1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወለንጪቲ ግጭትና ኦሮሚያ ፀጥታ ስጋት

ሐሙስ፣ ግንቦት 10 2015

ወለንጪቲ ወይም ኦላንጪቱ ከተማ ባለፈዉ ማክሰኞ የመንግስት ፀጥታ አስከባሪዎችና አማፂያን ባደረጉት የተኩስ ልዉዉጥ 2 ሰላማዊ ሰዎችና 6 አማፂያን መገደላቸዉን የአካባቢዉ ባለስልጣናት አስታወቁ።የቦሰት ወረዳ የፀጥታ ባለስልጣናት እንዳሉት መንግስት ኦነግ-ሸኔ በሚል በአሸባሪነት የፈረጀዉ አማፂ ቡድን የከተማይቱን ፖሊስ ጣቢያ ለመምታት አቅዶ ነበር

https://p.dw.com/p/4RY2J
Äthiopien | Wahlen | Oromia

«2 ሰላማዊ ሰዎችና 6 አማፂያን ተገደሉ» ፖሊስ

                             
ኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ ወለንጪቲ ወይም ኦላንጪቱ ከተማ ዉስጥ ባለፈዉ ማክሰኞ የመንግስት ፀጥታ አስከባሪዎችና አማፂያን ባደረጉት የተኩስ ልዉዉጥ 2 ሰላማዊ ሰዎችና 6 አማፂያን መገደላቸዉን የአካባቢዉ ባለስልጣናት አስታወቁ።የቦሰት ወረዳ የፀጥታ ባለስልጣናት እንዳሉት መንግስት ኦነግ-ሸኔ በሚል ስም በአሸባሪነት የፈረጀዉ አማፂ ቡድን ታጣቂዎች የከተማይቱን ፖሊስ ጣቢያ ለመምታት አቅደዉ ነበር።ከአዳማ ወይም ናዝሬት 30 ኪሎ ሜትር ግድም በምትርቀዉ ወለንጪቲና አካባቢዋ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ ጥቃት ያደርሳሉ።ታጣቂዎች ባለፈዉ ዕሁድ ቢሸፍቱ ከተማ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ላይ በከፈቱት ጥቃት ሰዎች መገድለዋቸዉ ተዘግቧልም።
 ባለፈው እሁድ እኩለ ለሊት ሰርድስት ሰዓት ገደማ በቢሾፍቱ ከተማ ማንነታቸው ያልተገለጸ ታጣቂዎች በአንድ የከተማዋ ፖሊስ ጣቢያ ላይ ከፈቱ በተባለ ጥቃት የሰዎች ህይወት ማለፉን ለደህንነታቸው የሰጉ የአከባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ በዚህ ላይ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ለከተማዋ ከንቲባ፣ ለከተማዋ ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ እና ለከተማዋ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊዎች በተደጋጋሚ ያቀረብነው ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ ጥረቱ አልሰመረም፡፡
ያንኑን ተከትሎም ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ ግንቦት 08 ቀን 2015 ዓ.ም. ከቀኑ 11 ሰኣት ገደማ ከአዳማ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ኦላንቺቲ ከተማ ላይ የመንግስት የፀጥታ ኃይላት ከታጠቁ አካላት ጋር የተውክስ ልውውት ማድረጋቸው ተሰምቷል፡፡ ይህን ግጭት በማስመልከት ለዶቼ ቬለ አስተያየታቸውን የሰጡት የቦሰት ወረዳ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ሞሃመድ ሱፋ በዚህ የተውክስ ልውውጥ መንግስት ሸነ በሚል ስያሜ በሽብርተኝነት የፈረጀውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን በከፈተው ተውክስ ሁለት ሰላማዊ ሰዎች በከተማው ውስጥ መገደላቸውን ተናግረዋል፡፡ “በዚህ አከባቢ ያለው ችግር አንዳንድ የኦሮሚያ ክልል አከባቢዎች እንደሚስተዋለው ኦነግ ሸነ የተባለው ታጣቂ ሃይል እዚህም አልፎ አልፎ ይንቀሳቀሳል፡፡ ሰሞኑን በከተማችን ላይ የተከፈተውም ተውክስም በዚሁ ኃይል እና በመንግስት የፀጥታ ኃይል መካከል የተፈፀመ ነው፡፡ የፀጥታ ችግሩ እየተባባሰ ነው የሚል ግምት የለንም፡፡ መንግስት እርምጃ ወስዶ የማስታገስ አቅም አለው በውስን ቀናት ደግሞ ይህን ያደርጋል፡፡  እነዚህ ታጣቂዎች ሸማቂ እንደመሆናቸው የሽፍታ አካሄድ ነው የሚሄዱት፡፡ ማህበረሰቡን እየገደሉ እያስፈራሩ እየመሸጉባም ከማህበረሰቡ በቀላሉ ለይቶ ማስወገድ ፈታኝ ነው፡፡ አሁንም ማህበረሰቡን መስለው ከተማ ውስጥ ገብተው የመንግስት አመራሮችን እና ተቋማትን እላማ አድርገው ለመምታት ሲንቀሳቀሱ ነበር የሞከሩት እንጂ ፈጽሞ ከመንግስት አቅም በላይ አልሆኑም፡፡ መንግስት አሁንም ከህብረተሰቡ ጋር ምክክር በማድረግ ከህዝቡ ሊለያቸው በቀስታ እየሄደ ባለበት ነው አሁን እነሱ በዚህ መንገድ ተጠቅመው ከተማውን ለመምታት የሞከሩት፡፡ ምናልባት ይህን ያደረጉት ወይ ለዝርፊያ አሊያም ትኩረት ለመሳብ ነው የሚል ግምት አለን፡፡”
የቦሰት ወረዳ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ሞሃመድ ሱፋ አክለው እንዳሉት  “በስፋት በወረዳው የሚንቀሳቀሰው የኦነግ ሸነ ኃይል ከተማዋን ለመምታት ተደጋጋሚ ጥረቶችን ያደርጋል፡፡’’ በማክሰኞው የተውክስ ልውውጥ ከታጣቂዎቹ ስድስት ሰዎች ተገድለው አራቱ መያዛቸውን ነው ይህ የአከባቢው ባለስልጣን የገለጹት፡፡ 
በኦላንጪቲ የነበረው የታጣቂዎች ጥቃት ከ30 ደቂቃ ያበለጠ ነው ያሉት እኚህ ባለስልጣን፤ የጥቃቱ ዓለማም በከተማው ፖሊስ ጣቢያ የሚገኙ በቁጥጥር ስር ያሉትን ታሳሪዎች ለማስለቀቅ ነበር ብለዋል፡፡ ይሁንና በአከባቢው የነበረው የመከላከያ ሰራዊት አባልም እርምጃ በመውሰዱ ታጣቂዎቹ ወደ ፖሊስ ጣቢያው ዘልቀው መግባት አለመቻላቸውን ባለስልጣኑ ተናግረዋል፡፡ 
“በዚህ አጋጣሚ የደረሰው ጉዳት በተለይም ከታጣቂዎቹ ወደ ከተማው በተተኮሱ ተኩሶች ሁለት ሰላማዊ ሰዎች መሞታቸው ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በሰላም ንግዳቸውን ሲያከናውኑ የነበሩ ሱቅ ውስጥ የነበሩ ናቸው፡፡ ከምንም ነጻ የሆኑ ሰላማዊ ሰዎች መሞታቸው አሳዛን ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የፖሊቲካ አመራርም ሆነ የፀጥታ አስከባሪ አካል አላለፈም፡፡ ከዳገቱ ሆነው ወደ ከተማ ተኩሰው የገደሉት ሰላማዊውን ሰው ነው፡፡”
ባለስልጣኑ በታጣቂዎች ላይ ደርሷል ስላሉት የአካል ጉዳት እና በመንግስት ወገን ጉዳት መድረስ አለመድረሱን ከገለልተኛ አካል ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ በዚህ ከመዲናዋ አዲስ አበባ ወደ ምስራቅ የአገሪቱ የተለያዩ አከባቢዎች በሚወስደው ኦላንጪቲ እና አከባቢው ተደጋጋሚ የፀጥታ ስጋቶች መከሰታቸው ግን በተደጋጋሚ ተሰምቷል፡፡ በቅርቡም አንድ የአፋር ክልል ባለስልጣናት ከወንድማቸው ጋር በዚሁ አከባቢ በጥይት ተደብድበው መገደላቸውን መዘገባችንም አይዘነጋም፡፡ የአከባቢው የፀጥታ ጉዳይ ባለስልጣኑ ግን ይህን ጥቃት የሚፈጽመው ጫካ ለጫካ የሚሄድ ያሉት ታጣቂ መሆኑን ገልጸው መንግስታቸው ስጋቱን እንደሚያስወግድ አመልክተዋል፡፡
“ይህ ሽፍታ ሃይል አሁንም እደረገ ያለው ይህ መንግስት አቅም የለውም የሚለውን መልእክት ለማስተላለፍ ነው፡፡ ከጫካ ውስጥ እየወጡ በለሊት አሽከርካሪን እየዘረፉ ይዟቸውም እየሄዱ ገንዘብ ይጠይቃሉ፡፡ ሰላማዊውን ሰው ነው እንዲህ የሚሰቃዩት፡፡ ያ የሚታገተው ሰው ሊኖረው የማይችል ገንዘብ ሁሉ ነው የሚጠየቀው፡፡ ከግማሽ እስከ አንድ ሚሊየን መጠየቅ፡፡ ይህ በየትኛውም ኣለም ባለው ሽፍታ የሚከወን ተግባር ነው፡፡”
ኦላንጪቲ ከተማ አሁን ላይ ሰላማዊ ሁኔታ ውስጥ እንደምትገኝና በዚሁ ወደ ምስራቅ የአገሪቱ አከባቢዎች የሚያልፉ የትራንስፖርት ፍሰትም በመደበኛ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ባለስልጣኑ አብራርተዋል፡፡ 
በተመሳሳይ ሁኔታ ከዚህ በፊት በተያዘው ዓመት ታህሳስ ወር መጨረሻ (ታህሳስ 29 ቀን 2015 ኣ.ም.) ምዕራብ ጉጂ ዞን ቡሌ ሆራ ከተማ ውስጥ ታጣቂዎች በማረሚያ ቤት ላይ ጥቃት ከፍተው በወቅቱ ከ400 በላይ እስረኞች ማስለቀቃቸውን የአይን እማኞችን ዋቢ አድርገን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በኢትዮጵያ መንግስት እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል በቅርቡ ሰላማዊ ድርድር በታንዛኒያዋ ዛንዚባር ደሴት መካሄዱን ተከትሎ የመረዳዳት እና ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት አዝማሚ ተስተውሎ ነበር፡፡ ይሁንና ምክክሩ ያለ ተጨባጭ ስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ በኦሮሚያ በተለያዩ አከባቢዎች ግጭት መቀጠሉ እየተሰማ ነው፡፡
የኦሮሞ ነጻ አውጪ ሠራዊት  ትናንት ባወጣው መግለጫም የመንግሥት ኃይሎች በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች መጠነ ሰፊ ጥቃት ከፍተውብኛል ብሏል። የቡድኑ ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ በትዊተር ገጻቸው ያጋሩት የቡድኑ መግለጫ፤ የታንዛኒያው የሰላም ውይይት ከተጠናቀቀ በኋላ በበርካታ አካባቢዎች የመንግሥት ኃይሎች ጥቃት እንደከፈቱበት አመልክቷል። እንዲህ ያለው እርምጃም በሰላም ውይይቱ ግጭትን ለመቀነስ የተደረሰባቸውን የመግባቢያ ሃሳቦች በእጅጉ የሚጻረር ብሆንም፤ ታጣቂ ቡድኑ ለሰላም ካለው ቁርጠኝነት ባሻገር በምዕራብ ወለጋ፣ በምሥራቅ ወለጋ፤ በሆሮ ጉድሩ፤ በምዕራብ ሸዋ፣ በምሥራቅ ሸዋ፣ በአርሲ፣ በሐረርጌ፣ ቦረና እና ጉጂ ይዞታዎቹን ለመከላከል መገደዱንም አመልክቷል። ቡድኑ በመግለጫው አክሎም በአሁኑ ጊዜ የተከፈተበትን ጥቃትም  ለሁለተኛው ዙር ውይይት የበላይነት ይዞ ለመቅረብ ያለመ ነው ብሎታል። እንዲያም ሆኖ በመንግሥትና በቡድኑ መካከል ሁለተኛ ዙር ውይይት መቼ እንደሚካሄድ እስካሁን የተባለ ነገር የለም። ታጣቂው ቡድን ያሰማውን ክስ በተመለከተ ከመንግሥት በኩል መረጃ ለማግኘት ዶይቼ ቬለ ለመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ባለስልጣናት ብደውልም ስልካቸው ባለመነሳቱ አስተያየታቸውንም ማካተት አልተቻለም፡፡

ስዩም ጌቱ

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ