1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተከፈለ ካፒታል ከ500 ሚሊዮን ወደ 10 ቢሊዮን ብር ሊያድግ ነው

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ሰኔ 19 2016

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተከፈለ ካፒታል ወደ 10 ቢሊዮን ብር የሚያሳድግ ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል። “የዋጋ መረጋጋትን ለማረጋገጥ የገንዘብ ፖሊሲን ቀርጾ ተግባራዊ ማድረግ” የብሔራዊ ባንክ ዋና ዓላማ ነው። መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ የሚወስደው የብድር መጠን፣ የአከፋፈል ሁኔታ እና ወለድ የሚወስኑ ድንጋጌዎች ተካተውበታል

https://p.dw.com/p/4hXDO
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ
የባንኩ ገዥ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ ረቂቅ አዋጁ ብሔራዊ ባንክ “አንጻራዊ ተቋማዊ ነጻነት” እንዲኖረው የሚያደርግ መሆኑን ተናግረው ነበር። ምስል CC BY 2.0/U.S. Institute of Peace

የብሔራዊ ባንክን ካፒታል ከ500 ሚሊዮን ወደ 10 ቢሊዮን ብር የሚያሳድግ የአዋጅ ረቂቅ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን አዋጅ ከ16 ዓመታት በኋላ የሚያሻሽለው ረቂቅ ደንብ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደርሷል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ካቢኔ ሰኔ 7 ቀን 2016 ይሁንታ የሰጠው ረቂቅ ባለፈው ሣምንት ለምክር ቤቱ የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል። ረቂቁ ለኮሚቴው በተመራበት ስብሰባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ተስፋዬ በልጅጌ ነባሩ አዋጅ “ሕጋዊ እና አስተዳደራዊ ክፍተቶች” እንዳሉበት ተናግረዋል።

መንግሥት ለምክር ቤቱ ባቀረበው ማብራሪያ “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕጋዊ እና ተቋማዊ ማዕቀፍ” ከሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ ሁለተኛ ምዕራፍ “ዓላማዎች፣ ከዓለም አቀፍ በተለይም የባዝል ኮሚቴ እና የፋይናንስ መረጋጋት ቦርድ ካስቀመጧቸው መርሆች እና ከአቻ ማዕከላዊ ባንኮች ከተገኙ ልምዶች አኳያ ሲገመገም ሰፊ ክፍተቶች እንዳሉበት፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅትን ጨምሮ በቅርብ ጊዜያት የተካሄዱ የተለያዩ ጥናቶች” ማረጋገጣቸውን ያትታል። በሰነዱ የተጠቀሱት የባዝል ኮሚቴ እና የፋይናንስ መረጋጋት ቦርድ ዓለም አቀፍ የባንኮች ቁጥጥር እና ክትትል ሥርዓትን የሚመሩ ናቸው።

“በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ በየጊዜው ከሚኖሩ ለውጦች ጋር በሚጣጣም መልኩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ሥልጣን እና ተግባራት እንደገና በመወሰን የቁጥጥር አቅሙን ማጎልበት እንዲሁም የባንኩን ተዓማኒነት፣ ተጠያቂነት፣ ግልጽነት እና አስተዳደር ከዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎች ጋር በተጣጣመ መልኩ ማጠናከር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ” ረቂቁ መዘጋጀቱን አቶ ተስፋዬ በልጅጌ አስረድተዋል።

አንጻራዊ ተቋማዊ ነጻነት

ማሻሻያው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከ2016 እስከ 2018 ባሉት ዓመታት ተግባራዊ በሚያደርገው ስትራቴጂክ ዕቅድ ከተካተቱ ዐበይት ጉዳዮች አንዱ ነው። ከተቋቋመ 80 ዓመታት ገደማ ያስቆጠረው ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ግሽበትን በ2017 ሰኔ መጨረሻ ከ10 በመቶ በታች ዝቅ የማድረግ ዕቅድ አለው። 

ባለፉት ሣምንታት ባንኮች መንግሥትን ጨምሮ ለደንበኞቻቸው ብድር የሚሰጡበትን አሰራር ጠበቅ የሚያደርጉ መመሪያዎችን ሥራ ብሔራዊ ባንክ ላይ አውሏል። ባለሙያዎች ባንኩ መሰል ኃላፊነቶቹን ይወጣ ዘንድ “ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ” ሆኖ መሥራት እንደሚኖርበት ሲሞግቱ ቆይተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለመንግሥት የሚሰጠው ብድር ላይ ከ16 ዓመታት በኋላ አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ገደብ ጥሏልምስል Eshete Bekele/DW

የባንኩ አስረኛ ገዥ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ ረቂቅ አዋጁ ብሔራዊ ባንክ “አንጻራዊ ተቋማዊ ነጻነት” እንዲኖረው የሚያደርግ መሆኑን አስረድተው ነበር። በረቂቅ አዋጁ መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተጠሪነቱ እንደከዚህ ቀደሙ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው። በአሁኑ ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ግርማ ብሩ በሊቀ-መንበርነት የሚመሩት እና ሰባት አባላት ያሉት የዳይሬክተሮች ቦርድ አለው። አሁን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት እየተደረገበት በሚገኘው ረቂቅ አዋጅ ግን የቦርድ አባላት ቁጥር ወደ ዘጠኝ ከፍ እንዲል ተደርጓል።

ረቂቁ በሥራ ላይ በሚገኘው አዋጅ ያልነበሩ “ሥልጣን እና ተግባራት” ለብሔራዊ ባንክ ሰጥቷል። “የዋጋ መረጋጋትን ለማረጋገጥ የገንዘብ ፖሊሲን ቀርጾ ተግባራዊ ማድረግ” በአዲሱ ረቂቅ ለብሔራዊ ባንክ የተሰጠ “ዋና ዓላማ” ነው። “የፋይናንስ ሥርዓቱን መረጋጋት እና ጤናማነት ማረጋገጥ” ፣ “የሀገሪቱን አጠቃላይ የኤኮኖሚ ዕድገት መደገፍ” በሁለተኛ እና ሦስተኛ ተራ ቁጥር እንደ ቅደም ተከተላቸው የተቀመጡ የባንኩ ዓላማዎች ናቸው።

አሁን በሥራ ላይ ከሚገኘው አዋጅ በተለየ በረቂቅ ማሻሻያው ብሔራዊ ባንክ “ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመመካከር የዋጋ መረጋጋት ግብ የማስቀመጥ” ሥልጣንም ተሰጥቶታል። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጋር “የዋጋ መረጋጋትን ግብ ከተወሰነ በኋላ ባንኩ የዋጋ ማረጋጋት ግቡን ለማሳካት የመረጠዉን የገንዘብ ፖሊሲ ማስፈጸሚያ መሣሪያ የመጠቀም ሥልጣን” ይኖረዋል።

በሥራ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል 500 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ይደነግጋል። በአዋጁ መሠረት “አስፈላጊ ሆኖ በተገኘ ጊዜ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚወጣ ደንብ” የባንኩ ካፒታል ሊጨምር ይችላል።

ለአዲሱ ረቂቅ አዋጅ መንግሥት ያቀረበው ማብራሪያ ግን “የባንኩ የተከፈለ ካፒታል እና አጠቃላይ የመጠባበቂያ ፈንድ ከሌሎች ሀገራት ማዕከላዊ ባንኮች ጋር ሲነጻጸር በጣም ዝቅተኛ” እንደሆነ ያትታል። በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተከፈለ ካፒታል 10 ቢሊዮን ብር እንዲሆን ረቂቁ ይደነግጋል። ይኸ አሁን ባንኩ ካለው የተከፈለ ካፒታል በ20 እጥፍ የላቀ ነው።

በያይነቱ ጋሽ ክፍሌ ቤት እንጀራ
በረቂቅ አዋጁ “የዋጋ መረጋጋትን ለማረጋገጥ የገንዘብ ፖሊሲን ቀርጾ ተግባራዊ ማድረግ” የብሔራዊ ባንክ ዋና ዓላማ ነው።ምስል DW/E. Bekele Tekele

ከዚህ በተጨማሪ በረቂቁ ውስጥ ባንኩ ከዚህ ቀደም ያልነበረ “የተፈቀደ ካፒታል” እንዲኖረው የሚያደርግ ምክረ-ሐሳብ የተካተተበት ነው። ረቂቁ የብሔራዊ ባንክ የተፈቀደ ካፒታል 20 ቢሊዮን ብር እንደሚሆን ሐሳብ ቢያቀርብም “አሁን አገሪቷ ባለችበት የኢኮኖሚ ሁኔታ የብሔራዊ ባንክን የካፒታል መጠን በሚፈለገው መጠን ለማሳደግ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል” የሚል ሐሳብ በማብራሪያው ተካቶበታል።

የተፈቀደ ካፒታል በረቂቁ የተካተተው “አዋጁን ማሻሻል ሳያስፈልግ በጊዜ ሂደት ባንኩ የተከፈለ ካፒታሉን የተፈቀደ ካፒታል እስከሚደርስ ድረስ እያሳደገ የሚሄድበትን ሁኔታ ለመፍጠር” እንደሆነ ለምክር ቤቱ የቀረበው እና ዶይቼ ቬለ የተመለከተው ሰነድ ያብራራል። በረቂቅ አዋጁ የባንኩ የተፈቀደ ካፒታል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቦርድ “በሚወስነው መጠን እና መንገድ ሊጨምር እንደሚችል” ይደነግጋል።

ይኸ ረቂቅ አዋጅ ብሔራዊ ባንክ ለመንግሥት የሚሰጠው ብድር ላይ ከነባሩ አኳያ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣ ነው። ከ1955 እስከ 2000 ድረስ የነበሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ ሕጎች መንግሥት ከባንኩ በሚወስደው የብድር መጠን፣ የአከፋፈል ሁኔታ እና ወለድ ላይ “ግልጽ ድንጋጌ” ነበራቸው። ድንጋጌዎቹ ከ2000 ጀምሮ በሥራ ላይ ከሚገኘው ነባሩ አዋጅ እንዲወጡ መደረጉ “መሠረታዊ ችግር” እንደሆነ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበው ሰነድ ተገልጿል።  

የኢትዮጵያ ብር
ረቂቅ አዋጁ መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ የሚወስደው ብድር “ካለፉት ሦስት የበጀት ዓመታት አማካይ ዓመታዊ ጠቅላላ የመንግሥት የሀገር ውስጥ ገቢ ከ15 በመቶ መብለጥ” አይችልም የሚል ገደብ አኑሯል። ምስል MICHELE SPATARI/AFP

በቅርቡ ይጸድቃል ተብሎ የሚጠበቀው ረቂቅ አዋጅ ብሔራዊ ባንክ ለመንግሥት የሚሰጠው “በጥሬ ገንዘብ ፍሰት ላይ የተመሠረተ” ብድር ከ12 ወራት ባልበለጠ ጊዜ ተመላሽ የሚደረግ እንደሚሆን ይደነግጋል።  የብድር መጠኑ “ካለፉት ሦስት የበጀት ዓመታት አማካይ ዓመታዊ ጠቅላላ የመንግሥት የሀገር ውስጥ ገቢ ከ15 በመቶ መብለጥ” አይችልም። ከዚህ በተጨማሪ የብድሩ “የመክፈያ ጊዜው ሲደርስ ሊከፈል ይገባል እንጂ አይተላለፍም።” ብድሩ “በገንዘብ ፖሊሲ ተመን ላይ ተመሥርቶ የሚሰላ” ወለድ ይከፈልበታል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ “በቀጣይ የሒሳብ ዓመት ተጨማሪ” ብድር የሚሰጠው “ያልተከፈለው የኦቨር ድራፍት መጠን በተቀመጠለት የመክፈያ ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ የተከፈለ እንደሆነ ብቻ” ነው። ይሁንና የአዋጅ ረቂቁ “ከአቅም በላይ የሆነ ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ መንግሥት” “ከተመለከተው ገደብ በላይ የሆነ ብድር ከብሔራዊ ባንክ ሊጠይቅ” እንደሚችል ይፈቅዳል። ባንኩ ተጨማሪ ብድር ሊሰጥ የሚችለው “ያልተጠበቀ የማሕበረሰብ ጤና፣ የተፈጥሮ አደጋ፣ ድርቅ ወይም አግባብነት ያለውን ሕግ መሠረት አድርጎ የታወጀ አጠቃላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ” ሲኖር ብቻ እንደሆነ በረቂቁ ተደንግጓል።

“በፌዴራል መንግሥት ገቢ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ጉልህ የውጭ የኤኮኖሚ ለውጦች” ከተከሰቱ ብሔራዊ ባንክ ብድሩን ሊሰጥ እንደሚችል ረቂቁ ይፈቅዳል። በረቂቅ አዋጁ እንደሰፈረው ተጨማሪ ብድር የሚሰጠው “የብሔራዊ ባንክ የዋጋ መረጋጋትን የማረጋገጥ ዓላማ ሳይጣረስ፣ የፌዴራል መንግሥትን የመንግሥት ብድር ጣሪያ ባከበረ መልኩ” ይሆናል። ተጨማሪ ብድር የሚሰጠው “ብሔራዊ ባንክ በሚወስነው መሠረት በጊዜ የተገደበ እና በገበያ ተመን ወለድ የሚታሰብበት” እንደሚሆን ረቂቁ ይደነግጋል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ