1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦሞ ወንዝ ሙላት ስላከተለው አደጋ፣ የኢሰመኮ ማሳሰቢያ

ሥዩም ጌቱ
ረቡዕ፣ ነሐሴ 29 2016

ዘንድሮም በወንዙ ሙላት የተደቀነውን ፈተና ከባድነት ያብራሩት ሌላኛውም ነዋሪ አስተያየታቸውን አከሉ፤ “የፈጣሪ ቁጣ ነው ብለን አጨብጭበን ሜዳ ላይ ከመቀመጥ ውጪ የምንለው የለም” ያሉት አስተያየት ሰጪው ተፈናቃይ ሙዝ፣ የአርብቶ አደር የመኖ እርሻ፣ ማሽላና የበቆሎ ምርቱ በዘንድሮው የወንዙ ሙላት እንዳልነበር ሆኗል ነው ያሉት፡፡

https://p.dw.com/p/4kHM6
Äthiopien Überschwemmungen Omo-Fluss
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የኦሞ ወንዝ ሙላት ስላከተለው አደጋ፣ የኢሰመኮ ማሳሰቢያ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ደቡብ ኦሞ ዞን የኦሞ ወንዝ ከመጠን በላይ በመሙላቱ ምክንያት በጎርፍ ከተጥለቀለቁ የወንዙ የታችኛው ተፋሰስ አካባቢዎች በተለይም ከዳሰነች ወረዳ የተፈናቀሉ ሰዎችን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ግንቦት ወር ላይ ይፋ ማድረጉን አስታውሶ ነው መግለጫውን የጀመረው፡፡ በወቅቱም በአምናው ክረምት የወንዙ ሙላት ያደረሰው አደጋ እንዳይቀጥል ኢሰመኮ ምክረ ሐሳብ በማቅረብ ይህ ምክረ ሃሳቡ እንዲፈጸም ውትወታ ስያደርግም ነበር ተብሏል፡፡ 


የኢሰመኮ የስደተኞች፣ ሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ፍልሰተኞች መብት ክፍል ዳይሬክተር እንጉዳይ መስቀሌ  ለዶቼ ቬለ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ ኮሚሽኑ ከዚህ በፊት የሰጠው ምክረሃሳብ ለመከታተል በሚያስብበት ወቅት ከአከባቢው ተወላጆችና ተፈናቃይ ተወካዮች እንደገና በጎርፍ የመትለቅለቅ ስጋት እንደተጋረጠባቸው አቤቱታዎች ደርሶአቸዋል፡፡ “እነዚህን አቤቱታዎች ተከትለን ከነሐሴ 17 እስከ 23 ቀን 2016 ዓ.ም. የምክረ ሐሳቡ አፈጻጸም ክትትል እንዲሁም የኦሞ ወንዝ መሙላትን ተከትሎ የቱርካና ሐይቅ መደበኛ ይዞታውን በማስፋት በኦሞራቴ ከተማ እና በተፈናቃዮች ማቆያ ጣቢያዎች ላይ የጋረጠውን የጎርፍ መጥለቅለቅ ሥጋት ማንጃበቡን አረጋግጠናል” ነው ያሉት፡፡ከዓመታት በፊት በውሃ ሙላት የፈናቀሉት የዳሰነች ነዋሪዎች ችግር ላይ ናቸው

በኦሞ ወንዝ ሙላት ከአምና እስከ ዘንድሮ

በየአመቱ በአከባቢው ሞልቶ በሚፈሰው የኦሞ ወንዝ ሙላት መማረራቸውን የሚገልጹት የአከባቢው ነዋሪዎችም የዘንድሮው የወንዙ ሙላትና አደጋ መደቀን አዲስ አይደለም ባይ ናቸው፡፡ “በ2015/16 ም ከ32 ቀበሌያት 79 ሺህ 800 ሰው ተፈናቅለዋል” ያሉት አስተያየት ሰጪው አሁንም በወንዙ ሙላት ተመሳሳይ አደጋ መደቀኑን ገልጸዋል፡፡
ዘንድሮም በወንዙ ሙላት የተደቀነውን ፈተና ከባድነት ያብራሩት ሌላኛውም ነዋሪ አስተያየታቸውን አከሉ፤ “የፈጣሪ ቁጣ ነው ብለን አጨብጭበን ሜዳ ላይ ከመቀመጥ ውጪ የምንለው የለም” ያሉት አስተያየት ሰጪው ተፈናቃይ ሙዝ፣ የአርብቶ አደር የመኖ እርሻ፣ ማሽላና የበቆሎ ምርቱ በዘንድሮው የወንዙ ሙላት እንዳልነበር ሆኗል ነው ያሉት፡፡

 የኦሞ ወንዝ ሙላት ባለፈው ዓመት በደቡብ ኦሞ ዞን ያስከተለው ጥፋት
የኦሞ ወንዝ ሙላት ባለፈው ዓመት በደቡብ ኦሞ ዞን ያስከተለው ጥፋትምስል Shewangizaw Wegayehu/DW


ኢሰመኮ ከዚህ በፊት በሰጠው ምክረ ሀሳብ መሰረት በዳሰነች ወረዳ በሚገኙ 12 መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ከሚገኙ ተፈናቃዮች ውስጥ ከ79 በላይ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በቂ፣ ወቅቱን የጠበቀ እና ተደራሽ የምግብ ድጋፍ ማግኘታቸውን በበጎ መመልከቱን አንስቷል። ነገር ግን በኦሞ ወንዝ የላይኛው ተፋሰስ ላይ እየተገባደደ ባለው ነሐሴ ከመጀመሪያው ጀምሮ በጣለው ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ የኦሞ ወንዝ ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልቶ፤ በተጨማሪም የቱርካና ሐይቅ መደበኛ ይዞታው ሰፍቶ ወደኋላ በመመለሱ (back-flow) ምክንያት የዳሰነች ወረዳ ዋና ከተማ ኦሞራቴ እንዲሁም በሲየስ፣ ልበሙቀት እና ቻይና ካምፕ በተባሉ የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች ሥጋት መደቀኑን ተመልክቷል። ባዩ የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የሚገኙ 2,744 የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ደግሞ በጎርፍ አደጋው ለዳግም መፈናቀል መዳረጋቸውን ኢሰመኮ በክትትሉ መረዳቱን ገልጿል፡፡ የኦሞ ወንዝ እና የቱርካና ሐይቅ የውኃ ሙላት የኦሞራቴ ከተማን አስግቷታል


በወንዝ ሙላቱ የተቋረጠው መንገድ የሚያስከትለው ተጨማሪ አደጋ


የኢሰመኮ የስደተኞች፣ ሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ፍልሰተኞች መብት ክፍል ዳይሬክተር እንጉዳይ መስቀሌ አክለውም፤ “በስፍራው በተከሰተው የውሃ መጥለቅለቅ ከኦሞራቴ ወደ ነብረሙስ የሚወስደው የአስፋልት መንገድ በመሰንጠቁ ለከባድ ጭነት ተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ሥጋት በመፍጠሩ ለተፈናቃዮች የሚደረገው የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦትን አሳሳቢ አድርጎታል” ነው ያሉት። ተፈናቃዮች የንጹሕ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ማግኘት አስቸጋሪ ሆኖበታልም ያሌት እንጉዳይ፤ ተፈናቃዮች የሚኖሩባቸው መጠለያ ጣቢያዎች በጎርፍ ውሃ የተከበቡ መሆኑ ተፈናቃዮችን ለወባ በሽታ ማጋ ለጡን፣ በቂ የመጸዳጃ አገልግሎት አለመኖሩ ደግሞ ተፈናቃዮችን ለኮሌራ በሽታ ተጋላጭነት መዳረጉን አስገንዝበዋል፡፡

 የኦሞ ወንዝ ሙላት ባለፈው ዓመት በደቡብ ኦሞ ዞን ያስከተለው ጥፋት
የኦሞ ወንዝ ሙላት ባለፈው ዓመት በደቡብ ኦሞ ዞን ያስከተለው ጥፋት ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW


ኢሰመኮ በሰጠው ምክረ ሃሳብም ለተጨማሪ አደጋ ተጋልጠው የሚገኙትን ተፈናቃዮች ከተጋረጠባቸው አደጋ መታደግ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው ይላል፡፡ አስቸኳይ ድጋፍ የሚሹት የዳሰነች ተፈናቃዮች

ተፈናቃዮች ለዳግም መፈናቀል እንዳይዳረጉ መስራት፣ ወባና ኮሌራን ጨምሮ ባለው የጎርፍ ችግር ማህበረሰቡ ላይ የተደቀኑ የጤና ፈተናዎችን ግብረሰበናይ የረድኤት ድርጅቶችን በማስተባበር መቅረፍ እና ከዚህ በፊት የተፈናቀሉትን 79 ሺህ ግድም ተፈናቃዮችን ዘላቂ እልባት እንዲሰጥም ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡ 
የኢሰመኮ ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት የሚደርስ መፈናቀል እየተስፋፋ መምጣቱን አስታውሰው፤ “መሰል የተፈጥሮ አደጋ ሥጋት ያለባቸውን አካባቢዎች ለይቶ ጉዳት ከመድረሱ በፊት ከመከላከል አንስቶ በጉዳቱ ልክ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ አስፈላጊ የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎች መውሰድ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል’’ ብለዋል። 

ሥዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ