1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤርዶኻን ድልና የወደፊቱ ጉዟቸው

ማክሰኞ፣ ግንቦት 22 2015

«ኤርዶኻን ከእርሳቸው በኋላ ፓርቲያቸው የሚተካውን ሰው ማዘጋጀት አለባቸው። ወደፊት የቱርክ ፕሬዝዳንት የሚሆነው በቅርቡ ይታወቃል። ምናልባት ግን ኤርዶኻን እንደገና እጩ ተፎካካሪ ሆነው እንዲቀርቡ ዳግም ሕገ መንግሥቱን የመቀየር እቅድ ላይ ውይይትም እንዲካሄድ ሃሳብ ሊቀርብ ይችል ይሆናል።»

https://p.dw.com/p/4RywE
Türkei, Ankara | Erdogan am Abend nach der gewonnenen Stichwahl
ምስል Murat Cetinmuhurdar/Presidential Press Office/Handout/REUTERS

የኤርዶኻን ድልና የወደፊቱ ጉዞአቸው

የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬጄፕ ታይብ ኤርዶኻን በሁለተኛ ዙር የቱርክ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ማሸነፋቸው ያልተጠበቀ ባይሆንም ምናልባት ላይሳካላቸው ይችላል የሚል ጥርጣሬም ነበር። ይሁንና በሁለተኛው ዙር ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አብላጫ የመራጭ ድምጽ አግኝተው እንደ ቀደሙት ምርጫዎች ድል ተቀዳጅተዋል። 
እንደ ከዚህ ቀደሞዎቹ ምርጫዎች ቀላል የነበረ ባይሆንም፤በምዕራባውያን በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብትን በመጫንና በመሳሰሉት ጉዳዮች የሚከሰሱት የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬጄፕ ታይብ ኤርዶኻን አሁንም ተሳክቶላቸዋል። ባለፈው እሁድ በተካሄደው ሁለተኛ ዙር ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የ69 ዓመቱ ኤርዶኻን ከ52 ከመቶ በላይ ድምጽ አሸንፈው ለተጨማሪ አምስት ዓመታት መንበረ ሥልጣናቸው ላይ እንደሚቆዩ አረጋግጠዋል። ከሰሾቻቸው ምዕራባውያንም መልካም ምኞታቸውን መግለጻቸው አልቀረም።ኤርዶኻን ከድሉ በኋላ ለደጋፊዎቻቸው ባሰሙት ንግግር ድሉ የርሳቸው ፓርቲ ብቻ እንዳይደለ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። ህዝቡ ያለፈውን ወደ ኃላ ትቶም አንድ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።  
«አሸናፊዎቹ እኛ ብቻ አይደለንም። አሸናፊዋ ቱርክ ናት ፤አሸናፊው የተከፋፈለ ቢሆንም ህዝባችን ነው 
ዛሬ ማንም አልተሸነፈም። 85 ሚሊዮን ህዝቡ በሙሉ ነው ያሸነፈው። ህዝባችን በሰጠን ሃላፊነት መሠረት አልተበሳጨንም አልተናደድም ከማንም ጋር አልተጋጨንም። አሁን የምርጫውን ጊዜ የነበሩትን ክሮክሮችና ግጭቶቹን ወደ ጎን ትተን  በብሔራዊ ግቦቻችንና ራይያችን ላይ አንድ እንሁን ።»
ኤርዶኻን ከፍተኛው የሀገሪቱ የስልጣን ማማ ላይ ከወጡ ሀያ ዓመታት አልፈዋል።ሀገሪቱን በፕሬዝዳንት መምራት የጀመሩት ከጎርጎሮሳዊው 2014 ወዲህ ቢሆንም ከዚያ በፊት ከጎርጎሮሳዊው 2003 እስከ 2014 በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከ1994 እስከ 1998 ደግሞ የትልቋ የቱርክ የንግድ ከተማ የኢስታንቡል ከንቲባም ነበሩ። በ2001 ዓ.ም. ከተቋቋመው ከፓርቲያቸው «ከፍትህና የልማት ፓርቲ» በምህጻሩ AKP መሥራቾች አንዱም ናቸው።  ከቀደሙት የቱርክ ፖለቲከኞች በተለየ ኤርዶኻን የሀገሪቱን አቅም ማጠንከር የቻሉ መሪ ናቸው። ከዘንድሮው የቱርክ ወሳኝ ምርጫዎች በፊት የተሰባሰቡ የህዝብ አስተያየቶች ኤርዶኻንን ከተፎካካሪያቸው ወደ ኃላ ያስቀሩ ነበሩና በ2018ቱ ምርጫ ኤርዶኻን ዳግም መመረጣቸውን የሚደግፉ ፓርቲዎችን ወዳሰባሰበው «ፒፕልስ አላያንስ» ተጨማሪ ፓርቲዎችን አስገቡ። ይህም ኤርዶኻንን ግንቦት 14 ቀን 2023 ዓ.ም. በተካሄደው የህዝብ እንደራሴዎች ምርጫ ከፓርላማው 600 መቀመጫዎች 323ቱን ለማሸነፍ አብቅቷቸዋል። የዶቼቬለው ዘጋቢ ቶፕኩ ኤልማስ አዲሱን ፓርላማ በቱርክ የቅርብ ጊዜ ታሪክ እጅግ ወግ አጥባቂ ብሔረተኛ እና የእስልምና አጥባቂ ብሎታል። 
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር በምህጻሩ UNHCR እንደሚለው ቱርክ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ከለላ የሚያስፈልጋቸው ወደ አራት ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች ይገኛሉ። ይህ ለቱርክ ትልቅ ተግዳሮት ሆኖ ቀeሏል። ከዚህ ሌላ ሀገሪቱ በኤኮኖሚ ቀውስ ፣በዋጋ ግሽበት ፣በከፍተኛ ሥራ አጥነት በኮቪድ እና በቅርብ ጊዜዎቹ የተፈጥሮ አደጋዎችም ተጎድታለች። ቱርክ በአሁኑ ጊዜ በነዚህ ቀውሶች ውስጥ ብትገኝም ችግሮቹ ኤርዶኻንን ከድሉ ባለቤትነት አላገዳቸውም ይላሉ ኢስታንቡል በሚገኘው ኦዜይግን ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህርት ፕሮፌሰር ኤብራን ባልታ።
«ቱርክ በበርካታ ቀውሶች ውስጥ ነበረች። መጀመሪያ የስደተኞች እንቅስቃሴ እና የስደተኞች ቁጥር መጨመር፤ ቀጥሎ ሀገሪቱ የኤኮኖሚ ቀውስ ውስጥ መግባቷ ፣ከዚያም የኮቪድ ወረርሽኝ፣ በዚህ ዓመት የደረሱ  እጅግ ከባድ ርዕደ መሬቶችም ይጠቀሳሉ። የቱርክ ህዝብ ረዥም አሳዛኝ ወቅቶችን አሳልፏል። እነዚህ የተደራረቡ ቀውሶች ቢኖሩም ህዝቡ በነዚህ ሁሉ ቀውሶች ወቅት ፕሬዝዳንቱ ለነበሩት ለኤርዶኻን ነው ድምጼን የሰጠው።በአንድ በኩል ይህ የተጠበቀ ቢሆንም በሌላ በኩል ደግሞ ብዙዎችን ማስገረሙ አልቀረም። ሆኖም የሚጠበቀው ምክንያት በዚህን መሰል ቀውሶች ወቅት መራጮች ከአሁን ቀደም ለሚያውቁትና ለሚያምኑት ፖለቲከኛ ድምጻቸውን ወደ መስጠት ነው የሚያዘነብሉት።እንደሚመስለኝ ሰዎች በኤርዶጋን ላይ ያላቸው እምነት በመጠኑ ቢዳከምም አዲስና ከዚህ ቀደም ያልተሞከረ ፖለቲከኛን መምረጥ ግን አልፈለጉም።»  
ኤርዶኻንም ይህን በጣም የተገነዘቡ ይመስላል ይላል ቶፕኩ ኤልማስ ዘገባ ።በምርጫው እለት ምሽት ከቤተ መንስታቸው ሰገነት ላይ ሆነው ባሰሙት የድል ንግግር ደጋፊዎቻቸውን አመስግነው፤ አብረዋቸው እየዘመሩ እስከ መቃብር ድረስ እንደማይለዩዋቸው ቃል ገብተዋል።አጋሮቻቸውን መድረኩ ላይ እየጋበዙም «የክፍለ ዓለሙ ድል»ያሉትን እውን ማድረግ ስላስቻሉ አመስግነዋቸዋል። በአንጻሩ በንግግራቸው ተቃዋሚዎችን በእጅጉ ወርፈዋል። ተፎካካሪያቸውን ኬማል ኪሊችዳሮግሉንም አሸባሪ ከሚባለው PKK ተብሎ ከሚጠራው ድርጅት ዋና ጽህፈት ቤቶች መመሪያ ተቀብለው ተግባራዊ ሲያደርጉ ነበር ሲሉም ከሰዋቸዋል። ኤርዶኻን  ከ350 ሺህ በላይ የተገመቱ ደጋፊዎቻቸው ፊት ኪሊችዳሮግሉ ያለምንም ምክንያት የቀድሞ የአፍቃሬ ኩርድ ፓርቲ  በእስር ላይ የሚገኙትን በምህጻሩ HDP የቀድሞ ሊቀ መንበር  ሴላሃቲን ዴሚትራስን ለመፍታት ቃል ገብተዋል ሲሉ ተናግረዋል። ኤርዶኻን ዴሚትራስን ፈጽሞ የመፍታት ሃሳብ የላቸውም። ህዝቡ በአጸፋው ዴሚትራስን የሞት ቅጣት እንዲበየንባቸው  ጠይቋል። ኩርዳዊውን ፖለቲከኛ ዴሚትራስን ቱርክ እንድትለቅ የአውሮጳ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድቤት በተደጋጋሚ ሲጠይቅ ቆይቷል። እስካሁን ግን ጥያቄውመልስ አላገኘም ።ዴሚትራስ ከሚገኙበት እስር ቤት በምርጫዘመቻ ወቅት በጠበቆቻቸው በኩል ኪሊችዳሮግሉ ቢመረጡ እንደሚፈልጉ ተናግረው ነበር።
ኢብራሂም ኡሱሉ የህዝብ አስተያየት አጥኚና የፖለቲካ ግንኙነት አዋቂ ናቸው። ኤርዶኻን ወደፊትም በዚህን መሰሉ ምህረት የለሽ አነጋገር ይቀጥላሉ ብለው ይጠብቃሉ። ኡሱሉ ኤርዶኻን ከአሁን በኋላ ለመለወጥ ምክንያት የላቸውም ይላሉ።በርሳቸው እምነት ዳግማዊ ድሉን ኤርዶኻን በቀደመው መስመር ለመቀጠል ማረጋገጫ አድርገው ነው የሚያዩት  
«ቱርክ ከ10 ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የአካባቢ ምርጫ ታካሂዳለች። ያም ማለት በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ሀገሪቱ ወደ ምርጫ ዘመቻ ትገባለች። ያኔም ኤርዶኻን በተለመደው ከፋፋይ ንግግራቸው መቀጠላቸው መታየቱ አይቀርም። ምክንያቱም መንግሥታቸው ብዙ መፍትሄ ካላገኙ ጉዳዮች ጋር እየታገለ ነው። ከመካከላቸው የታመመው ኤኮኖሚና በሀገሪቱ የሚታየው የማኅበራዊ እኩልነት እጦት ይገኙበታል። ታዲያ ኤርዶኻን ህዝቡን ጽንፍ ማስያዙን ማቆም ይገባቸዋል? ወይም በሰላማዊ ቃላት ብቻ ተቃውሞአቸውን መግለጽ አለባቸው? ህዝቡ ይህን ጉዳይ መንግሥትን ለመፈተን መጠቀም መጀመሩ ከዛም በላይ ደግሞ ጥያቄውን ማንሳቱም አይቀርም። በዚህ ወቅት alይደግሞ መንግሥት ይህንማድረግ አይችልም። በሚቀጥለው ዓመት በጸደይ ወራት ከሚካሄደው ከምርጫው በኋላም የተለመደውን ህዝቡን ጽንፍ ማስያዙንና መከፋፈሉን ይቀጥልበታል ብዬ እጠብቃለሁ። »
አሁን ግን ይህ አስፈላጊ ነው ወይ የሚለው ነው ጥያቄው? ምክንያቱም ትልቁ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ኅብረት ከአሁኑ ሽንፈት በኋላ እንደ ከዚህ ቀደሙ አቅም ኖሮት መቀጠሉን አሁን እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም። ይህን ጉዳይ የተቃዋሚዎቹ መሪ ኬማል ኪሊችዳሮግሉም ከሦስት ዓመት በፊት አንስተውት ነበር።እስካሁን ከኅብረቱ አባላት ስድስቱ ከጥምረቱ ጋር ለመዝለቅ ሲሉ ልዩነቶቻቸውን ለማቻቻል ብዙ ርቀት ሄደዋል።  ይሁንና  እነዚህ ፓርቲዎች ወደፊትም አብረው ይዘልቁ ይሆን ነው ጥያቄው። በፕሮፌሰር ኤብራን ባልታ እምነት የተቃዋሚዎቹ ኅብረት ሊዘልቅ የሚችለው ቢያንስ የአካባቢ ምርጫ እስከሚካሄድ ነው።ሆኖም ተቃዋሚዎቹ ስኬታማ እንዲሆኑ አሁን የገጠማቸው ሽንፈት ትኩረት ሰጥተው መገምገም እና አዲስ አነቃቂ ኃይልም ማግኘት አለባቸው። 
ኢብራሂም ኡሱሉ እንደሚሉት ደግሞ ኤርዶኻን ዳግም እንዲመረጡ ጥረት ሊደረግም ይችላል። 
«ይህ ለኤርዶኻን በፕሬዝዳንትነት የመጨረሻ የስልጣን ዘመናቸው ነው። ምክንያቱም በሕገ መንግስቱ መሠረት ከአሁን በኋላ በፕሬዝዳንትነት መወዳደር አይችሉም። ኤርዶኻን በርካታ ችግሮች አሉባቸው። ይህ ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ ነው። ይሁን ናከእርሳቸው በኋላ ፓርቲያቸው የሚተካውን ሰው ማዘጋጀት አለባቸው። ወደፊት የቱርክ ፕሬዝዳንት የሚሆነው በቅርቡ ይታወቃል። ምናልባት ግን ኤርዶኻን እንደገና እጩ ተፎካካሪ ሆነው እንዲቀርቡ ዳግም ሕገ መንግሥቱን የመቀየር እቅድ ላይ ውይይትም እንዲካሄድ ሃሳብ ሊቀርብ ይችል ይሆናል።»  

Türkei Präsidentschaftswahl Erdogans Anhänger
ምስል Emrah Gurel/AP Photo/picture alliance
Duisburg | In Deutschland lebende Türken feiern den Wahlsieg von Recep Tayyip Erdogan
ምስል Christoph Reichwein/dpa/picture alliance
Türkei, Ankara | Erdogan am Abend nach der gewonnenen Stichwahl
ምስል Valery Sharifulin/TASS/dpa/picture alliance

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ