1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም አቀፍ ቁንጅና ተወዳዳሪዋ ብሩክታዊት ሐብታሙ

ልደት አበበ
ዓርብ፣ መጋቢት 8 2015

ብሩክታዊት ሐብታሙ በአሁኑ ሰዓት ሚስ ካልቸር ኢንተርናሽናል በሚል ዓለም አቀፍ ባህላዊ የቁንጅና ውድድር ላይ ተሳታፊ ናት። ኢትዮጵያን ወክላ ለመወዳደር የበቃችውም «ሚስ ካልቸር ኢትዮጵያ» ተብላ ኢትዮጵያ ውስጥ የተካሄደውን ውድድር በማሸነፏ ነው። ብሩክታዊት ለዚህ ምን ያህል ዝግጁ ናት? ሰዎችስ ለምን ለእሷ ድምጫቸውን ይስጡ?

https://p.dw.com/p/4OovF
Äthiopien   Miss Culture Ethiopia
ምስል privat

የዓለም አቀፍ ባህላዊ ቁንጅና ተወዳዳሪዋ ብሩክታዊት ሐብታሙ

የ 24 ዓመቷ ብሩክታዊት ከስድስት ሳምንት ገደማ በኋላ ደቡብ አፍሪቃ ላይ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ ባህላዊ የቁንጅና ውድድር ላይ ከመሳተፏ በፊት ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ባለፈው ዓመት መወዳደር እና ማሸነፍ ነበረባት። «ምዝገባው በኢንተርኔት ነበር» የምትለው ብሩክታዊት በመጨረሻም መስፈርቱን ያሟሉ ተወዳዳሪዎች « ጥሪ ተደርጎልን ውድድሩ ተካሄደ» ትላለች። « ባህላዊ ልብሶችን ነው ለብሰን የተወዳደርነው። ውድድሩ ዓለም አቀፋዊ ስለነበር ጥያቄዎቹ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ነበሩ።  ሀገራችንን በደንብ የሚገልፅ ሰው ነበር መምረጥ የፈለጉት። » ብሩክታዊት ሌላው መስፈርት አለባበስ እንደነበር ትናገራለች።  ውድድሩ የአንድ ቀን ስለነበር የአንድ ብሔር ልብስን ብቻ መልበስ እንደቻሉ የምትናገረው ብሩክታይት እሷም የሐረር ባህላዊ ልብስን መርጣለች። « የሐረር ባህላዊ ልብስን የመረጥኩት ፍቅር ያለበት እና ሁሉም ተቻችሎ የሚኖርበት ከተማ በመሆኑ ነው» ብሩክታዊት  ይህንን ውድድር አሸንፋ ለቀጣዩ የደቡብ አፍሪቃ ውድድር «በዝግጅት ላይ ነኝ» ትላለች። ይህም በአንድ በኩል ራሷን በማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን በማስተዋወቅ ሲሆን ሌላው ደግሞ በውድድሩ ዕለት የሚያስፈልጓት ነገሮች ላይ ነው።  « ልብሶችን እያሰባሰብኩ ከብዙ ዲዛይነሮች ጋር እያወራሁኝ ነው።  ሀገራችንን የምናስተዋውቅበት ነገሮችን ይዤ ለመሄድ ጥረት እያደረኩ ነው።»
ለሚስ ካልቸር ኢንተርናሽናል ተወዳዳሪዎች በኢንተርኔት ድምፅ መስጠት ይቻላል። ለዚሁ በተዘጋጀው ድረ ገጽ ገፅ ላይ ብሩክታይት እስካሁን 1140 ድምፅ ያገኘች ሲሆን ብርቱ ተፎካካሪዋ ደግሞ ከ1700 ድምፅ በላይ ያገኘችው ኤርትራዊቷ ሄቨን ማህሪ ናት።  « እየተፎካከርን ነው። ጎረቤት ሀገራት ነን ደስ ይላል። አብዛኞቹ ሀገራት የሚፎካከሩትም አፍሪቃውያን ናቸው።»  ከሰላሳ በላይ ተወዳዳሪዎች ነን የምትለው ብሩክታይት በዚህ ድምፅ አሰጣጥ የመጀመሪያዎቹ ሶስት አብላጫ ድምፅ የሚያገኙት በውድድሩ ቢካፈሉም ከምርጥ 10 ሰዎች ውስጥ ስለሚካተቱ የድምፅ አሰጣጡ ወሳኝ እንደሆነ ትናገራለች። 
የመጀመሪያ ዲግሪዋን በአርክቴክቸር ሁለተኛ ዲግሪዋን ደግሞ በአስተዳደር ሙያ ያገኘችው  ብሩክታይት በትርፍ ጊዜዋ በአንድ የሞዴሊንግ አካዳሚ ውስጥ ሌሎች ወጣቶችን ታሰለጥናለች።  ወደዚህ ሙያ የገባችው የመጀመሪያ ዓመት የዩንቨርስቲ ተማሪ ሳለች ነው።  181 ሴንቲ ሜትር ርዘመት እና 56 ኪሎ ግራም ክብደት ያላት ብሩክታይት  መልክ እና ክብደት የግድ የውድድሩ ወሳኝ አይደለም ትላለች። « የቁንጅና ውድድር ላይ ብዙ ከውጫዊ ነገራችን ይልቅ ስብዕናችን እና ስለእዛ ነገር ያለን እውቀት ነው ሚና የሚጫወተው» ትላለች። 

ብሩክታዊት ሐብታሙ
ብሩክታዊት ሐብታሙ በአርክቴክቸር እና በአስተዳደር ሙያ ሁለት ዲግሪ አላትምስል privat

ሰዎች ለምን ለእሷ ድምፃቸውን ይስጡ?

« ኢትዮጵያን ወክዬ ነው የምሄደው። ኢትዮጵያዊ የሆነ ሰው ኢትዮጵያ በጥሩ ስሟ ሲነሳ መስማት የማይፈልግ ያለ አይመስለኝም። እግዢያብሔር ብሎ ውድድሩን ባሸንፍ ጥሩ አጋጣሚ ነው።  ኢትዮጵያን ትልቅ መድረክ ላይ ማስተዋወቅ ለእኔ ትልቅ ነገር ነው። » የምትለው ብሩክታይት በዚህ አጋጣሚ ብዙ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ አበረታታለሁ የሚል ዕምነት አላት።
የኢትዮጵያን ስም በጥሩ ማስጠራት ትልቅ ምኞቷ እንደሆነ የምትናገረው ብሩክታይት ክብደቷ ካላት እድሜ እና ቁመት ጋር ሲነፃጸር በ Body-Mass-Index  የሰውነት አቋም መዘርዝር መሰረት ዝቅተኛ ክብደት የሚባል ነው።  አብዛኛውን ጊዜ አዳሚ ወጣቶች የቁንጅና ውድድር ላይ ወይም የፋሽን መፅሔቶች ላይ የሚያያቸውን ሰዎች ቀጭን በመሆናቸው እንደነሱ ለመቅጠን በሚያደርጉት ጥረት የአመጋገብ መስተጓጎል ሲገጥማቸው ይስተዋላል።  ብሩክታይት « የውስጣችን ውበት ላይ ማተኩር ያለብን» ስትል  ለሌሎች አዳጊ ወጣቶች ትመክራለች። « ግዴታ የሆነ ሰውን መምሰል የለብንም።  ከኪሏችን እና ከቁመታችን ፣ከመልካችን ይልቅ የውስጣችን ይበልጣል የሚለው ላይ ነው ማተኮር ያለብን። »
ከ «ሚስ ካልቸር ኢትዮጵያ»  በተጨማሪ ብሩክታዊት ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት የቁንጅና ውድድሮችን አሸንፋለች።  ወደፊትም ቢሆን «በአንድ ዘርፍ ላይ  መወሰን አልፈልግም» የምትለው ወጣት ወደፊት በተማረችበት እና በዚሁ በሞዴሊንግ ስራዋ ጠንክራ መስራት እንደምትፈልግ ገልፃልናል። ለእሷ ዋናው ነገር ባህልን ከስራዋ የምታዋህድበት አጋጣሚ ማግኘት ነው። « በተለይ ከባህል ጋር የተገናኙ ነገሮች ላይ በሁለቱም ዘርፍ መስራት እፈልጋለሁ። » ትላለች። «ሚስ ካልቸር ኢትዮጵያ»  ወይም በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያን ወክላ ሚስ ካልቸር ኢንተርናሽናል ላይ የምትወዳደረው ብሩክታዊት ሐብታሙ ደምሴ።  

ብሩክታዊት ሐብታሙ
ከ «ሚስ ካልቸር ኢትዮጵያ»  በተጨማሪ ብሩክታዊት ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት የቁንጅና ውድድሮችን አሸንፋለችምስል Eyob Picture

ልደት አበበ

አዜብ ታደሰ