ጋዛ የእርዳታ ድርጅቶች ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ጋዛ ለማስገባት እየጣሩ ነው
አንድ የአውሮጳ ኅብረት ከፍተኛ ዲፕሎማት ሰዎችን ማስራብ እንደ ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው ካሉ በኋላ ለጋሽ መንግሥታት የእርዳታና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ዛሬ የምግብ እርዳታ በየብስ በአየርና በባህር ወደ ጋዛ ለማስገባት የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው መቀጠላቸው ተሰምቷል። የአውሮጳ ኅብረት የውጭ ጉዳዮች ሃላፊ ጆሴፕ ቦሬል ትናንት ለፀጥታው ምክር ቤት ባሰሙት ንግግር ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ጋዛ መግባት እንዳለበት አስታውቀው የአውሮጳ ኅብረትም ይህ እንዲሳካ የተቻለውን ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል። ሆኖም እርዳታ ጋዛ ሊደርስ ያልቻለው በሰው ሰራሽ ችግር ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።
«(በጋዛ)የተፈጥሮ አደጋ ሳይሆን ሰብዓዊ ቀውስ ነው ያለው። ጎርፍ አይደለም የመሬት መንቀጥቀጥም አይደለም። ሰው ሰራሽ ችግር ነው። በአየርም ሆነ በባህር እርዳታ ማቅረብ የሚቻልባቸውን አማራጮች ስንመለከት ማድረግ እንደሚገባን መገንዘብ አለብን። ምክንያቱም መንገድ በመዘጋቱ በሰው ሰራሽ ችግር በመዘጋቱ በተለመደው መንገድ እርዳታ ማቅረብ አልተቻለም። ሰዎችን ማስራብ እንደ ጦር መሣሪያ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት በዩክሬን መሆኑን ስናወግዝ በጋዛም ስለሚሆነው ተመሳሳይ ቃላት መጠቀም አለብን።»
በርካታ ሰዎችን የገደለውና ብዙ ንብረትም እንዳልነበረ ያደረገው የእስራኤል ሀማስ ጦርነት የ2.4 ሚሊዮን ሰዎች መኖሪያ በሆነው በፍልስጤም ግዛቶች ረሀብ እንዳያስከትል ማስጠንቀቂያዎች እየጎረፉ ነው። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በግብጽ በኩል ወደ ጋዛ የሚገባው እርዳታ አዝጋሚ መሆን ምግብ ማግኘት ያልቻሉ የጋዛ ነዋሪዎችን ትዕግስት አሳጥቶ ወደ አካባቢው የሚገቡ እርዳታዎችን ዘረፋ አስከትሏል።የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው ኦፕን አርምስ የተባለው አንድ የስፔይን የእርዳታ መርከብ ትናንት ሁለት መቶ ቶን እርዳታ ጭኖ ከቆጵሮስ ወደ ጋዛ እየተጓዘ ነው። በርካታ የአረብና ምዕራባውያን ሀገራት እርዳታዎችን ከአየር በፓራሹት ወደ ጋዛ ሲጥሉ ነበር። ሞሮኮ ደግሞ አንድ አውሮፕላን ሙሉ የእርዳታ አቅርቦት በእሥራኤሉ የቤንጉርዮን አውሮፕላን ማረፊያ ልካለች። የእስራኤል ጦር እንዳስታወቀው የተመ የምግብ መርሀ ግብር ስድስት እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎችን በደቡብ እስራኤል በኩል ክፉኛ ወደተጎዳው ወደ ሰሜን ጋዛ ልኳል። ድርጅቱ እንደሚለው ለሰሜን ጋዛ በየቀኑ እርዳታ ማድረስም ሆነ ፤በቀጥታ ወደ ሰሜን ጋዛ የሚወስዱ መግቢያዎችም አስፈላጊ ናቸው።
ዋሽንግተን ፍልስጤማውያንን የሚረዳው የተመድ ቅርንጫፍ የሚሰጠው እርዳታ ላይ የተጣለው እገዳ ሊቀጥል ይችላል
የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት ለፍልስጤማውያን እርዳታ የሚሰጠው የተመድ ቅርንጫፍ ላይ ለጊዜው የጣሉትን የእርዳታ እገዳ ቋሚ ለማድረግ እየተዘጋጁ መሆኑ ተዘገበ። ምንም እንኳን የባይደን አስተዳደር የእርዳታ ድርጅቱ ስራ አስፈላጊ ነው ቢልም ከዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት አባላት ተቃውሞ ስለገጠማቸው ባለሥልጣናቱ እገዳውን ቋሚ ለማድረግ እየተዘጋጁ ነው ተብሏል። እስራኤል ከድርጅቱ 13 ሺህ ሠራተኞች 12ቱን በመስከረም 26 ቀን 2016ቱ የሀማስ ጥቃት ተሳትፈዋል ስትል ከከሰሰች በኋላ የዩናይትድ ስቴትስና ሌሎች በርካታ ሀገራት ፍልስጤማውያንን ለሚረዳው ለዚህ ድርጅት የሚሰጡትን እርዳታ አቋርጠዋል። እስራኤል ለድርጅቱ ያቀረበችውን ክስና መረጃዎች የመረመረው የተመድ ከሠራተኞቹ አንዳንዶቹን አባሯል። በምህጻሩ UNRWA ለተባለው ለዚህ ድርጅት በየዓመቱ 400 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ የምትሰጠው ዋነኛዋ ለጋሽ ዩናይትድ ስቴትስ እርዳታውን ከመቀጠሏ በፊት የምርመራውን ውጤትና የተወሰዱትን የማስተካከያ እርምጃዎች ማወቅ እንደምትፈልግ ገልጻለች። ይሁንና ከሁለቱም ፓርቲዎች ለድርጅቱ የሚሰጠው እርዳታ ተቃውሞሞ ስለገጠመው በቅርቡ አሜሪካን እርዳታውን መቀጠሏ አጠራጣሪ ነው ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
በርሊን ሾልዝ ታውሩስን ለዩክሬን የማይሰጡበትን ምክንያት ለጀርመን ፓርላማ ተናገሩ
የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ ታውሩስ የተባለውን የረዥም ርቀት ተመዘግዛጊ ሚሳይል ወደ ዩክሬን መላክን የተቃወሙበትን ምክንያት ዛሬ ለጀርመን ፓርላማ አስረዱ።ሾልዝ ክየቭን እንደሚያምኑ አስታውቀው አስተዋይነት ግን ድክመት አይደለም ብለዋል። ከዩናይትድ ስቴትስ ቀጥሉ ለዩክሬን በብዛት የጦር መሣሪያ የምታቀርበውን ጀርመንን ዩክሬን የታውሩስ ሚሳይሎች እንዲሰጧት ብትጠይቅም ጀርመን ግን ፈቃደኛ አልሆነችም። የታውሩስ ሚሳይሎች እስከ 500 ኪሎሜትር ርቀት የሚምዘገዘጉ እና በጽንሰ ሃሳብ ደረጅ በሩስያ ግዛት የሚገኙ ዒላማዎችን ለማጥቃት የሚያስችሉ ናቸው።ጥቄው የቀረበላቸው ሾልዝ ባለፈው ወር ሀገራቸው በዩክሬኑ ጦርነት በቀጥታ ተሳታፊ መሆን የለባትም ሲሉ መልስ ሰጥተው ነበር። ከረዥም ጊዜ አንስቶ ጦርነቱ እንዳይባባስና ጀርመንና ኔቶም ወደ ጦርነቱ ሳይገቡ ዩክሬንን ለመርዳት ያላቸውን ዝግጁነት አጽንኦት ሰጥተው የሚናገሩት ሾልዝ በተለይ ጀርመን በጦርነቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆን የለባትም ሲሉ በጥብቅ ተናግረዋል። ሾልስ ለጀርመን ፓርላማ እንደተናገሩት በርሳቸው እምነት ታውሩስ በጣም ረዥም ርቀት የሚምዘገዘግ ሚሳይል ነው። በዚህም ምክንያት ሚሳይሉ ከዒላማው ውጭ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል ተብሎ ስለሚታሰብ የራሷ የጀርመን ወታደሮች ካልተቆጣጠሩት በስተቀር ሚሳይሉን መላክን ተቃውሜያለሁ ብለዋል።
ብራሰልስ የአውሮጳ ኅብረት ለሄይቲ እርዳታ ሊልክ ነው
የአውሮጳ ኅብረት በወሮበሎች አመጽ ችግር ላይ ለወደቀችው ሄይቲ የ20 ሚሊዮን ዩሮ ወይም የ21.8 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ እንደሚልክ አስታወቀ። የኅብረቱ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ባላዝ ሹጅቫሪ ኅብረቱ እርዳታውን ወደ ሄይቲ የሚልከው በድንገተኛው የወሮበሎች አመጽ ሰበብ በሀገሪቱ የሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎት እየጨመረ በመሄዱ መሆኑን ተናግረዋል። እንደ ቃል አቀባይዋ እርዳታው ሰብዓዊ አጋሮች እጅግ አስፈላጊ የሆኑትን የህዝቡን ፍላጎቶች እንዲያሟሉ ይረዳል። የሄይቲ ጠቅላይ ሚኒስትር አርየል ሄነሪ ትናንት ስልጣን ለመልቀቅ መስማማታቸውን አስታውቀዋል። በአመጹ የመንግሥት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ስራ አቁመዋል።በርካታ ሰዎች ተፈናቅለዋል። አስከሬኖችም በየጎዳናዎችም ተጥለዋል። ከሄቲ ዋና ከተማ ፖር ኦፕ ረንስ አብዛኛውን ክፍል የያዙትና ፖሊስ ጣቢያዎች፣ እስር ቤቶችናና ሌሎች ተቋማት ላይ ጉዳት ያደረሱት የወሮበሎቹ ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከስልጣን ይልቀቁ የሚል ነው። በቀውሱ ምክንያት ሄይቲን ለማረጋጋት በሚደረገው ዓለም አቀፍ ጥረት ውስጥ ልትሳተፍ የነበረችው ኬንያ እቅዷን ለጊዜው ማቆሟን አስታውቃለች።
ቴላቪቭ በሀማስ ታግቶ የነበረው ጀርመናዊ እስራኤል መሞቱ ተነገረ
ባለፈው መስከረም መጨረሻ በጋዛ ሰርጥ ታግቶ የነበረው ጀርመናዊ እስራኤላዊ መሞቱን በእስራኤል የጀርመን አምባሳደር አስታወቁ። በእስራኤል የጀርመን አምባሳደር ስቴፈን ዛይበርት፣ኢትይ ቼን የተባለው ጀርመናዊ በሕይወት አለ የሚል ተስፋ እንደነበር አስታውቀው ሆኖም መሞቱን አውቀናል ሲሉ ዛሬ በኤክስ ወይም በቀድሞ መጠሪያው ትዊተር ገጻቸው ጽፈዋል። ዛይበርት እንዳሉት መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. በሀማስ የተገደለው የ19 ዓመቱ ጀርመናዊ እስራኤላዊ አስከሬን ወደ ጋዛ መወሰዱን አስታውቀዋል። ሀሳባቸውም በሕይወት ያለ መስሏቸው እንዲፈታ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርጉ ከቆዩት ቤተሰቦቹ ጋር መሆኑን ገልጸዋል። የናታንያ ከተማው ወታደር ቼን መገደሉን ትናንት ነበር የእስራኤል ጦር ያሳወቀው። የእስራኤል ጦር የቼንን ሌሎች ዜግነቶች አልገለጸም ሆኖም በሌሎች የመገናኛ ብዙሀን ዘገባዎች ቼን አሜሪካዊም እንደነበር ተዘግቧል። የቼን ወላጆች በልጃቸው ሞት ልባችን ተሰብሯል ማለታቸውን የጀርመን ዜና አግልግሎት DPA ዘግቧል። ባለፈው መስከረም 26 ቀን 2016 ዓም ሀማስ እስራኤል ውስጥ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ ቁጥራቸው 250 የሚጠጋ ሰዎችን አግቶ ወደ ጋዛ ሰርጥ ወስዷል። ባለፈው ህዳር እሥራኤልና ሀማስ የተኩስ አቁም ባደረጉበት ወቅት 105 ታጋቾች ተለቀው ነበር።የእስራኤል መንግሥት እንደሚለው በአጠቃላይ በጋዛ ከታገቱት መካከል ቁጥራቸው ወደ መቶ እንደሚደርስ የተገለጸው በሕይወት አሉ ተብሎ ይታመናል።
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር