1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ዜና፤ መስከረም 13 ቀን 2017 ዓ.ም ሰኞ

ሰኞ፣ መስከረም 13 2017

--ሶማሊያ ከግብፅ ከፍተኛ መጠን ያለዉ የጦር መሳሪያን ለሁለተኛ ጊዜ ተረከበች። ግብፅ ዜጎችዋ በቶሎ ከሶማሌላንድ እንዲወጡም ጠይቃለች።--ፓኪስታን ዉስጥ የኢትዮጵያንና የሩስያ ዲፕሎማቶችን ጨምሮ የተለያዩ ሃገራት ልዑኮች ከጥቃት መትረፋቸዉ ተመለከተ።--ሱዳን ባለፈው ነሐሴ ወር ብቻ በኮሌራ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ወደ 388 ከፍ ማለቱ ተነገረ። በወረርሽኙ ወደ 13,000 ሰዎች ተይዘዋል።--እስራኤል በሊባኖስ እያካሄደች ያለዉ ጥቃት 'አደገኛ መዘዝ' ያስከትላል ስትል ኢራን አስጠነቀቀች። በእስራኤል እና በሂዝቦላ ሚሊሻ መካከል እየጠነከረ የመጣው ዉጥረት ፤ በመካከለኛው ምስራቅ የሚታየዉን ቀዉስ እንዳያሰፋ ስጋት አሳድሯል።

https://p.dw.com/p/4kzeH

ፓኪስታን፤ የተለያዩ ሃገራት ዲፕሎማቶች ከጥቃት ተረፉ 

ፓኪስታን ዉስጥ የኢትዮጵያን እና የሩስያ ዲፕሎማቶችን ጨምሮ የተለያዩ ሃገራት ልዑኮች ከጥቃት መትረፋቸዉ ተሰማ። የፓኪስታን ባለስልጣናት እንደገለፁት፤ ዲፕሎማቶች የነበሩበት ተሽከርካሪን አጅቦ ሲጓዝ የነበረ ተሽከርካሪ ላይ በደረሰዉ የቦንብ ጥቃት አንድ ፖሊስ ተገድሏል፤  ሶስት ደግሞ ቆስለዋል።  መንገድ ዳር የተጠመደ የቦንብ ጥቃት የደረሰዉ፤  ዲፕሎማቶቹ አፍጋኒስታን አዋሳኝ ላይ ወደ ሚገኝ የቱሪስት መዳረሻ ቦታ ላይ የሃገሪቱ ንግድ እና ኢንዱስትሪ መስርያ ቤት በቱሪዝም እና የእጅ ጥበባት ብሎም ስለከበሩ ድንጋዮች ጉዳይ ባዘጋጀዉ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ሲጓዙ እንደነበር ነዉ የተገለፀዉ። ዲፕሎማቶቹ ከጥቃቱ ያመለጡት  አጅቧቸዉ የነበሩት ፖሊሶች ተሽከርካሪ ዲፕሎማቶቹ የተሳፈሩበትን ተሽከርካሪ እየመራ ስለነበረ፤ ጥቃቱ መጀመርያ ባገኘዉ በፖሊሶቹ ተሽከርካሪ ላይ ማረፉን የፓኪስታን ባለስጣናትን ተናግረዋል። ለጥቃቱ እስካሁን ሃላፊነትን የወሰደ አካል የለም። ታሊባን በበኩሉ በጥቃቱ እጄ የለበትም ብሏል። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ አምባሳደርን ጨምሮ በሌሎች የዲፕሎማቲክ ኮንቮይ ላይ የተፈጸመውን የሽብር ጥቃት አውግዟል። ሚኒስቴር መስርያ ቤቱ ዲፕሎማቶቹን አጅበዉ ለነበሩት እና በጥቃቱ  ህይወታቸዉን ላጡት የሟች ፖሊስ ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝቷል፡፡ ፓኪስታን ዉስጥ ከጥቃት ያመለጠዉ የዲፕሎማቶች ቡድን ዉስጥ የኢትዮጵያ፤ የሩስያ ፤ የኢንዶኔዢያ፤ የፖርቹጋል፤ የካዛኪስታን፤ የቦስኒያና ሄርዞጎቪና፣ የዚምባቡዌ፣ የሩዋንዳ፣ የቱርከምንስታን፤ የቬትናም፤ የኢራን፣ እና የታጃኪስታን አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ይገኙበታል። ከጥቃቱ በኋላ የሁሉም ሃገራት ዲፕሎማቶች ወደ መዲና ኢስላማድ መመለሳቸዉም ተመልክቷል። ታሊባን በጎርጎረሳዉያኑ 2021 ዓም የአፍጋኒስታንን ስልጣን ከተቆጣጠረ ወዲህ የፓኪስታን ተልባን ጥቃት መጨመሩ ተያይዞ ተዘግቧል። ባለፈዉ የጎርጎረሳዉያን 2023 ዓመት በፓኪስታን ታሊባኖች 930 ሰዎች ተገድለዋል፤ ወደ 2000 የሚሆኑ ደግሞ መቁሰላቸዉ የወጣዉ ዘገባ ያሳያል። ከተገደሉት እና ከቆሰሉት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ የፓኪስታን የፀጥታ ኃይላት ናቸዉ። 

ግብፅ፤ ለሶማልያ ለሁለተኛ ጊዜ የጦር መሳርያን ሰጠች 

በኢትዮጵያ እና በሶማልያ መካከል ዉጥረቱ እየጨመረ በመጣበት በአሁኑ ወቅት ሶማሊያ ከግብፅ ከፍተኛ መጠን ያለዉ የጦር መሳሪያን ለሁለተኛ ዙር መረከብዋ ተሰማ። ሮይተርስ የዜና አገልግሎት የሶማልያ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበዉ፤ ግብፅ በዚህ ዙር ለሶማልያ የሰጠችዉ ከፍተኛ መጠን ያለዉ የጦር መሳርያን ጨምሮ ፀረ-አውሮፕላን መሳርያዎች ፤ እና የተለያዩ ተተኳሽ መድፎች ይገኙበታል። ካሲማዳ የተባለ አንድ ድረገፅ  እንደዘገበዉ ከሆነ ደግሞ፤ ኢትዮጵያ እና ሶማልያ አወዛጋቢ የተባለ የወደብ ስምምነት ከፈፀሙ እና በሁለቱ ሃገራት መካከል ዉጥረት በነገሰበት በአሁኑ ወቅት፤ ግብጽ ለሶማልያ የሰጠችዉ የጦር መሳርያ እና ሌሎች ቁሳቁሶች በግብፅ ወታደራዊ የእቃ መጫኛ መርከብ ተጭነዉ ትናንት ለዛሬ አጥብያ ማለትም መስከረም 12 ለ መስከረም 13 አጥብያ መቃደሾ ዋንኛ የባህር ወደብ ደርሰዋል። የተለያዩ ዘገቦች እንደሚጠቁሙት ግብፅ የጦር መሳርያዉን የላከችዉ ለሶማልያ ፌደራል መንግሥት ነዉ። ሌሎች ዘገቦች እንደሚያመለክቱት ደግሞ ሶማልያ የጦር መሰራያዎቹን ከግብፅ ገዝታ ነዉ። ይሁንና ወዳጅነታቸዉ በተለይ በዚህ አመት እየጠነከረ የመጣዉ የግብፅም ሆነ የሶማልያ መንግሥት ስለጉዳዩ በይፋ የገለፁት ነገር የለም። ግብፅ ለሶማልያ የጦር መሳርያ መላክዋ የተሰማዉ፤ ኢትዮጵያ ለከፊል ራስ ገዝ ለሆነው ፑንትላንድ የጦር መሳሪያ ትሰጣለች ስትል ሶማልያን ከከሰሰች በኋላ መሆኑ ነዉ። በሌላ በኩል ግብፅ በሶማሌላንድ የሚኖሩ እና የሚሰሩ ዜጎችዋ አካባቢዉን በቶሎ ለቀዉ እንዲወጡ ማሳሰብዋም ተሰምቷል።

ኬንያ፤ ተጨማሪ 400 የሰላም አስከባሪ ፖሊሶችን ወደ ሄቲ ክትልክ ነዉ

የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ተጨማሪ 600 የፖሊስ መኮንኖችን ሄይቲ ወደሚገኘው እና «የብዝሃ ሀገር ደህንነት ድጋፍ » ወደሚባለዉ ተልዕኮ ለማሳማራት ቃል ገቡ። ኬንያ በተመድ ከሚደገፍዉ የጸጥታ ኃይል ጋር በሄይቲ ወሮበሎችን በመፋለም ላይ ያለውን የፖሊስ ኃይል ለማገዝ ወታደሮቿን ማሰማራትዋ ይታወቃል። ሩቶ እንደተናገሩት መንግሥታቸዉ በሚቀጥለው ሳምንት መጨረሻ ተልዕኮዉ የሚያበቃዉ የደህንነት ድጋፍ ኃይል ፤ ወደ ሙሉ የተመድ የሰላም አስከባሪ ጓድነት እንዲቀየር ፤  ከተመድ ጋር እየተነጋገረ ነው ብለዋል። ሩቶ ይህን የተናገሩት፤ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ወደ ኒዮርክ ከመጓዛቸዉ በፊት በሄቲ ተልዕኮ ላይ የሚገኘዉን የኬንያን 400 የፖሊስ አባላትን ፖርት ኦ ፕሪንስ ተገኝተዉ በጎበኙበት ወቅት ነዉ። ሩቶ እንዳሉት "ቀጣዩ 600 ተጨማሪ የሰላም አስከባሪ ጓዳችን ለመሰማራት ስልጠና እየወሰደ ነው፤ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ለተልዕኮ ዝግጁ እንሆናለን፤ ለስምሪቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንጠባበቃለን." ብለዋል። ፕሬዝዳንት ሩሮ በሄቲ የሚገኘዉ የኬንያ የደህንነት ድጋፍ ተልዕኮ ወደ ሙሉ የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ጓድ እንዲቀየር ፍላጎት እንዳላቸዉም ገልፀዋል። ከዚህ ሌላ ተጨማሪ መሳርያ እና የጦር ኃይሎች እንዲሰጡ ሩቶ ለሌሎች ሃገራት ጥሪ አስተላልፈዋል። በሄቲ የሚገኙ ትችት አቅራቢዎች እንደሚሉት ከሆነ፤  በሄቲ የተሰማራዉ የብዝሃ ሀገር የደህንነት ድጋፍ ተልዕኮ፤ በካሪቢያይቱ ሀገር በታጠቁ ቡድኖች ላይ ፈጣን እና ቆራጥ እርምጃ እየወሰደ አይደለም ሲሉ ይከሳሉ።  

ፍልስጤም፤ አልጃዜራ ራህማላ ላይ ያለዉ ጣብያ ተዘጋ 

የእስራኤል ጦር በፍልስጤም በምዕራብ ዮርዳኖስ ዳርቻ የሚገኘውን የአልጀዚራ የዜና ማሰራጫ ጣብያን በጊዜያዊነት መዝጋቱን አስታወቀ።  በዘገቦች መሰረት ጣብያዉ ለቀጣዮቹ 45 ቀናት ዝግ ሆኖ ይቆያል። ዋና መቀመጫውን በኳታር ያደረገዉ የአልጃዚራ ዋና መስርያ ቤት፤ እስራኤል በተቆጣጠረችው በምዕራብ ዮርዳኖስ ዳርቻ የሚያካሂደዉን እንቅስቃሴ “ወንጀል” ሲል የእስራኤል ወታደራዊ ኃይል አውግዟል። የጀርመን ጋዜጠኞች ማህበርን ጨምሮ የዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች ማህበራት የእስራኤል ወታደሮችን እርምጃ ተችተዋል።  በእንግሊዘኛ በአረብኛ እና በሌሎች ቋንቋዎች የሚያሰራጨዉ አልጃዚራ የዜና ማሰራጫ የእስራኤል ወታደሮች ትናንት እሁድ ማለዳ  በምዕራብ ዮርዳኖስ ዳርቻ ራማላ ላይ የሚገኘዉን ጣብያ ከመዝጋታቸዉ በፊት የእስራኤል ጦር ሰራዊት በአካባቢው ላይ የሚያካሂደዉን ጥቃት በቀጥታ ስርጭት እየዘገቡ እንደነበርም ተመልክቷል።  

ሱዳን ፤ በየኮሌራ ወረርሽኝ 388 ሰዎችን ሞቱ 

በሱዳን ባለፈው ነሐሴ ወር ብቻ በኮሌራ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ወደ 388 ከፍ ማለቱ ተነገረ። በእርስ በእርስ ጦርነት ዉስጥ ባለችዉ ሃገር ሱዳን እየተሰራጨ ባለዉ የኮሌራ ወረርሽኝ በአንድ ወር ብቻ   ወደ 13,000 የሚጠጉ ሰዎች መያዛቸዉን የሃገሪቱን የጤና ሚኒስቴር ጠቅሶ ፓሪስ የሚገኘዉ ሱዳን ትሪቡነ ድረገፅ ዘግበዋል። እንደ ዘገባዉ፤ የኮሌራ ወረርሽኝ በሱዳን ከሚገኙ 18 ግዛቶች በ10 ሩ ውስጥ 54 አካባቢዎችን አዳርሷል። ወረርሽኙ በእጅጉ የተስፋፋዉ ባለፈዉ ነሐሴ ወር አጋማሽ በሱዳን የጣለዉን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተከሰተዉ  የጎርፍ መጥለቅለቅ ምክንያት ነዉ። የሱዳን የጤና ዘርፍ በሀገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነት ክፉኛ ተጎድቷል። የዓለም ጤና ድርጅት ይፋ እንዳደረገዉ የሱዳን የህክምና ተቋማት 80% ከአገልግሎት ዉጭ ናቸዉ ሲልም አስታዉቋል። በሱዳን የሚታየዉን የእርስ በእርስ ጦርነት ተከትሎ ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል። አብዛኞች ተፈናቃዮች በተጨናነቁ መጠለያዎች እና የንጽህና ጉድለት ባለባቸው አካባቢዎች በመኖራቸዉ ለኮሌራ ወረርሽኝ መጋለጣቸዉ ተመልክቷል። 

ጀርመን ብራንደንቡርግ ግዛት የሶሻል ዲሞክራቶች ፓርቲ «SPD» በጠባብ ሁኔታ አሸነፈ  

ትናንት በጀርመን ብራንደንቡርግ ግዛት በተካሄደ የአካባቢ ምርጫ የሶሻል ዲሞክራቶች ፓርቲ «SPD» በጠባብ ሁኔታ አሸነፈ። የሶሻል ዲሞክራቶች ፓርቲ አባል የሆኑት የብራንድቡርግ ግዛት ጠቅላይ ሚንስትር ዲትማር ዉይ  ፓርቲያቸዉ በአስተዳደር ለመቀጠል አዲስ ጥምረት ፈጥረዉ አብላጫ ድምጽ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል። በትናንቱ ምርጫ የሶሻል ዲሞክራቶች ፓርቲ «SPD» 30,9 % ድምፅን ፤  በሁለተኛነት ደግሞ 29,2 % ድምፅን በማግኘት መጤ ጠሉ እና ቀኝ ጽንፈኛዉ ፤ አማራጭ ለጀርመን  AfD የተባለዉ ፓርቲ ቀዳሚዉን ስፍራ ይዘዋል። 13,5 % ድምፅ እና ከዝያ በታች ድምፅን ያገኙት ሌሎች ፓርቲዎች ከቀኝ ጽንፈኛዉ ፓርቲ ጋር ጥምረት መፍጠር እንደማይሹ የምርጫዉ ዉጤት እንደተነገረ አቋማቸዉን አሳዉቀዋል።  

 የመካከለኛው ምስራቅ የቀዉስ መስፋፋት ስጋት

እስራኤል በሊባኖስ እያካሄደች ያለዉ ጥቃት 'አደገኛ መዘዝ' ያስከትላል ስትል ኢራን አስጠነቀቀች። እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ የሂዝቦላ ታጣቂዎች ላይ እያካሄደችዉ ባለዉ የአፀፋ ጥቃት ቢያንስ 182 ሰዎች መገደላቸዉ ተዘግቧል። በጥቃቱ ህጻናት ሴቶች እና የህክምና ባለሞያዎችን ጨምሮ 727 ሰዎች መቁሰላቸዉን ሮይተርስ ዛሬ ከቀትር በኋላ የሊባኖስ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያወጣውን  መግለጫ ጠቅሶ ዘግቧል። እስራኤል በአዉሮጳ ህብረት ሽብርተኛ ተብሎ በተፈረጀዉ እና በሊባኖስ ከሚንቀሳቀሰዉ ከሂዝቦላህ ጥቃትን ለመመከት በሳምንቱ መጨረሻ የአፀፋ ጠንካራ ምላሽ ማካሄድዋ ተዘግቧል። ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ፤ የተለያዩ የዓለም ሃገራት፤  በእስራኤል እና በሂዝቦላ ሚሊሻ መካከል እየጠነከረ የመጣው ዉጥረት ፤ በመካከለኛው ምስራቅ የሚታየዉን ቀዉስ እንዳያሰፋ ሲሉ ስጋታቸዉን እየገለፁ ነዉ። 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።