1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«በአፋርና በአማራ ክልሎች 3 ኢትዮጵያውያን የተራድዖ ድርጅት ሠራተኞች ተገድለዋል።»

ረቡዕ፣ ሐምሌ 19 2015

በቅርቡ በሥራ ላይ የነበሩ በአፋር ሁለት ፣ በአማራ ክልል አንድ የሰብዓዊ ድጋፍ ሠራተኞች ላይ "የሞት አደጋ ደርሷል" ሲሉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክርቤት ዋና ዳይሬክተር ሄኖክ መለሰ ጦርነት በነበረባቸው የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች ጥቂት የማይባል ቁጥር ያላቸው የተራድዖ ድርጅት ሠራተኞች መገደላቸውን ገልፀዋል።

https://p.dw.com/p/4UQAQ
Äthiopien I Situation in Tigray
ምስል Yasuyoshi Chiba/AFP/Getty Images

«ባለፈው ሳምንት ብቻ በአፋር እና በአማራ ክልሎች ሦስት ኢትዮጵያውያን የተራድዖ ድርጅት ሠራተኞች ተገድለዋል።»

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተከሰተ ወዲህ 40 የሲቪል ማህበረሰብ በዋናነት የተራድዖ ድርጅቶች ሠራተኞች ሕይወት ማለፉ ተገለፀ። ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት እንዳስታወቀው ዋነኛ የችግሩ ሰለባ እየሆኑ ያሉት የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ናቸው። ባለፈው ሳምንት ብቻ በአፋር እና በአማራ ክልሎች ሦስት ኢትዮጵያውያን የተራድዖ ድርጅት ሠራተኞች ምክንያቱ እስካሁን በውል ባልታወቀ ሁኔታ ተገድለዋል። 
በተራድዖ ድርጅት ሠራተኞች ላይ ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት በከፍተኛ ሁኔታ እንዳሳሰበው የገለፀው ምክር ቤቱ የግጭት ተሳታፊ አካላት የረድዔት ሠራተኞችን ደህንነት እንዲጠብቁ  ፣ ግጭቶች እንዲቆሙ እና መንግሥት የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት የማረጋገጥ ግዴታውን እንዲወጣ ጠይቋል። የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ሠራተኞቻቸው የሞቱባቸው የረድዔት ድርጅቶች የትኞቹ እንደሆኑ ከመግለጽ ተቆጥቧል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በዘርፉ ሠራተኞች ላይ እየደረሰ ነው ያለው ጉዳት በከፍተኛ ደረጃ እንዳሳሰበው ገልጿል። በቅርቡ በሥራ ላይ የነበሩ በአፋር ሁለት ፣ በአማራ ክልል አንድ የሰብዓዊ ድጋፍ ሠራተኞች ላይ "የሞት አደጋ ደርሷል" ያሉት የምክር ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ሄኖክ መለሰ  ጦርነት በነበረባቸው የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች ጥቂት የማይባል ቁጥር ያላቸው የተራድዖ ድርጅት ሠራተኞች መገደላቸውን ገልፀዋል።
"በተለይ የሰሜኑ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ቁጥራቸው ወደ 40 የሚደርሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ሠራተኞች ሕይወት አልፏል እና ጥንቃቄ ሊደረግበት ፣ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚሰጡ ሠራተኞች ፍፁም ከፖለቲካ ውጪ ሆነው ለማህበረሰቡ እርዳታ የሚያደርሱ ስለሆነ ልዩ ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል።" ብለዋል። 

ድርጅታቸው የተቋቋመበትን ዓላማ ለማስፈፀም በተለያዩ ክልሎች ተንቀሳቅሶ እንደሚሠራ የገለፁት ቪዥን ኢትዮጵያ ኮንግረስ ለ ዴሞክራሲ የተባለ ሲቪክ ድርጅት ዋና ሥራ አሥኪያጅ አቶ ታደለ ደርሰህ "ዛሬ መንቀሳቀስ አይቻልም" በማለት የሲቪል ድርጅቶች ሠራተኞች ተዘዋውሮ ለመሥራት እንቅፋት እየገጠማቸው መሆኑን አብነት ሠጥተዋል።"ዛሬ መንቀሳቀስ አይቻልም። ዛሬ ጋምቤላ ሄደን ማስተማር አንችልም። ዛሬ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ አሶሳ ሄደን ማስተማር አንችልም። አማራ ክልል ሄደን ማስተማር አንችልም።  ይሄ በሥራችን ላይ ትልቅ ጫና ፈጥሮብናል።" ብለዋል።የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ መለሰ በቅርቡ በአፋር እና አማራ ክልሎች ከተገደሉት የተራድዖ ድርጅት ሠራተኞች ውስጥ የውጭ ዜጎች የሉበትም ብለዋል። ኃላፊው ድርጅቶቹ እነማን እንደሆኑ ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል። ሠራተኞቹን ለሞት የዳረጋቸው ምክንያት ምን እንደሆንም ጠይቀናቸዋል። "ምክንያቶቹ ተባራሪ ሊሆን ይችላል። በግጭት ውስጥ ዒላማ የተደረገ ላይሆን ይችላል። ግን አካባቢዎቹ ከሰሜኑ ጦርነት ከትግራይ ጀምሮ በአማራ ክልል የነበሩ ግጭቶች ከፍተኛ ድርሻ ይወስዳሉ።" ብለዋል። 
የተራድዖ ድርጅት ሠራተኞች ሞቱባቸው የተባሉት ሁለቱ ክልሎች ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጡ በተለይ የአደጋ ሥጋት ተቋማትን ወደሚመሩ ኃላፊዎች ብንደውልም ምላሽ አላገኘንም። የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የግጭት ተሳታፊ አካላት የረድዔት ሠራተኞችን ደህንነት እንዲጠብቁ ፣ ግጭቶች እንዲቆሙ እና መንግሥትም የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት የማረጋገጥ ግዴታውን እንዲወጣ ጠይቋል። 
ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
ታምራት ዲንሳ