1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የገንዘብ ልውውጥ ሥምምነት እንዴት ያለ ነው?

ረቡዕ፣ ሐምሌ 10 2016

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ማዕከላዊ ባንክ 817 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው የመገበያያ ገንዘብ ልውውጥ ሥምምነት ተፈራርመዋል። ሥምምነቱ የሁለቱን ሀገራት የፋይናንስ እና የንግድ ትብብርን ይደግፋል ተብሏል። በድንበር ተሻጋሪ ክፍያዎች ብር እና ድርሐም የበለጠ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማድረግ የመግባቢያ ሥምምነቶች ተፈርሟል።

https://p.dw.com/p/4iQri
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ማዕከላዊ ባንክ ገዥ ኻሊድ ሞሐመድ ባላማ የተፈራረሟቸው ሥምምነቶች የሁለቱን ሀገሮች ግንኙነት ያጠናክራሉ ተብሏል። ምስል CC BY 2.0/U.S. Institute of Peace

የኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የመገበያያ ገንዘብ ልውውጥ ሥምምነት እንዴት ያለ ነው?

የኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ማዕከላዊ ባንኮች የመገበያያ ገንዘቦቻቸው ብር እና ድርሐምን የሚለዋወጡበት የሁለትዮሽ ሥምምነት ትላንት ማክሰኞ ተፈራርመዋል። ሥምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ማዕከላዊ ባንክ ገዥ ኻሊድ ሞሐመድ ባላማ ናቸው።

በሥምምነቱ መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 3 ቢሊዮን ድርሐም በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ማዕከላዊ ባንክ ተቀማጭ ይኖረዋል። የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ማዕከላዊ ባንክ በአንጻሩ 46 ቢሊዮን ብር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይኖረዋል። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ “የኢትዮጵያ መንግሥት ለምሳሌ የፋይናንስ ቀውስ ቢመጣ ወይም የውጭ ምንዛሪ ከባድ እጥረት በሚገጥምበት ሰዓት [በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ማዕከላዊ ባንክ] የተቀመጠውን ገንዘብ በቀላሉ መጠቀም ይችላልሲሉ ይናገራሉ።

ሁለቱ ባንኮች የተፈራረሙት 817 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው ሥምምነት ዶክተር አብዱልመናን እንደሚሉት ጊዜው ሲደርስ መወራረድ አለበት። ኢትዮጵያ በጎርጎሮሳዊው 2017 ከሱዳን ጋር ለሦስት ዓመታት የሚቆይ የ16 ሚሊዮን ዶላር ተመሣሣይ ሥምምነት ተፈራርማ ነበር።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ማዕከላዊ ባንክ በጋራ ባወጡት መግለጫ ሥምምነቱ “በሁለቱ ሀገራት መካከል የፋይናንስ እና የንግድ ትብብርን ይደግፋል” ብለዋል። የሥምምነቱ ፈራሚዎች ውሉ “ድንበር ተሻጋሪ ክፍያዎችን የበለጠ ውጤታማ እና ቀልጣፋ ያደርጋል” የሚል ተስፋም አላቸው።

የሀገራት ማዕከላዊ ባንኮች እንዲህ አይነት ሥምምነት በሌሎች ሀገራት ከሚገኙ አቻዎቻቸው የሚፈራረሙት የምንዛሪ ቁጥጥርን ለማምለጥ ነበር። የበለጸጉት ሀገራት የምንዛሪ ቁጥጥርን ሲያስወግዱ ግን መሰል ሥምምነቶች የረዥም ጊዜ ኢንቨስትመንትን ለመጠበቅ እና ፈራሚዎች በወለድ ተመን ምክንያት የሚያጋጥማቸውን ተጋላጭነት ለመለወጥ የሚጠቀሙበት መሳሪያ ሆነው ያገለግላሉ።

የአጭር ጊዜ የመገበያያ ገንዘብ ልውውጥ ሥምምነቶች እስከ አንድ ዓመት የሚቆዩ ናቸው። ረዥም የሚባሉት በአንጻሩ ከሦስት እስከ አስር ዓመታት ሊዘልቁ ይችላሉ። የሥምምነቶቹ የጊዜ ርዝማኔ በፈራሚዎቹ ድርድር የሚወሰን ይሆናል። ከ17 ዓመታት ገደማ በፊት ማለትም በጎርጎሮሳዊው 2007 መነሻውን ከአሜሪካ ያደረገው የዓለም የፋይናንስ ቀውስ በተከሰተበት ወቅት የዶላር እጥረት የገጠማቸው ባንኮችን ለመታደግ የበለጸጉት ሀገራት የምንዛሪ ልውውጥ መንገድ ተከትለው ነበር።

በኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ባንኮች መካከል የተፈረመው አይነት የመገበያያ ገንዘብ ልውውጥ ሥምምነቶች የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥትን በኃይል ለሚፈታተነው የውጪ ምንዛሪ እጥረት የተወሰነ እፎይታ ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ባለሙያዎች ያምናሉ። መሰል ሥምምነቶች ኢትዮጵያ አማራጭ የመገበያያ ገንዘቦች እንድታገኝ መንገድ ይጠርጋሉ። ይኸ ብሔራዊ ባንክ ለሀገር ውስጥ ተቋማት እና ለባንኮች የሚያስፈልጋቸውን የውጪ ምንዛሪ እንዲያቀርብ የተወሰነ አቅም ይሰጠዋል። ከዶላር ጥገኝነት የሚነጨውን ሥጋት ለመቀነስ ጭምር ዕድል የሚፈጥር ነው። ኢትዮጵያ ጠቀም ያለ ሸቀጥ ከምትሸምትባቸው እንደ ቻይና ያሉ የንግድ ሸሪኮቿ፣ እንዲሁም የውጭ ቀጥተኛ መዋዕለ-ንዋይ (FDI) እና ሐዋላ ከምታገኝባቸው ሀገሮች ጋር የሚበጁ መሰል ሥምምነቶች ፋይዳ ሊኖራቸው ይችላል።

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ማዕከላዊ ባንክ ጋር የተፈረመው ሥምምነት ለኢትዮጵያ ጠቃሚ የገንዘብ ምንጭ እንደሚሆን እምነት አላቸው። ሥምምነቱ ኢትዮጵያ የምትጠቀምባቸውን የመገበያያ ገንዘቦች ብዛት እንደሚያሰፋ የገለጹት አቶ ማሞ በመጪዎቹ ዓመታት ያድጋል ተብሎ የሚጠበቀውን የንግድ እና የመዋዕለ-ንዋይ ክፍያዎች ለማመቻቸት ፋይዳ እንደሚኖረው ሁለቱ ባንኮች ባወጡት የጋራ መግለጫ ጠቁመዋል።

ብርቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት የሚፈትነው የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ካሉ ተቋማት ጋር እያካሔደ የሚገኘው ድርድር ሲጠናቀቅ ለችግሩ መፍትሔ ሊያበጅ የሚችል ጠቀም ያለ ገንዘብ ሊያገኝ እንደሚችል ይጠብቃል። የ2017 በጀት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀበት ስብሰባ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አዝጋሚው ድርድር ወደ መገባደዱ እየተቃረበ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው ጠቆም አድርገው ነበር።

ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ከዓለም ባንክ ጋር ላለፉት አምስት ዓመታት “ሰፊ ንግግር፣ ድርድር እና ውይይት ሲደረግ” መቆየቱን የጠቀሱት ዐቢይ “እኛም አስቸጋሪዎች፣ እነሱም አስቸጋሪዎች በመሆናቸው” መጓተቱን ለምክር ቤቱ አባላት አስረድተዋል። መንግሥታቸው ተግባራ በሚያደርጋቸው የኤኮኖሚ ማሻሻያዎች ላይ የሚደረገው ድርድር በየትኞቹ ጉዳዮች ላይ ልዩነት እንደተፈጠረ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመናገር ተቆጥበዋል። “አሁን አንዳንድ ወዳጅ አገሮቻችን ባደረጉልን ድጋፍ አብዛኛው ሐሳቦቻችን ተቀባይነት እያገኙ ይመስላል” ሲሉ ተናግረዋል።

የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ፕሬዝደንት ሼይክ ሞሐመድ ቢን ዛይድ አል ናሕያን
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ፕሬዝደንት ሼይክ ሞሐመድ ቢን ዛይድ አል ናሕያን ባለፉት ዓመታት ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጠበቅ ያለ ግንኙነት አበጅተዋል። ምስል picture alliance/Photoshot

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ማዕከላዊ ባንክ የክፍያ እና የመልዕክት መለዋወጫ ሥርዓቶችን ለማስተሳሰር፤ በድንበር ተሻጋሪ ክፍያዎች ብር እና ድርሐም የበለጠ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማድረግ ሁለት የመግባቢያ ሥምምነቶች ተፈራርመዋል። የመግባቢያ ሥምምነቱ ዓላማ የንግድ ክፍያዎች በብር እና በድርሐም እንዲከናወኑ ማመቻቸት፣ የፋይናንስ እና የባንክ ትብብሮችን ማጠናከር፣ የሁለትዮሽ ንግድ፣ ቀጥተኛ መዋዕለ-ንዋይ ማመቻቸት እና መረጃ እና እውቀት መለዋወጥ ናቸው።

ከዶላር የሚሸሸውን የብሪክስ ስብስብ የተቀላቀሉት የሁለቱ ሀገሮች ማዕከላዊ ባንኮች በተለይ በሁለትዮሽ የንግድ ልውውጣቸው ብር እና ድርሐምን ጥቅም ላይ ለማዋል የተፈራረሙት የመግባቢያ ሥምምነት ለኢትዮጵያ ላቅ ያለ ፋይዳ የሚኖረው ነው። የመግባቢያ ሥምምነቱ ወደ ተሟላ ሥምምነት ከተሸጋገረ በኢትዮጵያ እና በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች መካከል በሚደረግ የንግድ ልውውጥ የሦስተኛ የመገበያያ ገንዘብን አስፈላጊነት ሊያስወግድ ይችላል።

የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ማዕከላዊ ባንክ ገዥ ኻሊድ ሞሐመድ ባላማ የመገበያያ ገንዘብ ልውውጥ እና የመግባቢያ ሥምምነቶቹ በሁለቱ ሀገሮች መካከል በተለይም በንግድ እና በመዋዕለ-ንዋይ ዘርፎች ያለው ጠንካራ የኤኮኖሚ ትብብር ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል። ሞሐመድ ባላማ የኢትዮጵያን “የፋይናንስ መረጋጋት ለማጠናከር እና የጋራ ጥቅሞችን ለማሳካት” በቅርበት ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውንም ጠቁመዋል። የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ በበኩላቸው ሥምምነቶቹ ኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች አላቸው ያሉትን “ጥብቅ የሁለትዮሽ አጋርነት የበለጠ ለማሳደግ” ቁርጠኝነታቸው የታየበት እንደሆነ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ግንኙነት በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከስድስት ዓመታት ገደማ በፊት ሥልጣን ከያዙ ወዲህ ሲጠናከር ታይቷል። በሰኔ 2010 ሀገሪቱ የውጪ ምንዛሪ በርቶበት ለነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት አንድ ቢሊዮን ዶላር በብሔራዊ ባንክ ተቀማጭ ለማድረግ ቃል ገብታ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ከያዙ በኋላ በኢትዮጵያ እና በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች መካከል ያለው ግንኙነት ሲጠናከር ታይቷልምስል DW/N.Sirarak

ኢትዮጵያ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች መንግሥት በብሔራዊ ባንክ ተቀማጭ ያደረገውን አንድ ቢሊዮን ዶላር እስካሁን እንዳልከፈለ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ከሁለት ሣምንታት ገደማ በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተናግረዋል። በብሔራዊ ባንክ ተቀማጭ የተደረገው የአንድ ቢሊዮን ዶላር አከፋፈል ላይ የተደረገው ለውጥ “ትልቅ እፎይታ የፈጠረልን ነው” ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አንድ ቢሊዮን ዶላር ተቀማጭ ያደረገችው አንድ የአሜሪካ ዶላር በ28 ብር ገደማ በሚመነዘርበት ወቅት ነው። ከስድስት ዓመታት በኋላ በባንኮች የዶላር ምንዛሪ በእጥፍ ገደማ አሻቅቧል። በምንዛሪ ተመን ላይ የታየው ከፍተኛ ለውጥ ኢትዮጵያ ገንዘቡን ለተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች መልሶ ለመክፈል ያላትን አቅም በኃይል የሚፈታተን ነው። የኢትዮጵያ ይፋዊ አበዳሪዎች እና ቻይና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ጠቃሚ የዕዳ ክፍያ እፎይታ መስጠታቸው አይዘነጋም።

የሶማሌላንድ በርበራ ወደብ በኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ኤኮኖሚያዊ ትሥሥር ፈጥሯል። የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ንብረት የሆነው ዶፒ ወርልድ ኩባንያ የሚያስተዳድረው የሶማሌላንድ በርበራ ወደብ ከኢትዮጵያን የገቢ እና የወጪ ንግድ 30 በመቶ ለማስተናገድ ያቀደ ነው። ሶማሌላንድ እና ዲፒ ወርልድ የበርበራ ወደብን ለማስፋፋት ሲነሱ ኢትዮጵያ 19 በመቶ ድርሻ አግኝታ የነበረ ቢሆንም ሳትጠቀምበት ቀርታለች። ሴኔጋል፣ አልጄሪያ፣ ግብጽ እና ሞዛምቢክን በመሳሰሉ የአፍሪካ ሀገሮች ጭምር ወደቦች የሚያስተዳድረው ግዙፉ ዲፒ ወርልድ የሼይክ ሞሐመድ ቢን ዛይድ አል ናሕያን መንግሥት የተጽዕኖ መሣሪያ ሆኖ የሚያገለግል ተቋም እንደሆነ ይነገርለታል።

እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ