1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ዳግም ስጋት

ማክሰኞ፣ መስከረም 19 2013

የኮሮና ወረርሽኝ ዓለም ላይ መርጉን ከጫነ ከ7 ወራት በላይ አለፉ። ተሐዋሲውን ለመከላከል የሚያስችል ክትባት የመፈለጉ ጥረት ቢካሄድም የሁሉን ልብ የሚያሳርፍ ውጤት ገና አልተጨበጠም። ከመፍትሄው በተቃራኒ አሁን ከጥቂት ወራት በፊት የኮሮና ተሐዋሲን ስርጭት መቀነስ ተሳክቶላቸው የነበሩ አውሮጳውያን ሃገራት ሁለተኛው ዙር የወረርሽኙ ስጋት አለ።

https://p.dw.com/p/3jB9S
Sars-CoV-2 Illustration
ምስል Reuters/NEXU Science Communication

«የኮቪድ ክትባት ፍለጋና ተስፋው»

«አሁን ሁሉም ነገር መልካም ነው፤ ምን የሚያሰጋ ነገር ሊኖር ይችላል? ዉሃን መጀመሪያ ወረርሽኙ የተቀሰቀሰባት ስፍራ ነች፤ በአግባቡ በቁጥጥር ሥር ውሏል ብዬ አምናለሁ።» የሚለው የ37 ዓመቱ የፋብሪካ ሠራተኛ እና የዉሃን ከተማ ነዋሪ ሺ አሊያንግ ነው።  የኮሮና ተሐዋሲ የመጀመሪያ መገኛ ተደርጋ የምትጠራው የቻይናዋ ዉሃን ግዛት አሁን ከወረርሽኙ ተላቃ እፎይ ብላለች። አፍና አፍንጫቸውን በጭንብል ያልሸፈኑ በሺህዎች የሚገመቱ ዜጎች የታደሙባቸውን የአደባባይ ላይ የሙዚቃ ድግሶችም ሆኑ ሌሎች ዝግጅቶችን ዳግም ወደማስተናገዱ ተመልሳለች። በተቃራኒው የስፔን ዋና ከተማ ማድሪድ ባለፈው ሳምንት ከፊል የእንቅስቃሴ እገዳ ጥላለች። የተለያዩ የአውሮጳ ሃገራትም በየዕለቱ በኮሮና ተሐዋሲ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመር ለሁለተኛው የወረርሽኙ ማዕበል እያዘጋጃቸው እንዳይሆን የሚል ስጋት ይነገርባቸዋል። የመድኃኒት ሙከራና የክትባት ፍለጋውም ቀጥሏል።

የዓለምን ሕዝብ ባለጸጋ ከምንዱባን ሳይለይ፤ ሰሜንም ሆነ ደቡብ ዋልታ ሳይገድበው ከኮሮና ተሐዋሲ ያስተዋወቀችው የቻይናዋ ዉሃን ከተማ ዛሬ የወትሮ ድባቧ ተመልሷል ይሏታል ያዩ የጎበኟት። ተሐዋሲው ጥቁር ከነጭ፣ ባለዘመናዊ የጤና ሥርዓት ከኋላ ቀር ሳያበላልጥ በመላው ዓለም የቀጠፈው የሰው ልጅ አንድ ሚሊየን ደርሷል። በሽታው ከምድሯ ወጥቶ የተዛመተባቸው ሃገራት ዛሬም ከሙት እና ታማሚያቸውን  ሲቆጥሩ ዉሃን እጇን እንደጲላጦስ ተጣጥባ የወትሮ የኑሮ ስልቷን መጀመሯ እየተነገረ ነው።

«ውሃን ዳግም አንሠራርታለች። ሕይወት ለወትሮ ወደምናውቀው ጣዕሙ ተመልሷል። እናም በዉሃን የሚኖር ማንኛውም ሰው አሁን እፎይታ ይሰማዋል።»

የሚሉት የከተማዋ ነዋሪ እና የመገናኛ ብዙሃን ሠራተኛ የሆኑት ወይዘሮ ናቸው። እውነት ነው፤ በወረርሽኙ ምክንያት ሚሊየኖች ከየቤታቸው እንዳይወጡ እገዳ በተጣለባቸው ባለፈው ዓመት የሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የክረምት ወራት ማለትም ከኅዳር ወር አንስቶ ባሉት ቀዝቃዛ ቀናት ከተማ የሙታን መንደር መስላ ነበር። በወቅቱ ተሐዋሲው በከተማዋ የመዛመቱን ስጋት ይፋ ያደረጉት ዶክተር ሊ ዌንሊያንግ ቢሆኑም መንግሥት በፍጥነት መረጃውን እንዳፈነ ነው የሚነገረው። የእሳቸውንም ሕይወት ሳይንቲስቶች ኮቪድ 19 በማለት ስያሜ ያወጡለት ተሐዋሲ ቀጠፈው። ከእሳቸው ሕልፈት በኋላም ዓለም በርካቶችን ባልተለመደ መልኩ ወደመቃብር ሸኝቷል። መነሻው ላይ ቻይናውያን ችግሩ እንዲህ ይከፋል ብለው ስላልገመቱ ተገቢውን ጥንቃቄ ባለማድረግ ብዙዎች መርገፋቸውን ውሃን ከተማ የተወለዱት ቻይናዊው ተመራማሪ ሁ ሊንግኳን ይናገራሉ።

China Filmstill aus "Coronation von Ai Weiwei: Lightshow über dem nächtlichen Wuhan
ምስል Ai Weiwei Studio

«ከቻይና አኳያ ብንመለከተው ጥሩ ነገር አላደረጉም። ምናልባትም ጉዳዩ ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ አልተረዱት ይሆናል። እናም ያኔ ውሃን ውስጥ በርካቶች በዚህ ምክንያት ይህቺን ዓለም ተሰናብተዋል። ተሐዋሲው አስፈሪ ነው።»

የመገናኛ ብዙሃን ባልደረባዋም ተመሳሳይ ግምት ነው የሚያነሱት፤ ምናልባት ተሐዋሲው ዓለም እንዲህ ይከድናል ብሎ የገመተ አልነበረም የሚል።

«ምናልባት እያንዳንዱ ሀገር እንዲሁም እኛ የውሃን ነዋሪዎችን ጨምሮ ተሐዋሲው እንዲህ በመላው ዓለም ወረርሽኝ ሆኖ ይከሰታል ብለን አልገመትንም ነበር። ያኔ ይህን እኔ በፍፁም አላሰብኩም።»

ዛሬ ውሃን ጣጣዋን ረስታ ጎዳናዋ በሰዎች ተሞልተው፤ መዝናኛ ስፍራዎችም አፍና አፍንጫቸውን ባልሸፈኑ ሰዎች ተጨናንቀው ሲታዩባት፤ «ታሞ የተነሳ,,,,  የሚለውን ትዝብት ታስታውሳለች። አንዳንዶችም ያኔ ዓለም አቀፍ ውግዘትን እንዳላስከተለ፤ የኮሮና ተሐዋሲን የመቆጣጠር ስልት ከቤጂንግ ተማሩ ይሉላት ጀምረዋል።

ባለፈው የካቲት እና መጋቢት ወር አንስቶ ባሉት ተከታታይ ወራት ተሐዋሲው ካደረሰባቸው ከፍተኛ ጫና ለጥቂት ወራት እፎይ ብለው የሰነበቱት የአውሮጳ ሃገራት አሁን ስጋት እየተሰማባቸው ነው።  በተለይም ስፔን፤ ፈረንሳይ፤ ብሪታንያ፣ ፖላንድ እና ኔዘርላንድስ ለሁለተኛው የኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝ እየተዘጋጁ መሆኑ እየተነገረ ነው። ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ፈረንሳይ 16,096 አዲስ በተሐዋሲው የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን ይፋ አድርጋለች። ኔዘርላንድስም እንዲሁ እሁድ ዕለት ብቻ ሦስት ሺህ አዳዲስ ታማሚዎችን መዝግባለች። ምሥራቅ አውሮጳ የሚገኙት አልባኒያ፤ ቡልጋሪያ፤ ቼክ ሪፑብሊክ፤ ሞንቴኔግሮ፤ እንዲሁም ሰሜን መቄዶኒያ በቀደሙት ወራት ባላዩት መጠን ካለፈው ነሐሴ ወር ወዲህ በየግላቸው በርካታ በኮሮና የተያዙ ሰዎችን እያስታመሙ ነው።  ስፔን ባለፈው ሳምንት ሰኞ በይፋ በዋና ከተማ ማድሪድ ሕዝብ በርከት ብሎ በሚኖርባቸው የከተማው ክፍሎች የእንቅስቃሴ ገደብ ጥላለች። በዚሁ ሳምንትም በሀገሪቱ በተሐዋሲው የተያዙ ሰዎች ቁጥር በ14 ሺህ ከፍ ብሏል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ጀርመን ውስጥም ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ከ24 ሺህ በላይ አዲስ የታማሚዎች ቁጥር ተመዝግቧል።

China Filmstill aus "Coronation von Ai Weiwei: Krankenhaus-Schwestern in Schutzkleidung
ምስል Ai Weiwei Studio

 በየዕለቱ በዚህ ጉዳይ ላይ አዳዲስ መረጃ ይፋ የሚያደርገው የአሜሪካኑ ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ እንደሚለው በመላው ዓለም በተሐዋሲው የተያዙት ቁጥር ከ33 ሚሊየን ሦስት መቶ ሺህ በልጧል። ከበሽታው ያገገሙት ደግሞ ከ23 ሚሊየን አንድ መቶ ሺህ አልፈዋል።

የዓለም የጤና ድርጅትም ሆነ የተለያዩ የዘርፉ ምሁራን እንደሚሉት ኮቪድ 19 በቀላሉ ከምድረ ገፅ ይወገዳል ተብሎ የሚታሰብ ተሐዋሲ አይደለም። እናም እነሱ እንደሚሉት ሰዎች በቂ የጥንቃቄ ርምጃዎችን እየተወሰዱ አፍና አፍንጫን የመሸፈን፤ እጅንም በቀን ውስጥ በተደጋጋሚ በመታጠብ እንዲሁም ሰዎች በሚበዙበት ስፍራ ርቀትን በመጠበቅ ከበሽታው ጋር ላልተወሰነ ጊዜ መኖር ግድ ነው። በዚህ መሃል በሀገሩ የክትባት ዝግጅቶች እንደሚደረጉ ይነገራል።

በተለይም ለቻይና አሁን ጊዜው ተሐዋሲውን የመመርመሪያ ቁሳቁስ አምርቶ ለገበያ ፤ ክትባትም ቀምሞ ለፈላጊዎች የማቅረብ ሆኗል። ባለፈው ሳምንት እንደተሰማው ቻይና ካሳለፍነው ሐምሌ ወር አንስታ በመቶዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ያዘጋጀችውን ክትባት በመሞከር ሥራ ተጠምዳለች። ሲኤን ኤን እንደዘገበውም ቤጂንግ ለምታዘጋጀው የኮሮና ተሐዋሲ መከላከያ ክትባት የዓለም የጤና ድርጅትን አዎንታዊ ድጋፍ አግኝታለች። በምዕራቡ ዓለም ጥቂት የማይባሉ ባለሙያዎች እና የክትባት ቀማሚዎች በበኩላቸው ክትባቱ የመጨረሻ ደረጃ ፍተሻ ሳይደረግለት ቤጂንግ በሰዎች ላይ የምታካሂደው የክትባት ሙከራ ተገቢ እንዳልሆነ ያሳስባሉ። ጀርመን ቢዘገይ እስከመጪው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት አጋማሽ ሥራ ላይ አውለዋለሁ ያለችውን ክትባት እያዘጋጀት መሆኗን ይፋ አድርጋለች። የሀገሪቱ የጤና ሚኒስትር የን ስቴፋን ቢያንስ ከጠቅላላው ሕዝብ ከ55 እስከ 65 በመቶው እንኳ ይህን ክትባት ከወሰደ ይበቃል ነው ያሉት። እንዲያም ሆኖ አንዳንድ የሕዝብ አስተያየት መመዘኛዎች እንደሚያሳዩት ጀርመን ውስጥ ከሦስቱ አንዱ ሰው ክትባቱን ለመውሰድ ፈቃደኛ አይመስልም።

ወረርሽኙ በመላው ዓለም የአንድ ሚሊየን ሰዎች ሕይወት መቅጠፉን አስመልክቶ በዛሬው ዕለት በተለይ ከዶቼ ቬለ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የዓለም የጤና ድርጅት ቃል አቀባይ ዶክተር ማርግሬት ሃሪስ አደገኛ ያሉትን ተሐዋሲ ለመከላከል ዓለም በአንድነት መንቀሳቀስ እንደሚገባው አሳስበዋል። ተሐዋሲው ለሰው ልጆች ከፍተኛ ስጋት መሆኑን እያንዳንዱ ሰው መረዳት እንዳለበት በማመልከትም ጉዳዩ የፖለቲካም ሆነ የአንድ ቡድን በሌላው ላይ የመነሳት ነገር እንዳልሆነ በመጥቀስ፤ ወረርሽኙ ስጋትነቱ የሚያበቃው ሁሉም በአንድነት ሲቆም መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል። በርካታ ክትባቶች እየተዘጋጁ መሆኑን በመጥቀስ መቼ አስተማማኝና ውጤታማ ክትባት ይቀርባል የሚል ጥያቄ ከዶቼ ቬለ የቀረበላቸው ዶክተር ማርግሬት ሃሪስ በሰጡት ምላሽ ጊዜ እንደሚፈልግ ጠቁመዋል።

USA New York Coronavirus Krankenhäuser
ምስል picture-alliance/Zumapress/U.S. Navy/S. Eshleman

«በርካታ ክትባቶችን ከማዘጋጀት ጋር አስተማማኝ ደረጃ ላይ ነን። ሦስተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ ማለትም ግማሹን በሰው ላይ የሚሞከር ዘጠኝ አሉን። እነዚህም በመሠረቱ ወደኅብረተሰቡ እንዲወጡ ተደርገዋል። እናም በትክክል ይከላከል እንደሆነ ይታያል። ይህን እያደረክም አስተማማኝነቱን እጅግ በቅርበት መከታተል ይኖራል። እናም አስፈላጊው ነገር መረጃ ማሰባሰቡ እና በእርግጥ አስተማማኝ ነው የሚለው አስቀድሞ ይታያል። ከዚያም እንበትነዋለን። ነገር ግን ይህን መረጃ እስከያዝነው ዓመት መጨረሻም ሆነ አዲሱ ዓመት መጀመሪያ ድረስ ማግኘት አንችልም። እርግጥ ነው የማዳረሱ ነገር አሁንም ጊዜ ይወስዳል። ሆኖም ገባህ፤ የሚታዩት ነገሮች በጣም ጥሩ ናቸው።»

ሌላው ከዚሁ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ የሚነገረው ቀናት የሚወስደው የምርመራ ውጤት ነው። ካለፉት ጥቂት ሳምንታት ወዲህ ግን በደቂቃዎች ውስጥ አስተማማኝ የምርመራ ውጤት ማሳየት የሚችሉ መመርመሪያዎች መገኘታቸው ተሰምቷል። ጀርመን ውስጥ የተዘጋጀው በ10 ደቂቃ የኮሮና ተሐዋሲ ምርመራ ውጤትን ማሳወቅ የሚያስችል አዲስ መመርመሪያ ሙከራ ላይ ውሏል። በሙከራው ኦስትሪያ ውስጥ ወደ 3000 ተማሪዎች የተሳተፉበት ምርመራ የተካሄደ ሲሆን ውጤቱ 99 በመቶ አስተማማኝ መሆኑ ነው የተገለጸው።

ሸዋዬ ለገሠ 

ኂሩት መለሰ