1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮሮና ቫይረስ ስጋት በአፍሪቃ፤የቻይና የአፍሪቃ የልማት አጋርነት

ቅዳሜ፣ ጥር 23 2012

ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት በቻይና ዉሃን ከተማ የኮሮና ባይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ከገለፀ ከታኅሳስ 12 ቀን 2012 ጀምሮ የዓለም ሀገራትን እያሳሰበ ነዉ።በወረርሽኙ የተጠቁና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ መምጣት ደግሞ ስጋቱን የበለጠ እንዲጨምር አድርጎታል።

https://p.dw.com/p/3X8vu
Deutschland Coronavirus Labortests
ምስል picture-alliance/dpa/M. Murat

ትኩረት በአፍሪቃ

የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅትም ወረርሽኙን ያለፈዉ ሀሙስ አስቸኳይ ድጋፍ የሚፈልግ ዓለም አቀፍ  የጤና ስጋት መሆኑን አዉጇል።የቻይና ባለስልጣናትም ቦታዉን የዘጉት ሲሆን የተለያዩ የዓለም ሀገራትም ዜጎቻቸዉን ከቻይና ዉሃን ግዛት ለማስወጣት እየሞከሩ ነዉ። አንዳንዶቹም የጉዞ እገዳ ጥለዋል።ሁኔታዉ በከተማዋ ለሚማሩ ከ5 ሺህ በላይ ለሆኑ የአፍሪቃ ሀገራት ተማሪዎችም በጣም አሳሳቢ ነዉ። ያም ሆኖ ተማሪዎቹ ቦታዉን የመልቀቅ ሀሳብና ተስፋ ብዙ አለመሆኑን ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሲገልፁ ይሰማል።ለዚህም የአፍሪቃ ባለስልጣናት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ወደ ሀገርቤት ቢመለሱ ወረርሽኙ ሊስፋፋ ይችላል የሚል ስጋት ያላቸዉ ይመስላል።ለአብነትም ቻይና ያሉ የደቡብ አፍሪቃ ተማሪዎች የቻይና ዩንቨርሲቲዎች የሚሰጧቸዉን መመሪያ ብቻ መከተል እንዳለባቸዉ ቤጅንግ የሚገኜዉ የሀገሪቱ ኢምባሲ በኩል ተነግሯቸዋል። ይህም ያለፍቃድ መዉጣት ብዙ መዘዝ እንዳለዉ ያመለክታል።«ልክ እስር ቤት ያለሁ ያህል ይሰማኛል»ይላል ከቶንጆ ህክምና ኮሌጅ የዶክትሬት ዲግሪዉን በመከታተል ላይ የሚገኜዉ የታንዛኒያዉ ሂላል ኪዚዊ  ሁኔታዉን ሲገልፅ።ያም ሆኖ እሱና ሌሎች ጓደኞቹ ቦታዉን ለቀዉ ለመዉጣት ከሀገራቸዉ ኢምባሲ መተማመኛ ማግኜት አለባቸዉ።ነገር ግን ይህን አልጠብቅም ይላል ሂላል። ይህንን ችግር ለመቋቋም ታዲያ አፍሪቃዉያኑ ተማሪዎች እርስ በእርሳቸዉ መረዳዳት ይዘዋል።እሱና ጓደኞቹ።ለአፍሪቃዉያን ተማሪዎች የራስ አገዝ ቡድን አቋቁመዋል። ቡድኑ በከተማዋ  ስላለዉ ወቅታዊ የጤና ሁኔታና ስለቫይረሱ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መረጃዎችን ያሰራጫል።በዚህም ጓደኞቻቸዉን ያበረታታሉ።ተማሪዎቹም «እኛ እንደ አንድ ቤተሰብ አባል ነን» ሲሉ ያለፈዉ ማክሰኞ በቲዊተር ገፃቸዉ  ፅፈዋል።ያም ሆኖ አፍሪቃዉያኑ ተማሪዎች የምግብ አቅርቦት ችግር እያጋጠማቸዉ መሆኑን የዶክትሬት ዲግሪዉን በመከታተል ላይ የሚገኜዉ ታንዛኒያዊዉ ተማሪ ከሃሚስ ሀሰን ባክሪ ይገልፃል።
«ሱቆች በአብዛኛዉ ተዘግተዋል።በዩንቨርሲቲዉ ግቢ ዉስጥ የሚገኙ ጥቂት የምግብ መደብሮች ለተወሰኑ ስዓታት ብቻ ይከፈታሉ።እዚያ  ነዉ ሰዎች ምግብ የሚገዙት።ነገር ግን ጥቂት የምግብ አይነቶች ብቻ ነዉ የሚገሸጡት።ዋጋቸዉም ቢሆን ዉድ ነዉ።»
የኮሮና ቫይረስ በእስያ፣በአዉሮፓና በአሜሪካ መከሰቱ ቢረጋገጥም በአፍሪቃም ሁኔታዉ አሳሳቢ ነዉ። ባለፈዉ ሳምንት የወጡ ይፋዊ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት የመጀመሪያዎቹ በኮሮና ባይረስ ተይዘዋል ተብለዉ የተጠረጠሩ ሰዎች በአይቮሪኮስት፣በሱዳን፣በኬንያ እንዲሁም በምርመራ ነፃ መሆናቸዉ ቢረጋገጥም በኢትዮጵያም ጥርጣሬ እንደነበር ሲገለፅ ቆይቷል።
ከአፍሪቃ ህብረት የበሽታዎች መቆጣጠሪያ ኤጀንሲ ጆን ናንጋሶንጎም የኮሮና ባይረስ ወረርሽኝ በአፍሪቃም የጊዜ ጉዳይ ነዉንጅ መረጋገጡ አይቀሬ ነዉ ይላሉ።
«በአህጉራችን ያልተረጋገጡ የበሽታዉ ምልክቶች አሉ።ነገር ግን የመከሰት ዕድል አለዉ ይህን መቀበል አለብን።በዓለም ዙሪያ በኮሮና ቫይረስ መኖሩ ከተረጋገጠ ፣በአፍሪቃ ዉስጥ የለም ብለን በጣም ዕድለኞች እንደሆን አምነን መቀበል የለብንም።»
እናም አስፈላጊዉ ነገር በአህጉሩ ጠንካራ የጤና ክትትል ስልቶችን ተግባራዊ ማድረግ ነዉ ሲሉ ናንጋሶንጎ ሰሞኑን በአዲስ አበባ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አመልክተዋል።
«የክትትል ስልቶቹ አባል ሀገራቱ ባላቸዉ የጤና ክትትል ስርዓት ይወሰናል።እንደምናዉቀዉ ሀገራቱ በተለያዬ የጥንካሬ ደረጃ ላይ ነዉ የሚገኙት።ስለዚህ ለአመታት የገነቧቸዉን ስልቶች እንዴት ጠንካራ እንደነበሩ ይህ ጉዳይ መፈተኛ ነዉ።»
በአፍሪቃ የኮሮና ቫይረስን የመቆጣጠር ስልት ከ2014 እስከ 2016 ከአስር ሺህ በላይ ሰዎችን ከገደለዉ ከኢቦላ ቫይረስ ልምድ እንዳገኙ የሚናገሩም  አሉ።በዚሁ መሰረት የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ስልት መንደፋቸዉን ከአቡጃ የመንግስት የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ተቋም ጆሴፍ ቤኒ ለዶቼ ቤለ ገልፀዋል።
«በኢቦላ ለተገኜዉ ልምድ ምስጋና ይግባዉና ከዚህ በፊት እንደሰራነዉ ተመሳሳይ ስልት ስራ ላይ እያዋልን ነዉ።»
ከ200 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በሚኖርባት ናይጀሪያ በአዎሮፕላን ጣቢያ ሳይቀር የቫይረሱን መከላከያ ማዕከላት ሀነዋል።ነገር ግን የኮሮና ቫይረስ እንደ ኢቦላ ወረርሽኝ አይደለም ይላሉ ጆን ናንጋሳንጎ።እናም አጀንዳዉ በአሁኑ ወቅት ከቻይና መንግስትና ከዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ጋር በመሆን ሁሉም የአፍሪቃ ህብረት ሀገራት ትክክለኛዉን የምርመራ ቁሳቁስ እንዲያገኙ መሆን አለበት።ምክንያቱም ቫይረሱ እስካሁን ከጥርጣሬ ባለፈ ለማረጋገጥ ፈተና ሆኗል።ኢትዮጵያም ብትሆን የተጠርጣሪዎቹን የደም ናሙና የላከችዉ ወደ ደቡብ አፍሪቃ ነበር።
የቻይና የልማት  አጋርነት በአፍሪቃ
ቻይና ከአፍሪቃ ሀገራት ጋር በኢኮኖሚ በቴክኖሎጅና በተለያዩ ዘርፎች የምታደርገዉ ትብብር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።በቅርቡ ኢትዮጵያ ከቻይና ባለሙያዎች ጋር በቻይና ሀገር ያደረገችዉ የሳተላይት ማምጠቅ አድዱ ማሳያ ነዉ።ቻይና ከ8 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካን ዶላር  ለዚሁ ፕሮጀገት ብድር ሰጥታለች።«አሁን አስራ አንድ ከሰሃራ በታች ያሉ ሀገሮች የራሳቸዉን ሳተላይት ማምጠቅ ችለዋል።»ይላሉ የናይጀሪያዉ« ስፔስ በአፍሪቃ» የተሰኜ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቲሚዮዶ ኢሳያህ ኦኒሰን።እንደ እሳቸዉ ገለፃ የአፍሪቃ የስፔስ ሳይንስ ኢንደስትሪ ከዚህ የበለጠ ማደግ አለበት ። 
«በአሁኑ ወቅት ብዙ መሻሻል አለ።ኢንደስትሪዉ አሁን ሰባት ነጥብ ሃያ ሰባት ቢሊዮን  የአሜሪካን ዶላር የደረሰ ሲሆን ፤በሚቀጥሉት አራት አመታት ደግሞ  ወደ  አስር ነጥብ ሃያ አራት  ቢሊዮን እንዲያድግ ይጠበቃል።» 
በጎርጎሮሳዊዉ 1999 ደቡብ አፍሪቃ የመጀመሪያዉን ሳተላይት ወደ ህዋ ያመጠቀች አፍሪቃዊት ሀገር ስትሆን ናይጄሪያ እስካሁን 4 ሳተላይቶችን በታላቋ ብሪታንያ፣በቻይናና በሩሲያ ድጋፍ በ2003 ዓ/ም አምጥቃለች።ጋና በ2017 በጃፓን ድጋፍ ሩዋንዳም «ዋን ዌብ »በተባለ የታላቋ ብሪታንያ ኩባንያ ድጋፍ ፤ያለፈዉ ዓመት ደግሞ ሱዳን በቻይና ድጋፍ ሳተላይት አምጥቀዋል።
በአፍሪቃ የስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጅ የተለያዩ ሀገራት መዋዕለ ንዋያቸዉን እያፈሰሱ የቆዩ ሲሆን የአዉሮፓ ሀገራት ቀዳሚዉን ስፍራ ይዘዉ ቆይተዋል።በአሁኑ ወቅት ግን ቻይና በቅርብ ርቀት  እየተከተለች ነዉ።ቻይና በ2018 ብቻ በ550 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለናይጀሪያ ሁለት የቻይና ሳተላይቶች ገዝታለች። ደቡብ አፍሪቃና ናይጀሪያን የመሳሰሉ ሀገራትም በትብብር ከቻይና ጋር የሚሰራ የራሳቸዉ የስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጅ ማዕከል አላቸዉ።ቻይና በአፍሪቃ በበጎ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ያላት ሀገር መሆኗም ተመራጭ አድጓታል ይላሉ ኦኒሰን። 
«በአመዛኙ ፖለቲካዊ ነዉ።በዚህ ረገድ ኢትዮጵያን ብትመለከቱ  ከቻይና ጋር በጣም ጥሩ የዲፕሎማሲ ግንኙነት አላት።ምክንያቱም መንግስታት የስፔስ ሳይንስ መርሀ-ግብሮችን ማካሄድ የሚፈልጉት  ከዚህ በፊት እንደቤተሰብ ከሚቀርቧቸዉ ሀገሮች ጋር ነዉ።ቻይና በአሁኑ ወቅት ከብዙ የአፍሪቃ ሀገራት ጋር ጥሩ ግንኙነት እየመሰረተች ነዉ።ለዚህ ነዉ ቻይና ጥሩ አማራጭ የሆነችዉ።»
ቻይና በፋይናንስ ረገድም ለአፍሪቃ በአሁኑ ወቅት ትልቅና ቀዳሚ አጋር ነች።ምክንያቱም ሀገሪቱ በምታደርገዉ የንግድ አጋርነት ቅድሚያ የምትሰጠዉ ለትርፍና ለአዋጭነት ነዉ።የምዕራባዉያን መንግስታት የንግድ ግንኙነት  ብዙ ቅድመሁኔታ ያለበት የፖለቲካ ማሻሻያን የሚጠይቅና ከዜጎች ነፃነት ጋር የተገናኜ በመሆኑ አንዳንድ የአፍሪቃ መንግስታት ግንኙነቱን «ጣልቃ ገብነት» የበዛበት ነዉ ይሉታል።እንደ ኦኒሰን ገለፃ አፍሪቃን ከተረጅነት ጋር ማያያዝም የምዕራባዉያን ሌላዉ ችግር ነዉ። 

China Quantum Satelit Micius
ምስል picture alliance/dpa/Photoshot/J. Liwang
Nasa Aufanhem von Afrika
ምስል picture-alliance/dpa/NASA
Deutschland Frankfurt am Main | Flughafen | Flugpassagiere mit Mundschutzmasken
ምስል picture-alliance/dpa/B. Roessler
Bangladesch | Aus China rückkehrendende Bangladeshi
ምስል A. Goni

 «በምዕራባዉያን ኩባንያዎች ዘንድ አፍሪቃን በኢኮኖሚ ጠቃሜታዋ ያለማየት አስተሳሰብ አለ። ብዙዎች አፍሪቃን የሚመለከቱት ከዕርዳታ ጋር አያይዘዉ ነዉ።ነገር ግን አፍሪቃ በኢኮኖሚ ማደግ ትፈልጋለች።»
ቻይና ሌላዉ በአፍሪቃ የምታካሂደዉ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት በመረጃ ቴክኖሎጅዉ ላይ ሲሆን ይህም ከግማሽ በላይ የበይነ መረብ ተደራሽነትን ለሌላቸዉ የአፍሪቃ ሀገራት ዕድል የሚሰጥ ነዉ።የስፔስ ሳይንስ ለአፍሪቃ ቀዳሚ ትኩረት ባይሆንም ፤የእርሻ ስራን ፣ምጣኔ ሀብትን ለማሳደግና አደጋን ቀድሞ በመከላከል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ይረዳል።እናም ትኩረቱ እዚያ ላይ መሆኑ ይበል የሚያሰኝ ነዉ ይላሉ ናይጄሪያዊዉ የስፔስ በአፍሪቃ ዳይሬክተር ቲሚዮዶ ኢሳያህ ኦኒሰን።

 

ፍሮይሊሽ ሲሊያ/ፀሐይ ጫኔ

እሸቴ በቀለ