1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ዜና፤ ሐምሌ 2 ቀን 20116 ዓ.ም

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 2 2016

DW Amharic --የ32ቱ የኔቶ አባል ሃገራት መንግሥታት እና የመንግሥታት ተጠሪዎች የሦስት ቀናት ጉባዔያቸዉን በዩናይትድ ስቴትስ ዋሽንግተን ዉስጥ ጀመሩ። --ጠ/ሚ ዶ/ር ዐብይ አህመድ በቀይባሕር ዳርቻ በምትገኘው የፖርት ሱዳን ከተማ ከጀነራል አብደል ፋታሕ አልቡርሃን ጋር ተገናኝተው ተወያዩ። --የ12ኛ ክፍል አጠቃላይ ፈተና ላይ በአማራ ክልል የሚገኙ ተፈታኞች ቁጥር ከታቀደው እንደሚያንስ የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ። --በሶማሊላንድ መካከል የሚታየዉ ዉጥረት መባባሱ ተመለከተ። የጅቡቲና የሶማሌላንድ ፕሬዚዳንቶች ለአካባቢዉ ቀዉስ አንዱ ሌላዉን እየከሰሰ ነዉ።

https://p.dw.com/p/4i4d5

ዓለም፤ ሰላማዊ ተቃውሞ መገደቡ እንዳሳዘነዉ ገለፀ

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዉ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከሰላማዊ የፖለቲካ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ የመሰብሰብ ነጻነት ገድበዋል ሲል በርካታ የአውሮጳ ሀገራትን ከሰሰ። ድርጅቱ ዛሬ በበርሊን በሚገኘዉ ጽ/ቤቱ ይፋ ባደረገዉ ዘገባ መሠረት፤ በተለያዩ የአዉሮጳ ሃገራት የሚካሄዱ ሰላማዊ የፖለቲካ ተቃዉሞዎች፤ በጨቋኝ ሕጎች፣ በአመዛኙ ደግሞ ኃይልን በመጠቀም፣ በዘፈቀደ እስሮች እና ተገቢ ያልሆኑ እገዳዎችን በመጣል የመሰብሰብ ነጻነት ተገድበዋል። ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዉ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ በዚሁ ዘገባ በጀርመን፤ በጣልያን በስፔን እና በቱርክ የሚገኙ የባለሥልጣን መስርያ ቤቶች የአየር ንብረት ተሟጋቾችን "ኢኮ-አሸባሪዎች" ወይም "ወንጀለኞች" ሲሉ እንደገለጿቸዉ ይፋ ባደረገዉ ዘገባ ላይ በምሳሌነት ጠቅሷል።  bk,ዚህ በተጨማሪ ጉዳት የደረሰባቸዉ በተጨማሪም ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች የተደራጁ ወንጀልን ለመዋጋትና ከሽብርተኝነት ጋር የተያያዙ ሕጎችን ለመጠቀም የሚያስችሉ እርምጃዎች ተወስደዋል።  እንደ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ይህን ዛሬ ይፋ ያደረገዉን ዘገባ ለማድረግ ሲዘጋጅ ጀርመንን ጨምሮ 21 የአውሮጳ ሀገራትን መርምሯል።

ዋሽንግተን፤ ኔቶ ለዩክሬን እርዳታ ለመስጠት የሦስት ቀናት ጉባዔ ዛሬ ይጀምራል 

የ32ቱ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን የኔቶ አባል ሃገራት መንግሥታት እና የመንግሥታት ተጠሪዎች የሦስት ቀናት ጉባዔያቸዉን ዛሬ ማክሰኞ ዩናይትድ ስቴትስ ዋሽንግተን ዉስጥ ይጀምራሉ። ኔቶ የተመሰረተበት  75ኛ ዓመት በሚያከብርበት በዚህ ጉባዔ ላይ፤ አባል ሃገራቱ ዩክሬን የሩስያን ጥቃት ለመከላከል በምታካሂደዉ ውጊያ ተጨማሪ ድጋፍ ለመስጠት እንደሚመክሩ ተነግሯል። ጉባዔዉ ከመጀመሩ ከቀናት በፊት አንድ የጀርመን ከፍተኛ ባለሥልጣን እንደተናገሩት፤ ዋሽንግተን ላይ በሚካሄደዉ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን የኔቶ አባል ሃገራት ጉባዔ ለኪየቭ መንግሥት በየዓመቱ 40 ቢሊዮን ዩሮ ለመስጠት ቃል የሚገባበት ነዉ ሲሉ መናገራቸዉን  የጀርመን የዜና አገልግሎት «dpa» ባለስልጣኑን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል። ኔቶ ራሱ በዩክሬን ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንደማያደርግም ተያይዞ ተዘግቧል። ዋሽንግተን ላይ ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚካሄደዉ የኔቶ ጉባዔ ዛሬ በነጬ ቤተ- መንግሥት በሚደረግ ግብዣ እንደሚጀምር ታዉቋል።  የህብረቱ ዋና ፀሐፊ ሆነዉ የሚቀርቡበት ፤ ጄንስ ስቶልተንበርግ የመጨረሻ የመሪዎች ጉባዔያቸዉ እንደሆነም ተዘግቧል። 

ጀርመን፤ የስደተኞች መጠለያ የሞተዉ ሰዉ ኢትዮጵያዊ መሆኑ ተነገረ 

በጀርመን በታችኛው ሳክሶኒ ኖርድሃይዴ ክልል ቡህሆልዝ ቀበሌ ዉስጥ በሚገኝ የስደተኞች መጠለያ ላይ ትናንት በደረሰ ፍንዳታ የሞተዉ ሰዉ ኢትዮጵያዊ መሆኑን ፖሊስ አሳወቀ።  ከኢትዮጵያ የመጣ የ28 ዓመት ጎልማሳ፤ ፍንዳታዉንም የፈፀመዉ እሱ ሳይሆን እንዳልቀረ ፖሊስ ዛሬ በሰጠዉ መግለጫ አሳዉቋል። የ 28 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ ለምን ፍንዳታዉን እንዳደረሰ እና ምን አላማ እንደነበረዉ ገና በምርመራ ላይ መሆኑን ፖሊስ በሰጠዉ መግለጫ አሳዉቋል። በፍንዳታዉ እና በደረሰዉ ቃጠሎ  20 ሰዎች ቀላል እና ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸዉ እና ኣ,ንድ ጀርመናዊ ፖሊስ ከፍተኛ ቃጠሎ ደርሶበት በሆስፒታል ክትትል እየተደረገለት እንደሆን ታዉቋል። ይሁንና ቃጠሎ የደረሰበት ፖሊስ ለህይወት አስጊ ከሚባል ሁኔታ መዉጣቱና አስተnማማኝ ጤና ዉስጥ እንደሚገኝ ተመልክቷል። ትናንት ቡህሆልዝ ቀበሌ ዉስጥ በሚገኝ የስደተኞች መጠለያ በደረሰዉ ፍንዳታ የተነሳዉን ቃጠሎ 150 የእሳት አደጋ ሰራተኞች ተሰማርተዉ እሳቱን ከጥቂት ጊዜ በኋላ በቁጥጥር ስር ማድረጋቸዉ ተመልክቷል። ፍንዳታ እና ቃጠሎ በተከሰተበት መጠለያ የተገኙት ፖሊሶች አካባቢዉ የቤንዚል ሽታ ነበር ማለታቸዉን የጀርመን የዜና አገልግሎት «dpa» ዘግቧል።

አማራ ክልል፤ የ12ኛ ክፍል አጠቃላይ ፈተና የሚወስዱ ገሚሱ ብቻ ናቸዉ

ነገ በሚጀመረው የ12ኛ ክፍል አጠቃላይ ፈተና ላይ በአማራ ክልል የሚገኙ ተፈታኞች ቁጥር ከታቀደው በግማሽ እንደሚያንስ የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ። የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ  ዶ/ር ሙሉሉነሽ ደሴ ዛሬ በጽ/ቤታቸው በሰጡት መግለጫ በዚህ ዓመት ከ 200 ሺህ በላይ ተማሪዎች ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እንደሚቀመጡ የታቀደ ቢሆንም ተፈታኞቹ ግን 96 ሺህ ብቻ ናቸው ብለዋል። ቀሪ 106 ሺህ ያህሉ ተማሪ  ደግሞ በመስከረም 2017 ዓ.ም እንዲፈተኑ እቅድ መያዙን ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡
ዓመቱን በሙሉ ትምህርት ቤቶች ዝግ እንደነበሩ የተናገሩት፤ አንድ የምዕራብ ጎጃም ዞን የፈረስ ቤት ከተማ ነዋሪ፤  ተማሪዎቹ ትምህርቱን ዘንግተውታል ሲሉ አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ ሰጥተዋል።  
በዋናነት በጎጃም ቀጠናዎች ያሉ ተማሪዎች ፈተናውን የማይወስዱ መሆኑ ተመልክቷል፣ በተመሳሳይ በቅርቡ የተሰጠው የ6ኛ  እና 8ኛ ክፍል ፈተናዎች በእነዚህ አካባቢዎች አልተሰጡም፡፡ 
 

አፍሪቃ ቀንድ ፤ በጅቡቲና በሶማሌ ላንድ መካከል አለመግባባት 

ሶማሌላንድ እና  ኢትዮጵያ ባለፈዉ ታህሳስ 22 ቀን 2016 ዓ.ም የተፈራረሙትን የመግባቢያ ስምምነት ተከትሎ በጅቡቲና  በሶማሊላንድ መካከል የሚታየዉ ዉጥረት መባባሱ ተመለከተ። በኢትዮጵያ እና በሶማሌላንድ መካከል የመግባቢያ ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ በአፍሪቃዉ ቀንድ ያለዉ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በጉልህ ለውጥ እየታየበት መሆኑም ተመልክቷል። ከቀናቶች በፊት እንደተዘገበዉ የጅቡቲና የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንቶች አካባቢዉ ላይ አለመረጋጋት እንዲፈጠር ምክንያት ሆንዋል ሲሉ እርስ በእርሳቸው መካሰሳቸዉ ተሰምቷል። የሶማሌላንድ እና የጅቡቲን መቆራቆስ ተከትሎ፤ ዛሬ የአዉሮጳ  ህብረት ኮሚሽን ቃል አቀባይ በእለታዊ መግለጫ ላይ ለቀረበላቸዉ ጥያቄ ሲመልሱ  ህብረቱ በአፍሪቃዉ ቀንድ አካባቢ የሚታየዉን አለመረጋጋት ማስወገድ ያስፈልጋል የሚል አቋም እንዳለዉ ተናግረዋል።  
«ይህን ጉዳይ በተመለከተ ማለት የምፈልገዉ ፤ የአዉሮጳ ህብረት  በአካባቢው ላይ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን እና ነገሮችን ከሚያባብሱ ነገሮች መቆጠብ እንደሚያስፈልግ ጥሪዉን እንደቀጠለ ነው። በዚህ ዓመት በጎርጎረሳዊዉ ጥር 1 ቀን በኢትዮጵያና በሶማሊላንድ መካከል የተፈረመዉን መግባንያ ስምምነት በተመለከተ ኢትዮጵያና የሶማሊያ ይህን ጉዳይ ለመፍታት በውይይት መሳተፋቸዉ የግድ ይላል። ከዚህ በተጨማሪ  በአካባቢው ላይ የሚገኙ ሌሎች ተዋናዮች ዉጥረትን በማብረድ እና በማስወገዱ ሂደት እንዲሳተፉ እንጠይቃለን።  እርግጥ ነው፣ የአዉሮጳ ህብረት ሁሉም ወገኖች በሚጠይቋቸዉ ነገሮች ሁሉ ድጋፉን ለመስጠት ዝግጁ ነው።»
በሶማሌላንድ የሉዓላዊነት ፍላጎት  ላይ የህብረቱን አቋም በተመለከተ  ለቀረበላቸው ጥያቄም፤ ቃል አቀባይዋ መልስ ሰጥተዋል።  
«ልለው የምችለው ብቸኛው ነገር፤ ለሶማሊያ  ሪፑብሊክ አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና ክልላዊ አቋም ያለንን ድጋፍ ማደስ ነው። ይህ ከህገ መንግስቱ ጋር ተያይዞ ለአፍሪቃ ህብረት ቻርተር እና ለተባበሩት መንግስታትም የሚሰራ ነዉ።  ይህም ለመላው አፍሪቃ ሰላምና መረጋጋት አስፈላጊ ነው።»

ኪይቭ፤ የህጻናት ሆስፒታል በሚሳይል ተመታ 

በዩክሬይን ዋና ከተማ ኪይቭ አንድ የሕጻናት ሆስፒታል በሚሳይል ተመታ። ለሆስፒታሉ መመታት ሩስያና ዩክሬይን እየተወነጃጀሉ ነው። የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛክሮቫ ዩክሬይን ከምድር ወደ አየር በሚምዘገዘግ ሚሳይል ኪይቭ  የሚገኝ  የሕጻናት ሆስፒታልን መትታለች ሲሉ ገልጸዋል። ስለደረሰው ጉዳት ግን ብዙ የተባለ ነገር የለም።
የዩክሬይን ባለስልጣናት በበኩላቸው ሆስፒታሉ የተመታው ከሩስያ በተተኮሰ ሚሳይል ነው ብለዋል። ባለስልጣናቱ አክለውም ሩስያ ይህን ጨምሮ ለወራት "አዘነበችው" ባሉት የሚሳይልና የአየር ድብደባ 41 ስቪሎች መገደላቸውን መግለጻቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ፖርት ሱዳን፤ አብይ አህመድ በሱዳን ከጀነራል አብደል ፋታሕ አልቡርሃን ጋር

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሱዳን ከጀነራል አብደል ፋታሕ አልቡርሃን ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውን የሱዳን የሽግግር ሉአላዊ ምክርቤት አስታወቀ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጀነራል አልቡርሃን የተገናኙት በቀይባሕር ዳርቻ በምትገኘው የፖርት ሱዳን ከተማ ነው።
የሱዳን ሉአላዊ ምክርቤት ባወጣው መግለጫ በዝግ በተካሄደው ስብሰባ ጀነራል አልቡርሃን፤  በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሐይሎች እየተፈጸመ ነው ስላሉት በሰብአዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገለጻ ማድረጋቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ መገናኛ ብዙሃን ገጻቸው "የወንድም የሱዳን ሕዝብ ችግር የኛም ችግር፤ ሰላማቸውም ሰላማችን በመሆኑ ለሱዳን ሕዝብ እፎይታና የብልጽግና ጉዞ ዛሬም እንደትላንቱ ከልብ እንሰራለን" ብለዋል።

ሩስያ፤ የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ሩስያን ለመጎብኘት ሞስኮ ገቡ 

የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ለሁለት ቀን ጉብኝት ሞስኮ ገቡ። ሞዲ በዚህ ጉብኝታቸዉ ከሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን ጋር ለዉይይት እንደሚቀመጡ ተመልክቷል። ሞዲ ሞስኮ ከደረሰ በኋላ በእንግሊዝኛ እና በሩሲያ ቋንቋ የመልካም ምኞት መግለጫ ምስሎችን በድረገጽ ላይ አካፍለዋል። ሞዲ ወደ ሞስኮ ሲጓዙ ከጎርጎረሳዉያኑ 2019 ዓ.ም በኋላ ይህ ለመጀመርያ ጊዜ መሆኑ ነዉ። ሞዲ ቀደም ሲል ወደ ሩስያ ሲመጡ በምስራቅ ሩስያ በምትገኘዉ በቭላዲቮስቶክ ከተማ ከፑቲን ጋር መገናኘታቸዉ የሚታወስ ነዉ። ሕንድና ሩሲያ ከቀዝቃዛው ጦርነት ጀምሮ ጠንካራ ትስስር የነበራቸው ሃገራት ናቸዉ። ምዕራባውያን የዩክሬን ተባባሪዎች የሞዲ መንግሥት ሩሲያን በዩክሬን ላይ እየፈፀመች ያለዉን ወረራ እንዲያወግዙ ማሳሰባቸዉ ተዘግቧል።  

 

አዜብ ታደሰ 

ፀሐይ ጫኔ 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።