የዉሓ አረንጓዴ እንደምግብ
ማክሰኞ፣ ሰኔ 4 2005ይልቁንም ባለሙያዎች ለሰዉነት የሚሰጡት ጠቀሜታ እየተመዘነ እስካሁን ያልተለመዱ ለምግብነት ሊዉሉ የሚችሉ ከእፅዋትም ከሌላዉ ፍጥረት እንዳሉ እያመለከቱ ነዉ።
ከወንዝም ሆነ ሌላ የዉሓ አካል ዉስጥ ተዘርግቶ በእግር ሲረግጡትም ሲያድጥ አለያም የዉሐ ዉስጥ ፍጥረታት ሲንቀሳቀሱበት ብዙዎች ያዉቁታል። ለምግብነት ግን እዚያዉ ዉሓዉ ዉስጥ ያሉት ካልሆኑ በቀር ሰዉ ምን በዉስጡ እንደያዘ ሳይሰማለት ቆይቷል። የዉሐ አረንጓዴ ወይም አልጌ ዉሓ ዉስጥ የሚበቅል እና የሚራባ ከእፅዋት ዘር የሚመደብ ነዉ። የተለያየ ዓይነት እንዳለዉ የሚታወቀዉ ይህ የዉሃ ዉስጥ ተክል በተለይ ጨዋማ በሆነ ሐይቅ ዉስጥ በብዛት እንደሚገኝ የተገለፀዉ አንዱ ዘር የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ሊታደግ እንደሚችል ጥናቶች ያመለክታሉ።
ቴልአቪቭ እስራኤል ዉስጥ የአንድ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን የቤተ ሙከራ ምርምር የቃኘ አንድ ዘገባ፤ ባለንበት በ21ኛዉ ክፍለ ዘመን የሚራቡ እና በቂ ምግብ የማያገኙ ሕፃናት መኖራቸዉ የታዳጊ ተማሪዎቹን መንፈስ ለምርምር ማነሳሳቱን ያመለክታል። ስፒሩሊና የተሰኘዉ የአልጌ ዘር በጥናት እንደተደረሰበት በተፈጥሮዉ በተለያዩ ንጥረነገሮች የበለፀገ ነዉ። በኢትዮጵያ ጤናና ስነምግብ ምርምር ተቋም በምግብ ሳይንስና ስነምግብ ተመራማሪ አቶ ጥበቡ ሞገስ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች እየተከሰተ የሚታየዉን የምግብ እጥረት በማሰብ ለሰዉ ልጅ ምግብ ሊሆኑ የሚችሉ ተክሎችም ሆኑ ሌሎች ፍለጋ የተጀመረበት ሁኔታ መኖሩን ይገልፃሉ።
ባለሙያዉ እንደሚሉት ለሰዉነታችን የሚያስፈልጉ አብዛኞቹ አሚኖ አሲድ የሚባሉት ንጥረነገሮች በዚህ በስፒሩሊና አልጌ ዉስጥ በብዛት ይገኛሉ። ከዚህ ሌላ ደማችን ዉስጥ የስኳርና የስብን/ኮለስትሮል/ መጠን ሊቆጣጠሩ የሚችሉ ንጥረነገሮችንም በሚገባ የያዘ ነዉ። ይህን አስመልክቶ የተመ የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት FAO ከአራት ዓመታት በፊት ያወጣዉ ዘገባ በዱቄትነት የተዘጋጀ 10 ግራም ስፒሩሊና አልጌ በቀን ለአንድ በተመጣጠነ የምግብ እጥረት ለተጎዳ ሕፃን በተጨማሪ ምግብነት ቢሰጥ ፈጣን ለዉጥ እንደሚያስገኝ ያብራራል።
የተመድ ባለፈዉ ጥቅምት ወር ይፋ ባደረገዉ ዘገባ መሠረት ባለፉት ሁለት ዓመታት ወደ870 ሚሊየን ሕዝብ፤ ወይም ከስምንት ሰዎችን አንዱ የተመጣጠነ ምግብ በማጣት የተጎዳ ነዉ። የዓለም የጤና ድርጅት በበኩሉ የተመጣጠነ ምግብ እጦት የሚከሰተዉ አንድም ለሰዉነት በቂ ምግብ ባለማግኘት፤ አንድም ለሰዉነት በሚጠቅም መልኩ የተመጣጠነ ምግብ ባለመመገብ እንደሆነ ያመለክታል። የተመጣጠነ ምግብ እጦት በሕፃንነት ሕይወትን ከመቅጠፉ በላይ በአካል ላይ በሚያስከትላቸዉ ለዉጦች የኑሮ ሁኔታን እንደሚያናጋ ባለሙያዎች ያመለክታሉ። የተመ የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት በዘንድሮዉ ጎርጎርዮሳዊ ዘመን ባወጣዉ ዘገባ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መኮሰስና አጥንት መግጠጥ ብቻ ሳይሆን መጠን ላጣ ዉፍረትም የሚዳርግ እንደሆነ ነዉ የገለፀዉ። የዉሃ አረንጓዴ ወይም አልጌ ዓይነቶቹ በርካታ ናቸዉ። ሁሉም ግን ለምግብነት አይሆኑም፤ የተጠቀሰዉ ዘር ብቻ እንጂ። ኢትዮጵያ ዉስጥ በስምጥ ሸለቆ አካባቢ ሊገኙ እንደሚችሉ ያመለከቱት በኢትዮጵያ ጤናና ስነምግብ ምርምር ተቋም በምግብ ሳይንስና ስነምግብ ተመራማሪ አቶ ጥበቡ ሞገስ ስፒሩሊና ላይ ጥናት ቢደረግ እንደሚያዋጣ ይጠቁማሉ፤ ስፒሩሊና ከሶስት ሚሊዮን ዘመን በላይ ማስቆጠሩንም መረጃዎች ያመለክታሉ።
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ