1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትአውሮጳ

የኮሮና ተፅዕኖ በጀርመን ወጣቶች ላይ 

ልደት አበበ
ዓርብ፣ የካቲት 5 2013

ጀርመን ውስጥ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የሚጣሉት ገደቦች በተለይ በወጣቱ ኑሮ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳረፉ ነው። ተማሪዎች የሚያመልጣቸውን ትምህርት እና ስነ ልቦናዊ ጉዳት በቀላሉ የሚካካስ አይደለም ይላሉ ባለሙያዎች። የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ገደቡወይም ሎክዳውን በጀርመን ወጣቶች ላይ ባሳረፈው ተጽዕኖ ላይ ያተኩራል።

https://p.dw.com/p/3pGWx
Symbolbild I Homeschooling im Lockdown
ምስል K. Schmitt/Fotostand/picture alliance

የኮሮና ተፅዕኖ በጀርመን ወጣቶች ላይ 

ለወትሮው ብዙ የመዝናኛ አማራጮች ያሏቸው የጀርመን ወጣቶች በኮሮና ገደብ ምክንያት እቤት መዋል ከጀመሩ ሰነባበቱ።  የስፖርት ማጠዉተሪያዎች፣ ቲአትር፣ሲኒማ ፣ ጭፈራ ቤቶችናመሰል መዝናኛዎች  እንደተዘጉ ነው። በየሱቁ ተዘዋውረው የሚፈልጉትን ነገር እንኳን መግዛት አልቻሉም።  በተለይ ህፃናት እና ወጣቶች በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት ከፍተኛ ስነ ልቦናዊ ጫና እየገጠማቸው እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ፓውል የ10ኛ ክፍል ተማሪ ነው። በአሁኑ ወቅት ትምህርቱን ከቤቱ ሆኖ ለመከታተል ተገዷል። ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት አንስቶ እስከ ከሰዓት 10 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ መምህራኑ በቪዲዮ የሚሰጡትን ትምህርት ይከታተላል ወይም የቤት ስራውን ይሰራል። ሁኔታን ቢለምደውም በኮሮና  ጓደኞቹን በአካል ማግኘት አለመቻሉ በጣም ያበሳጨዋል። ይህ ብቻ አይደለም። «ዛሬ ለምሳሌ በኛ በወጣቶች ዘንድ ተወዳጅ የሆነው የካርኔቫል በዓል ነው። ሊካሄድ ባለመቻሉ በጣም አዝናለሁ። በዛ ላይ ደግሞ ባለፉት ሶስት እና አራት ወራት በትርፍ ጊዜዬ እግር ኳስ ከቡድኔ ጋር ልጫወት አልቻልኩም። ለምን እንደተከለከለ ይገባኛል ግን ጥሩ መዝናኛዬ ነበር። በቃ የዕለት ከዕለት ኑሮዬ ይናፍቀኛል። በአካል ትምህርት ቤት ተገኝቶ መማር፤ ከሌሎች ልጆች ጋር መገናኘት እና ማውራት እሻለሁ፤ የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ መማር የሚቻለውም እዛው ትምህርት ቤት ነው። ሌሎቹም ቢሆኑ ከሰው ጋር መገናኘት እና መወያየቱ የሚያስደስታቸው ይመስለኛል።»የኮሮና ወረርሽኝኝ ለመግታት ጀርመን ውስጥ የእንቅስቃሴ ገደብ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተጣለ ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ፓውል ትምህርት ቤት ተገኝቶ የተማረው ሶስት ወር ቢሆን ነው። ያውም በፈረቃ!

የ9 ዓመቷ ሉናም ብትሆን ከጓደኞቿ ጋር ተገናኝታ መጫወት አለመቻሏ በጣም ይረብሻታል። «ከሁሉም ከባዱ ለረዥም ቀናት፣ ሳምንታት፣ ወራት ከሌሎች ልጆች ጋር በአካል መገናኘት አለመቻሌ ባህሪዬን ሁሉ ቀይሮታል። ምክንያቱም የብቸኝነት ስሜት ስላለው፤ አብሮኝ የሚጫወት  ሰው አልነበረም። እና ይህ ነው በጣም የሚናፍቀኝ። »በተለይ እህት እና ወንድም የሌላቸው ህፃናት እና ወጣቶች ከጓደኞቻቸው ጋር እንደልብ መገናኘት አለመቻላቸው ብቸኝነቱን አጉልቶባቸዋል። የ8ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ሀነስ በዚህ እረገድ እድለኛ ነው።« ደግነቱ ወንድሞች አሉኝ። ከጓደኞቼ ጋር ባይሆንም ከወንድሞቼ ጋር በተናጥል መጫወት እችላለሁ። አብዛኛውን ጊዜ ስፖርት ከእነሱ ጋር እሰራለሁ፤ እጫወታለሁ።»ሀነስ 13 ዓመቱ ነው። ኮሮና ባይኖር ኖሮ የሚወደውን እግር ኳስ በመጫወት ትርፍ ጊዜውን ያሳልፍ ነበር። እሱም እንደሌሎቹ ልጆች ጎደኞቹን መልሶ የሚያገኝበትን ቀን ይናፍቃል።

Deutschland - Urlaub in der Corona-Krise
በርካታ ቤተሰቦች ለዕረፍት ሽርሽር መሄድ ስላልቻሉ መዋኛ እየገዙ እቤታቸው ውስጥ በጋውን አሳልፈዋልምስል picture-alliance/dpa/P. Pleul

ከዘንድሮዉ የጎሪጎሪያኑ የገና በዓል በፊት ትምህርት ቤት ዳግም የተዘጋባቸው እነዚህ ተማሪዎች በየጊዜው ትምህርት ቤት ይከፈታል ብለው ተስፋ ቢያደርጉም እስካሁን ከተስፋ ያለፈ ነገር አልገጠማቸውም። አሁን ግን ትንሽ ጭላንጭል ይታያል። ምንም እንኳን ጀርመን የኮሮና እገዳውን ካለፈዉ ዕሮብ ዕለት ጀምሮ ለተጨማሪ አንድ ወር ገደማ ያህል ብታራዝምም ትምህርት ቤቶች እና የህፃናት መዋያዎች፤ እንደየ ክፍለ-ግዛቱ እና የኮሮና የስርጭት መጠን አስቀድመው አንዳንዶችም የሚቀጥለው ሳምንት ሊከፈቱ ይችላሉ።  ልዩነት ያለው ትምህርት መልሶ የሚከፈትበት ጊዜ ላይ ብቻ አይደለም። ምንም እንኳን ጀርመን ሀብታም ሀገር ብትሆንም አንዳንድ ተማሪዎች ትምህርቱን በኦንላይን ለመከታተል የሚያስችል በቂ መገልገያዎች እንኳን የላቸውም። በተለይ በሀገሪቱ አዳዲስ ትምሕርት ቤቶች የገቡ ወይም  ለመጀመሪያ ጊዜ ተማሪዎች ከቤታቸው ሆነው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ መደረጉ ለብዙዎች ይህ ትልቅ ፈተና ነበር። ፓውል እድለኛ ከሚባሉት ተማሪዎች አንዱ ነው፤ እንደዛም ሆኖ እሱም ጋር ፈተናዎች አልጠፉም።«እኔ ለምሳሌ ሁለት ወንድሞች አሉኝ፣ አባቴም ከቤት ነው የሚሰራው፤  አንዳንዴ ሁላችንም በተመሳሳይ ሰዓት የቪዲዮ ውይይት ሲኖረን ፤ ኢንተርኔቱ ይንቀራፈፋል። ከዚህም ሌላ አራት ሰዎች ሲኖሩ ሁሉም በጥሩ ሁኔታ ተቀምጠው የሚሰሩበት ቦታ ያስፈልጋቸዋል። እና እነዚህ ነገሮች ትንሽ ፈታኝ ናቸው። ሌሎች ከዚህ የከበደ ነገር ሊገጥማቸው እንደሚችል እገምታለሁ፤ ነገር ግን በአካባቢዬ ካሉም ይሁን ከኔ ትምህርት ቤት ልጆች ይህንን አልሰማሁም።»የህፃናት መርጃ ተቋም የሆነው ዶይቸ ኪንደር ሂልፍስቬርክ ስራ አስኪያጅ ሆልገር ሆፍማን ችግሩን በሚያገባ ያውቃሉ።  ኃላፊው እንደሚሉት ከሆነ በአፋጣኝ ርምጃ መወሰድ አለበት፤« በድህነት ለሚያድጉ ህፃናት ከትምህርት እና ማህበራዊ ግንኙነት አንፃር በጣም አስጨናቂ እና ኪሳራ የሆነ አመት ነበር።  በቀላሉ ማካካስም አይቻልም። ስለሆነም እነዚህን ቤተሰቦች ቀውሱ ካለፈ በኋላ ሳይሆን አሁኑኑ ማገዝ እንዳለብን መረዳት ይኖርብናል። »ጀርመን ውስጥ አንድ አምስተኛ የሚሆኑት ህፃናት በጀርመን የኑሮ ደረጃ ደሀ ወይም ድህነት ያጠላባቸው ተብለው ይቆጠራሉ። አብዛኛውን ጊዜ ወላጆቻቸው የሚያስፈልጉዋቸውን ነገር ሊያሟሉላቸው አይችሉም።

የኮሮና እገዳ ራሳቸውን ችለው ይኖሩ የነበሩትንም ወጣቶች ህይወት ክፉኛ አስተጓጉሏል። በትርፍ ጊዜያቸው በምግብ ቤት ፣ፋብሪካዎች እና ሱቆች በመሳሰሉ ቦታዎች እየሰሩ የዩንቨርስቲ ትምህርታቸውን ይከታተሉ የነበሩ ተማሪዎች ስራ ካጡ ወራቶች ተቆጠሩ። በዚህም የተነሳ የቤት ኪራያቸውን መክፈል አልቻሉም። ቅርብ ጊዜ የተደረገ አንድ መጠይቅ እንደሚጠቁመው ከ 30 በመቶ በላይ የሚሆኑት ተማሪዎች መልሰው ወላጆቻቸው ቤት ገብተዋል። ታድያ ነፃነት ለቀመሱት የዮንቨርስቲ ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን በጉርምስና እድሜ ላይ ለሚገኙትም ወጣቶች ቢሆን 24 ሰዓት ከወላጅ ጋር አንድ ቤት ውስጥ መሆን ደግሞ፤ ከባድ መሆኑ ለማንም ግልፅ ነው፤ «የሆነ ጊዜ ኮሮና ያበቃል፤ በጋራ እንወጣዋለን የሚል አመለካከት ነበረን። አሁን ላይ ግን በቃ ሁኔታው ያበሳጫል፤ የቀድሞውን የዕለት ከዕለት ኑሮ ሁላችንም እናፍቃለን።  አንዳንድ ወላጆች ከቤት ነው የሚሰሩት፤ ሌሎች ደግሞ እቤት አይደሉም። እና ምንም እንኳን ሁላችንም በየክፍላችን ሆነን የየራሳችንን ስራ ብንሰራም፤ ከቤት ከሚሰሩት ወላጆች ጋር በመጠኑም ቢሆን መነዛነዙ አይቀርም። »ይላል ፓውል። የጀርመን መንግሥት በተቻለ መጠን ሰዎች ከቤታቸው ሆነው እንዲሰሩ ግፊት እያደረገ ነው፤  የሀነስ ወላጆችም ቢሆኑ አብዛኛውን ጊዜ ከቤት ነው የሚሰሩት።

Homeoffice - Arbeitsplatz in der Coronakrise
ጀርመን ውስጥ በኮሮና ምክንያት እገዳ ከተጣለ ጊዜ አንስቶ ወላጆች እና ልጆቻቸው ከቤት ሆነው የሚሰሩበት እና የሚማሩበት ሁኔታ ተጠናክሮ ቀጥሏልምስል Imago/O. Müller

ሀነስ የኮሮና ደንቦች ያበሳጩታል ቢሆንም ህጉ በሚፈቅደው መሠረት  ከጓደኞቹ ጋር በተናጥል አልፎ አልፎ ይገናኛል። አብዛኛው ጊዜ ግን በስልክ እና በቪዲዮ ነው የሚወያዩት፤ ኮሮና አንዱ መወያያ ርዕሳቸው ነው።« በመጠኑም ቢሆን አሁን ለምደንዋል ።መጀመሪያ ላይ ከባድ ነበር ስሜቱም የተረጋጋ አልነበረም።አሁን ግን ስለለመድነውም ይሆናል ደህና ነው ።»

በጀርመን ሀገር ወጣቶች ለምሳሌ 16 ዓመት ከሞላቸዉ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ዲስኮ ወይም ጭፈራ ቤት መግባት እና መቆየት ይፈቀድላቸዋል። ጭፈራ ቤቶች ግን በሀገሪቱ የመጀመሪያው እገዳ ከተጣለ ጊዜ አንስቶ እንደተዘጉ ነው።  ስለሆነም 16 ዓመት የሞላቸው እና ይህንን ቀን በጉጉት ሲጠብቁ የነበሩ ወጣቶች እስካሁን እድሉን አላገኙም። ፓውልስ ይህንን ቀን በጉጉት ይጠባበቅ ይሆን? «አዎ!  16 አልሆነኝም። ግን ሊሞላኝ ነው። እና እስካሁን ጭፈራ ቤት አልገባሁም። ቢሆንም ከዚህ ቀደም ጭረራ ቤትም ባይሆን ማታ ላይ ተሰባስበን መዝናናት እንችል  ነበር። ይህም አሁን ቀርቷል እና ያሳዝናል። እስቲ 16 ሲሞላኝ ይከፈት እንደው እናያለን። ሌላው ደግሞ ከጓደኞቼ ጋር ወደ ስፔን ሽርሽር ለመሄድ ቲኬት ገዝተናል። ይህም ይሳካ ወይስ ይሰረዝብን እንደው ለማወቅ በጣም ጓጉቻለሁ። »

ልደት አበበ

ነጋሽ መሀመድ