1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ወቅታዊ ሁኔታ

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 14 2015

ኮሮና ተኅዋሲ ጎብኝዎችን በማራቅ፣ ጦርነት ደግሞ የሚጎበኙ ሥፍራዎች ሰው እንዳይደርስባቸው ከማድረግ አልፎ ቅርሶችን በማውደም ጭምር ከፍተኛ ችግር ውስጥ የጣሉት የቱሪዝም ዘርፍ እንዲነቃቃ የሚያግዙ "ዲጂታል" አሠራሮችን እየተከተለ መሆኑን ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።

https://p.dw.com/p/4LN6b
Äthiopien Addis Abeba Stadtansicht
ምስል Seyoum Getu/DW

የቱሪዝም ዘርፉ የኮሮና የወረርሽኝና የጦርነት ድብርት ተቻጭኖታል


ኮሮና ተኅዋሲ ጎብኝዎችን በማራቅ፣ ጦርነት ደግሞ የሚጎበኙ ሥፍራዎች ሰው እንዳይደርስባቸው ከማድረግ አልፎ ቅርሶችን  በማውደም ጭምር ከፍተኛ ችግር ውስጥ የጣሉት የቱሪዝም ዘርፍ እንዲነቃቃ የሚያግዙ "ዲጂታል" አሠራሮችን እየተከተለ መሆኑን ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ። ከዚህ በፊት በኮሮና እና በጦርነት ምክንያቶች ለጉብኝት ወደ መዳረሻ ስፍራዎች መጓዝ ሥጋት የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ደግሞ በተሽከርካሪ ለጉብኝት መጓዝ የሀገር ውስጥም ይሁን የውጪ ጎብኝዎችን አላንቀሳቅስ ያለ አሳሳቢ የፀጥታ ችግር መሆኑን በዘርፉ ላይ የሚሠራ አንድ ግለሰብ ተናግሯል። 
ቱሪዝም ሚኒስቴር እንደሚለው የቱሪዝም ሥራ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሚባል ችግር ውስጥ ቢሆንም ዘርፉ የመንግሥት ዋና የሥራ ትኩረት ነው። 
ቱሪዝም ሚኒስቴር ሰራሁት ያለውን በተለይ የውጪ ጎብኝዎች ላገኙት አገልግሎት የሚከፍሉበትን የክፍያ አሠራር መላ ዛሬ አስተዋውቋል። ዘርፉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከገባበት ድባቴ እየወጣ ይመስላልም ብሏል። ሚኒስትሯ አምባሳደር ናኒሴ ጫሊ ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት የጉብኝት እንቅስቃሴ አለ ማለት ይቻላል ወይ ? ተብለው ተጠይቀው ጦርነትና ወረርሽኝ የጎዳው የሥራ ዘርፍ መሆኑን በመጥቀስ በዚህም ምክንያት ዘርፉን መንግሥት ትኩረት የሰጠው መሆኑን ገልፀዋል።
"በተጨባጭ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች አሉ። የመሰረተ ልማት ሥራ እየተሰራ ነው። ብዙ የግል ድርጅቶች በሆቴልና በማስጎብኘት ሥራ ውስጥ እየገቡ ነው" 
"ከዓመታት በፊት የሀገር ውስጥም ሆነ የውጪ ጎብኚ ቁጥር ጨምሮ ነበር። ኮሮና ችግር ፈጠረበት" የሚለው በቱሪዝም ላይ አተኩሮ የሚሰራው ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ከኮሮና መቀዛቀዝ ተከትሎ የዓለም ቱሪዝም ድርጅት የመልሶ ማገገም ስልት እየሰራ ባለበት ወቅት ኢትዮጵያ ሊጎበኙ ከሚችሉ ጥቂት ሀገሮች አንዷ መሆናን አስፍሮ እንደነበር፣ ይህ መልካም ገጽታ ግን በጦርነቱ ምክንያት "መክኖ መቅረቱን" አስታውሷል።
ከሰላም ስምምነቱ በኃላ የውጪ እንግዶች በተለይ በውስን ቁጥርም ቢሆን ወደ ላሊበላ እና ጎንደር ለመጓዝ ፍላጎት ማሳየታቸውንም መስክሯል። "ፍላጎትና መነቃቃት አለ በሀገር ውስጥ ቱሪስቱ በኩል። አሁን ደግሞ የመንገድ ሥጋት እየጨመረ መጣ፣ መድረስ ሳይሆን መጓዝ ሥጋት ሆኗል" ይላል።
የቱሪዝም ዘርፍ ከእነዚህ የወረርሽኝ እና የጦርነት ድብርት የወጣ ነው የሚሉት የቱሪዝም ሚኒስትሯ በእነዚህ ችግሮች ምክንያት የኢትዮጵያ የተሩዝም ዘርፍ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰበት ግን አልገለፁም። ጦርነቱ ያስከተለው የቅርስ ውድመት፣ መዘረፍ ፣ የውጭ ዜጎች ፍሰት ቅናሽንም ጠይቀናቸው አልመለሱትም። የቱሪዝም ጋዜጠኛው እንደሚለው ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት ቱሪስት ለመሳብ ማስታወቂያ ከመስራት ይልቅ የጦር መሳሪያ ሸመታ ላይ እንደነበረች አልሸሸገም። ያም ሆኖ ግን በተለይ የሰላም ስምምነት የሚለው ሀሳብ የተዘጋውን የዘርፉን ሥራ ለመክፈት እድል መፍጠሩን ገልጿል።

ሰለሞን ሙጬ 
አዜብ ታደሰ 
ማንተጋፍቶት ስለሺ