሬታ ተከትሎ ጉዳይ ያላቸው ተገልጋዮች ወደ መንግሥት መሥሪያ ቤት መጥተው አገልግሎት ሲያገኙ እንደማይታዩ ነው አስተያየት ሰጪው ያመለከቱት። ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የጎሮዶላ ወረዳ ምክር ቤት የፋይናንስ እና በጀት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዳንጎ ሙዳ በበኩላቸው የዞን መዋቅር ተቃውሞውን ተከትሎ የደመወዝ መቀቋረጥ ይስተዋላል ነው የሚሉት።

«ከዞን መዋቅሩ በኋላ ከኅብረተሰቡ ተቃውሞ የተነሳ ከክልል የወረደው በጀት ምንነት የሚታወቅ ነገር የለም። ለሠራተኛ በተለያዩ ጊዜያት ደመወዝ ያልተከፈለባቸው ጊዜያት አሉ። በዚህ ወርም እስካሁን መከፈል የነበረበት አልተከፈለምና ችግሩ ምን እንደሆነ አናውቅም።»

አክለውም ከዚህ በፊትም ለስድስት ወራት ሳይከፈል የቆየ የወረዳው ሠራተኞች ደመወዝ ዘግይቶ በውሳኔ መከፈሉንም አስረድተዋል። በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የተጠየቁት የወረዳው ፋይናንስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደገፋ ታደለ ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ከአዲስ አበባ ዘጋቢያችን ሥዩም ጌቱ በላከው ዜና ጠቅሷል።

 

ዱባይ፤ የቀይ ባሕር የመርከብ ላይ ጥቃት

የየመን ሁቲ አማጽያን ዛሬም በቀይ ባሕር ላይ ስትጓዝ በነበረች በመርከብ ላይ አምስት ሚሳኤል መተኮሳቸው ተነገረ። የብሪታንያ የባሕር ንግድ ኮርፖሬሽን ዛሬ እንደገለጸው በመርከቧ ላይ ጉዳት አልደረሰም። መርከቧ በሁቲዎች ቁጥጥር ሥር በሆነው የየመን የባሕር ወደብ አቅራቢያ ጥቃቱ እንደተሰዘረባት ሆኖም ጉዳት ሳያገኛት ወደ ሰሜን አቅጣጫ መጓዟንም ገልጿል። የተተኮሱት ሚሳኤሎች ከመርከቧ አቅራቢያ መውደቃቸው የተገለጸ ሲሆን የመርከቡ ካፒቴን ጉዳት እንዳልደረሰ ማረጋገጡን ሮይተርስ በዘገባው ጠቅሷል። እንዲያም ሆኖ ሁቲዎች ለድርጊቱ ኃላፊነት አልወሰዱም። እስካሁን የሁቲ አማጽያን በቀይ ባሕር ላይ ሲጓዙ በነበሩ 60 መርከቦች ላይ የሚሳኤል እና የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ማድረሳቸው ነው የተገለጸው።

 

ብራስልስ፤ የአውሮጳ ሕብረት ጉባኤና ሹመት

የአውሮጳ ሕብረት ሃገራት መሪዎች ለሕብረቱን ኮሚሽን ፕሬዝደንትነት ዑርዙላ ፎንደር ሌይንን ለሁለተኛ ጊዜ በይፋ ሰየሙ። ቀደም ብሎም ማክሰኞ ዕለት መሪዎቹ ፎደር ሌይን በያዙት ኃላፊነት እንዲቀጥሉ ተስማምተው እንደነበር የአውሮጳ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ቻርልስ ሚሼል ገልጸዋል። እንዲያም ሆኖ የፎንደር ሌይን ሥልጣን የሚረጋገጠው አዲስ በተመረጠው የአውሮጳ ሕብረት ምክር ቤት አባላት ድጋፍ ካገኘ ይሆናል። በሕብረቱ አባል ሃገራት ጉባኤ ስምምነት መሠረትም የቀድሞው የፖርቱጋል ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ኮስታ ቀጣዩ የሕብረቱ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ይሆናሉ። የኢስቶኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ካያ ካሌስ ደግሞ የሕብረቱን የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬልን ተክተው ተሰይመዋል። የሕብረቱ አባል ሃገራት መሪዎች ለቀጣይ አምስት ዓመት የሚከናወኑ አጀንዳዎችን ለማጽደቅና የተቋማት መሪዎችን ለመምረጥ ለሁለት ቀናት ያካሄዱት ጉባኤ ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል።

 

ላ ፓዝ፤ ዐቦሊቪያ መንግሥት ተጨማሪ አራት ተጠርጣሪዎችን አሰረ

የቦሊቪያ መንግሥት በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የተጠረጠሩ ተጨማሪ አራት ሰዎችን ማሠሩን አስታወቀ። ረቡዕ ዕለት ፕሬዝደንት ሉዊስ አርሴን ከሥልጣን ለማስወገድ ተደርጎ ከከሸፈው የመፈንቅለ መንግሥት ሤራ ጋር በተገናኘ የታሠሩ ሰዎች ቁጥር 21 ደርሷል። ከሀገሪቱ ሚኒስትሮች አንዱ ኤድዋርዶ ዴል ካስቲሎ ለዜና አውታሮች እንደተናገሩት ከታሠሩት ውስጥ ወታደራዊ መኮንኖች ይገኙበታል። መሣሪያ የተጠመደበትን ተሽከርካሪ እየነዳ ቤተመንግሥቱን ጥሶ ለመግባት የሞከረው ሌላኛው ታሣሪ የፕሬዝደንቱን ሕይወት አደጋ ላይ በመጣል ተጠያቂ እንደሆነም አመልክተዋል። ቀደም ሲል ከተያዙት መካከልም የስለላ እና የመረጃ ቅብብል ላይ ይሠሩ ነበር የተባሉ እንደሚገኙበት ተገልጿል። የቦሊቪያ መንግሥት መፈንቅለ መንግሥቱ በዋነኛው ጀነራል ኹአን ኾሴ ዙኒጋ መመራቱን ይገልጻል።  አላማውም በኤኮኖሚ ቀውስ በምትናጠው ሀገር የፕሬዝደንቱን እውቅና ከፍ ለማድረግ ሳይሆን አይቀርም የሚል ነው። ፕሬዝደንቱ ግን ትናንት ምሽት በሰጡት መግለጫ የተባለውን ውድቅ በማድረግ ጀነራል ዙኒጋም ሆኑ የተያዙት ሌሎች ተጠርጣሪዎች ለሕግ እንደሚቀርቡ ዝተዋል።

 

ዋሽንግተን፤ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንታዊ ክርክር

በዩናይትድ ስቴትስ በተካሄደው የፕሬዝደንታዊ የምርጫ የመጀመሪያ ዙር ክርክር በሥልጣን ላይ ያሉት ፕሬዝደንት አቀራረብ በጣም ደካማ  እንደሆነ ታዛቢዎች አመለከቱ። ትናንት በፕሬዝደንት ጆ ባይደን እና በተፎካካሪያቸው ዶናልድ ትራምፕ መካከል በተካሄደው ክርክር ትራምፕ ሃሳባቸውን ለመግለጽ ተሽለው ታይተዋል። የ81 ዓመቱ ፕሬዝደንት ባይደን የተረበሸና የተቆራረጠው አገላለጻቸው በተለይም የዴሞክራቲክ ፓርቲ ደጋፊዎችን ስጋት ላይ መጣሉ ነው የተነገረው። የአሜሪካን ፕሬዝደንታዊ ክርክር ጉዳይ ባለሙያ የሆኑት የሚቺጋን ዩኒቨርሲቲው ባልደረባ አሮን ካል በተለይም የክርክሩ መጀመሪያ አካባቢ ተፎካካሪዎች የሚያሳዩት አቀራረብ ወሳኝ መሆኑን በማመልከት የትናንቱን ግን እጅግ የከፋ ይሉታል።

«አዎ በተለይም የመጀመሪያዎቹ 15 እና 20 ደቂቃዎች እንደ ሥልጣን ላይ የሚገኝ እጩ ተፎካካሪ እጅግ የከፋው አቀራረብ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ብዬ አስባለሁ። አጀማመራቸው በጣም ቀርፋፋ ነበር። እንደምታውቁት በርካታ ሰዎች እሳቸው የተሻለ አቀራረብ እንዲኖራቸው ብዙ ለፍተዋል፤ ብዙዎችም ለመርዳት ዝግጅዎች ነበሩ። ያንን ሁሉ ሥልጠና ወስዶ እንደዚያ ያለ አቀራረብ ማሳየት ግን በጣም አሳዛኝ ነው። »

እንዲያም ሆኖ ባይደን  ከተለያዩ ጥፋቶችና የወንጀል ጉዳዮች ጋር አገናኝተው ትራምፕን በመተንኮስ እራሳቸው መከላከል ላይ እንዲያተኩሩ ለማድረግ መሞከራቸውን ግን እንደ አንድ ጠንካራ ስልት አንስተዋል። ምንም እንኳን የባይደን አቀራረብ ደጋፊዎቻቸውን ቢያሳስብም በሀገሪቱ የውጪ ፖሊሲ ላይ ያን ያህል የጎላ ለውጥ ሊያስከትል እንደማይችል ነው ተንታኞች ያመለከቱት። የባይደን ደጋፊዎች አስቀድሞ በፕሬዝደንታዊ ክርክሩ የተሻለ ተስፋ እንደሚገኝ ገምተው እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፤ በተቃራኒው አጋጣሚው ለትራንፕ ብርታት እንደሰጣቸው እየተገለጸ ነው።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።