1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ የበጀት ጉድለት በ2017 ከአጠቃላይ ሀገራዊ የምርት መጠን 2.1% ድርሻ ይኖረዋል

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ሰኔ 5 2016

በ2017 የኢትዮጵያ የበጀት ጉድለት ከአጠቃላይ ሀገራዊ የምርት መጠን 2.1% ድርሻ እንደሚኖረው አቶ አሕመድ ሽዴ ተናግረዋል። መንግሥት ለሚቀጥለው ዓመት ያዘጋጀው 971 ቢሊዮን ብር በጀት 358.5 ቢሊዮን ብር ጉድለት ይገጥመዋል። ከ2017 በጀት 139.3 ቢሊዮን ብር ለዕዳ ክፍያ የታቀደ ነው። መንግሥት ኤኮኖሚው በ8.4% ያድጋል ብሎ ይጠብቃል።

https://p.dw.com/p/4gy8P
የኢትዮጵያ ብር
ኢትዮጵያ የምትከተለው የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት በ2017 እንደሚቀጥል የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተናግረዋል።ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የኢትዮጵያ የበጀት ጉድለት በ2017 ከአጠቃላይ ሀገራዊ የምርት መጠን 2.1% ድርሻ ይኖረዋል

ኢትዮጵያ የምትከተለው የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት በ2017 እንደሚቀጥል የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ትላንት ማክሰኞ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተናግረዋል። የገንዘብ ሚኒስትሩ ይኸን ያሉት መንግሥታቸው ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጋር በሚያደርገው ድርድር ብር ዶላር እና ፓውንድን ከመሳሰሉ ዋና ዋና የመገበያያ ገንዘቦች ጋር ያለው የምንዛሪ ተመን ሊዳከም ይችላል የሚል ሥጋት በበረታበት ወቅት ነው።

በባንኮች በሚከወነው ይፋ ምንዛሪ እና በተለምዶ ጥቁር እየተባለ በሚጠራው ትይዩ የውጪ ምንዛሪ ግብይት መካከል ያለውን እጅግ ሰፊ ልዩነት ማጥበብ በመጀመሪያው ሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር የተካተተ እንደነበር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የተናገሩት አቶ አሕመድ ዕቅዱ ተግባራዊ መደረጉ ባይቀርም የ2017 በጀት የተዘጋጀው ግን አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት እንደሚቀጥል ታሳቢ ተደርጎ መሆኑን ተናግረዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ የብር የመግዛት አቅምን የሚያዳክም እርምጃ ገቢራዊ እንደማይሆን ማስተማመኛ ለመስጠት የሞከሩት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ነው። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲን ወክለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን የተቀላቀሉት ዶ/ር አብርሃም በርታ ያነሱት ጥያቄ ጭምጭምታውንም ሥጋቱንም ያጣቀሰ ነበር።

“ችግሩን ለመቅረፍ የሚወሰዱ እርምጃዎች የሕዝባችንን የኑሮ ሁኔታ የሚያረጋጋ፤ ሀገርንም ጭምር የሚያረጋጋ መሆን መቻል አለበት” ያሉት ዶ/ር አብርሃም በርታ “ከአንዳንድ ወገኖች” “ከውጭ መንግሥታት በብድር ምክንያት ጫና በመፍጠር” ይፋውን የውጪ ምንዛሪ ግብይት ከትይዩው “ዕኩል ለማድረግ ሙከራዎች አሉ” የሚል መረጃ መስማታቸውን ተናግረዋል። “ይኸ ደግሞ የማንወጣው ችግር ውስጥ ይከተናል” የሚል የባለሙያዎች ትንታኔ መኖሩን የጠቀሱት ዶክተር አብርሀም “የሀገራችንንም ሕዝብ የማያረጋጋ ጉዳይ ሆኖ ሊታይ ይችላል” ሲሉ ተደምጠዋል።

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ባንኮች በ57 ብር ገደማ የሚገዙትን አንድ የአሜሪካ ዶላር በ58 ብር ገደማ ይሸጣሉ። በትይዩው ገበያ ግን አንድ የአሜሪካ ዶላር እስከ 120 ብር ድረስ እየተመነዘረ እንደሚገኝ ዶይቼ ቬለ ለመገንዘብ ችሏል። ባለፉት ዓመታት ብር ከዶላር አኳያ ያለው የምንዛሪ ተመን በሽርፍራፊ ሳንቲሞች እየተዳከመ ቢሔድም በባንኮች እና በትይዩ ገበያ መካከል ያለው ልዩነት ሊቀራረብ አልቻለም።

የኢትዮጵያ ብር እና ድንች ሽንኩርት
የብር የምንዛሪ አቅም ቢዳከም ኢትዮጵያ ከውጪ የምትሸምታቸው ሸቀጦች ዋጋ ሊንር እንደሚችል ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ። ምስል Eshete Bekele/DW

ብር እንደ ዶላር ካሉ ዋና ዋና መገበያያ ገንዘቦች ያለው ይፋዊ የምንዛሪ ተመን ተጋኗል የሚል አቋም ያላቸው እንደ ዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ያሉ ተቋማት ግፊት ተቀባይነት አግኝቶ የመግዛት አቅሙ ቢዳከም በገበያው ከፍ ያለ የዋጋ ግሽበት ሊከተል እንደሚችል ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።

የዓለም የምግብ መርሐ-ግብር ባለፈው ሚያዝያ ይፋ ባደረገው ሰነድ መንግሥት የውጪ ምንዛሪ ግብይት በአቅርቦት እና ፍላጎት መሠረት እንዲከወን ቢወስን ምግብ፣ የአፈር ማዳበሪያ እና ነዳጅን ጨምሮ ከውጪ የሚገቡ ሸቀጦች ዋጋ እንደሚጨምር አስጠንቅቋል።

ብርን ሊያዳክም የሚችለው ውሳኔ የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ከሚያደርገው ድርድር ጋር የተያያዘ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ከዓለም ባንክ በድምሩ ሰባት ቢሊዮን ዶላር የመበደር ፍላጎት እንዳለው ዘገባዎች ይጠቁማሉ።

ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጋር የሚደረገው ድርድር ኢትዮጵያ ከአበዳሪዎቿ ያገኘችው የብድር ክፍያ እፎይታ ዕጣ ፈንታን ይወስናል። የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ጋር በአንድ ወር ውስጥ ከሥምምነት ካልደረሰ ከፓሪስ ክለብ አበዳሪ ሀገራት ያገኘው የብድር ክፍያ እፎይታ ሊያበቃ ይችላል።

ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጋር በሚደረገው ድርድር ገፊ ምክንያት ብር ሊዳከም ይችላል የሚል ሐሳብ ላለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ እንደነበር የሚናገሩት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ “የሆነ ጊዜ እንደሚዳከም ብዙ ሰው የተቀበለው ጉዳይ ነው” ሲሉ ይናገራሉ። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው እንደሚሉት ጥያቄው “መቼ?” የሚለው ነው።

“የማዳከሙ ነገር ካለ በበጀቱ ውስጥ ታሳቢ መደረግ አለበት” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን የብር የምንዛሪ ተመን አሁን ባለበት ቢቀጥል ወይም ቢዳከም በ2017 በጀት ውስጥ የሚኖረው ተጽዕኖ መታሰቡ እንደማይቀር ያምናሉ። “የመንግሥት ሰዎች ለፓርላማ አያቅርቡት እንጂ ይኸን ጉዳይ ምንም ጥርጥር የለኝም ይሰሩታል” ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ
በ2017 የበጀት ጉድለት ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ሀገራዊ የምርት መጠን 2.1 በመቶ ድርሻ እንደሚኖረው የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ተናግረዋል። ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

አቶ አሕመድ ሽዴ ጉዳዩ የፈጠረውን ሥጋት መንግሥታቸው እንደሚረዳ ተናግረዋል። ይሁንና ሥራ ላይ ያለው የመንግሥት የምንዛሪ ተመን እንደሚቀጥል ለምክር ቤቱ አባላት አስረድተዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “ሥጋቱ የምንገነዘበው ነው” ያሉት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ “ዘንድሮ የነበረው ይፋ የምንዛሪ ተመን በቀጣይ ይኸንንው ታሳቢ አድርጎ ነው በጀቱ የቀረበው የሚለውን መያዝ ያስፈልጋል” ሲሉ ተደምጠዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለ2017 ያቀረበው 971.2 ቢሊዮን ብር በጀት ከተያዘው ዓመት አኳያ በ21.1 በመቶ ከፍ ያለ ነው። ለሚቀጥለው ዓመት የተዘጋጀው በጀት ከዘንድሮው በ169.56 ቢሊዮን ብር ይበልጣል። የ2017 በጀት ቅድሚያ ከሰጣቸው ጉዳዮች ቀዳሚው የዕዳ ክፍያ ነው።

“ለመደበኛ ወጪ የተደለደለው በጀት ለዕዳ ክፍያ የተያዘው ብር 139.3 ቢሊዮን ሲሆን ይኸም ለመደበኛ ከተመደበው ጠቅላላ ወጪ ውስጥ የ30.9 በመቶ ድርሻ ይዟል” ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። “ለዕዳ ክፍያ ከተያዘው በጀት ውስጥ 54.8 በመቶው ለሀገር ውስጥ ዕዳ ክፍያ እንዲሁም ቀሪው 45.2 በመቶው ለውጭ ሀገር ዕዳ ክፍያ የሚውል ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ከዕዳ ክፍያ ቀጥሎ እንደቅደም ተከተላቸው መንገድ፣ ትምህርት፣ መከላከያ፣ ጤና እንዲሁም ፍትህ እና ደሕንነት በፌዴራል የመደበኛ እና ካፒታል ወጪ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ የተሰጣቸው ናቸው። ግብርና ዝቅ ብሎ በ8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ሀገሪቱ የገጠሟትን የማክሮ ኤኮኖሚ ተግዳሮቶች ለመፍታት ሁለተኛው ሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ ተስፋ ተጥሎበታል። መንግሥት የሀገሪቱ ኤኮኖሚ በሚቀጥለው ዓመት 8.4 በመቶ ያድጋል ብሎ መተንበዩን አቶ አሕመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተናግረዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
የኢትዮጵያ የ2017 በጀት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሚደረጉ ውይይቶች በኋላ በአንድ ወር ውስጥ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል። ምስል Solomon Muche/DW

ከ2017 በጀት 451 ቢሊዮን ብር የተመደበው ለመደበኛ ወጪ ነው። ለካፒታል በጀት 283.2 ቢሊዮን ብር፣ ለክልል መንግሥታት ድጋፍ 222.7 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ 140 ቢሊዮን ብር ተመድቧል። ይኸ በጀት እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት የተጫነው ነው።

አቶ አሕመድ ሽዴ “የአጠቃላይ የፍጆታ ዕቃዎች እና የአገልግሎት የዋጋ ዕድገት በበጀት ዓመቱ የመቀነስ አዝማሚያ እያሳየ ቢሆንም ለተወሰነ ጊዜ ባለሁለት አሐዝ ሆኖ እንደሚቀጥል ግምት ተወስዷል” ሲሉ ተናግረዋል።

መንግሥታቸው “ጥብቅ የገንዘብ እና የፊስካል ፖሊሲ እርምጃዎች ተግባራዊ” እንደሚያደርግ የገለጹት አቶ አሕመድ የዋጋ ግሽበት በሚቀጥለው ዓመት ወደ 12 በመቶ ዝቅ ይላል ተብሎ እንደደተነበየ ገልጸዋል።  አቶ አሕመድ “የገቢ ዕቃዎች ዋጋ value of imported goods በ2016 በጀት ዓመት የአንድ በመቶ ጭማሪ እንደሚኖረው የተገመተ ሲሆን በ2017 በጀት ዓመት ደግሞ የ9 በመቶ ዕድገት እንደሚኖረው ግምት ተወስዷል” ሲሉ ተደምጠዋል።

መንግሥት የ2017 በጀት ለመሸፈን ከሀገር ውስጥ የገቢ ምንጮች፤ ከውጭ ዕርዳታ እና ብድር 612.7 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ዕቅድ አለው። ከዚህ ውስጥ 563.6 ቢሊዮን ብር ከሀገር ውስጥ ገቢ፤ 7.3 ቢሊዮን ብር በቀጥታ በጀት ድጋፍ ከሚገኝ ከመሠረታዊ አገልግሎት ከለላ ዕርዳታ እንዲሁም 41.8 ቢሊዮን ብር ከፕሮጀክቶች ዕርዳታ ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ መንግስት ለፓርላማ ያቀረበው ረቂቅ በጀት ያሳያል።

በዚህም መሠረት የሚቀጥለው ዓመት በጀት 358.5 ቢሊዮን ብር ጉድለት እንደሚገጥመው ሰነዱ ይጠቁማል። የበጀት ጉድለቱ ከአጠቃላይ ሀገራዊ የምርት መጠን (GDP) ያለው ድርሻ አቶ አሕመድ እንዳሉት 2.1 በመቶ ይሆናል። መንግስት በሚቀጥለው ዓመት በጀት የሚገጥመውን ጉድለት ለመሙላት ከሀገር ውስጥ 325.6 ቢሊዮን ብር የመበደር ዕቅድ አለው።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ