1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች እሮሮ በደቡብ ሱዳን

ዓርብ፣ ሰኔ 9 2015

በሱዳን የተቀሰቀሰውን ግጭት ሸሽተው ወደ ደቡብ ሱዳን የተሰደዱ ኢትዮጵያዉያን የከፋ ችግር ውስጥ መሆናቸውን ገለፁ።ስደተኞቹ ደቡብ ሱዳን ዶሮ በሚባል የስደተኞች መጠለያ የሚገኙ ሲሆን የምግብ፣የጤና እና የፀጥታ ስጋት ችግር እያጋጠማቸው መሆኑን ገልፀዋል።ቦታው ደን ዉስጥ በመሆኑ በወባ በሽታ በጊንጥ እና በእባብ እየተጎዱ መሆኑንም ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/4SetO
Sudan Um Raquba Flüchtlingscamp
ምስል Will Carter/NRC

ከሱዳን የሸሹ ኢትዮጵያውያን ችግር



በሱዳን ጦር ኃይል አዛዥ ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አልቡርሐንና የቀድሞ ምክትላቸዉና  የፈጥኖ ደራሽ ጦር አዛዥ ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ /ሐምዲቲ/ መካከል የተፈጠረው ግጭት ዳፋው በሀገሪቱ ለተጠለሉ የውጭ ሀገር ዜጎችም ተርፏል። 
 ካለፈዉ ሚያዚያ ወር  ጀምሮ ከሁለት ወራት በፊት በሱዳን የተቀሰቀሰውን ግጭት  ሸሽተው ወደ ደቡብ ሱዳን የተሰደዱ ኢትዮጵያዉያን እና የተለያዩ ሀገር ዜጎች አሁን ብርቱ ችግር ገጥሟቸዋል። 
በደቡብ ሱዳን መባን ወይም ቡኝ በሚባለው አካባቢ ልዩ ቦታው ዶሮ በሚባል የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የሰፈሩት እነዚህ ስደተኞች  ኢትዮጵያዉያንን ጨምሮ  ኤርትራውያን፤ ሶማሊያውያን፤ ኬንያውያን እና የሌሎች አፍሪቃ ሀገራት ዜጎችም ይገኙበታል። 
በፖለቲካ ችግር ከኢትዮጵያ ሸሽተው በስደት ከነበሩበት ሱዳን  ወደ ደቡብ ሱዳን ለዳግም ስደት ተዳርገው በዚሁ መጠለያ ጣቢያ የሚኖሩ አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ኢትዮጵያዊ ለDW እንደተናገሩት ወደ መጠለያ ጣቢያው የገቡት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አማካኝነት ቢሆንም፤ የከፋ ችግር እያጋጠማቸው ነው። «ቡን ወይም መባን ይባላል።ልዩ ቦታው ደሮ የሚባል ካምፕ ነው ያስቀመጡን።ቦታው ሜዳ ከመሆኑ አንፃር እንደገና በረሃ ነው። ውሃ የሚተኛበት ነው።በጣም አስቸጋሪ ነው።የሆነ መጋዝን የሚመስል ነው።ሴቱም ወንዱም በቃ አንድ ላይ ነው ያለው።ሴቶች አሉ ህፃናት አሉ።ነብሰጡሮች አሉ።ሁሉም በአንድ ላይ ነው ያለው።ምግብ የተወሰነ አምጥተዋል።ግን ለአንድ ሰው ለአንድ ወር ስድስት ኪሎ ነው።ሁለት መቶ ግራም በቀን ለአንድ ሰው ማለት ነው።ዘይት ሁለት መቶ ሃምሳ ግራም ነው ለአንድ ወር።ስለዚህ በጣም አስቸጋሪ ነው።»በማለት ገልፀዋል።
በመጠለያ ጣቢያው የሚገኙት ስደተኞች ቁጥራቸው ወደ 500 የሚጠጉ መሆናቸውን  የገለፁት እኙሁ ግለሰብ፤  ምንም እንኳ በሰላም እጦት ከሱዳን ሸሽተው ቢወጡም አሁን በተጠለሉበት  መጠለያ ጣቢያም ስደተኖቹ  የፀጥታ ችግር እና የደህንነት ስጋት እያጋጠማቸው መሆኑን ገልፀዋል።  
ከፀጥታ ችግሩ ባሸገር  የተጠለሉበት ቦታ ዝናብ የሚበዛበት፣ በጣም ሞቃታማ እና  እና ደን ዉስጥ በመሆኑ  በወባ በሽታ በጊንጥ እና በእባብ እየተጎዱ መሆኑን ተናግረዋል። ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገች ሌላዋ በዚሁ መጠለያ የምትገኝ ወጣትም በርካታ ህፃናት፣ ሴቶች ነብሰጡር እናቶች እና ህሙማን በመጠለያ ጣቢያው መኖራቸውን ገልፃ በችግሩ የበለጠ ተጎጅ መሆናቸውን አመልክታለች። 
«በመጀመሪያ ደረጃ የሰው ልጅ ሊያኖረው የሚችል ውሃና ምግብ ሊኖር ይገባል። ከዚያም አስተማማኝ የፀጥታ ሁኔታ ሊኖር ይገባል። እዚህ ቦታ ላይ ይህ ሁሉ የለም። እኔ ከተጠቁት መካከል አንዷ ነኝ። በጣም መጥፎ በሆነ ሁኔታ  ላይ ነው ያለነው። እባቦች አሉ ጊንጦች አሉ፤ ሁሌም የሚነከሱ ሰዎች አሉ። በዝናብ ምክንያት ተጥለቅልቀናል። የቀረፅነው ቪድዮ አለ ልንልክላችሁ እንችላለን። በጣም መጥፎ ኑሮ ነው እየኖርን ያለነው። ነብሰጡሮች አሉ፤ የታመሙ ሰዎችም አሉ።እኔ በበኩሌ የጥርስ በሽታ ነበረኝ። ወደሱዳን ከመጣሁ ቡኋላ ታስነቅይዋለሽ ተብዬ ነበረ። እንደ እኔ የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች አሉ።»
በተባበሩት መንግስታት እርዳታ ሱዳን ውስጥ  የነበሩት  እነዚህ ሰዎች ወደ ሌላ ሶስተኛ ሀገር ለመሻገር ይጠባበቁ የነበሩ ቢሆንም፤ በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት የወረቀት ማስረጃ እንዳልተሰጣቸውም ተናግረዋል። 
የደረሰባቸውን ዘርፈብዙ ችግር ለአካባቢው ባለስልጣናት እና ለተባበሩት መንግስታት ቢያሳውቁም እስካሁን ምንም መፍትሄ አለማግኘታቸውንም ጨምረው ገልፀዋል።በመሆኑም የሚመለከተው አካል መፍትሄ እንዲሰጣቸው ተማፅነዋል።

Sudan Flüchtlingswelle
ምስል Gueipeur Denis Sassou/AFP
Sudan | Kämpfe in Khartoum
ምስል - /AFP/Getty Images


ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ
ታምራት ዲንሳ