1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ስፖርትሰሜን አሜሪካ

የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ

ሐሙስ፣ ሰኔ 15 2015

ፌዴሬሽኑ በየዓመቱ በተለያዩ የአሜሪካ ክፍለ ግዛቶች፣የእግር ኳስ ውድድርና የባህል ፌስቲቫል እንዲሁም የኢትዮጵያ ቀን ዝግጅቶችን ያካሂዳል።ዘንድሮ በአርባኛው የፌድሬሽኑ ክብረ በዓል ከፊታችን ሐምሌ ሁለት እስከ ስምንት ቀን የሚቆይ ትልቅ ዝግጅት ይዘው እንደሚቀርቡ፣ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚደንት አቶ አብይ ኑርልኝ ለዶቼቬለ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/4SxMt
USA | Mitglieder der ESFNA
ምስል The Ethiopian Sports Federation in North America

የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ በየዓመቱ የሚያካሂደው  የባህልና ስፖርት ፌስቲቫል ዘንድሮ ቴክሳስ ውስጥ ይካሄዳል።

ፌዴሬሽኑ፣በ40 ኛ ዓመት ክብረ በዓሉ፣ኢትዮጵያዉያንን ከማቀራረብና በመኻከላቸው  አንድነት ከመፍጠር አኳያ ፋይዳ ያለው ትልቅ ዝግጅት ማሰናዳቱን የፌዴሬሽኑ ስራ አመራሮች ለዶይቸ ቨለ ተናግረዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያን ቆጣጠር በ1984 የተመሰረተው የኢትዮጵያውያን ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ፣እጅግ የበለጸገውን የኢትዮጲያ ባህልና ቅርሳ ቅርሶች ማስተዋወቅን ዋነኛ ግቡ አድርጎ ይንቀሳቀሳል።

 ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተሰባስበው አንድ ላይ የሚገናኙበት ዓመታዊ  የስፖርትና የባህል ፌስቲቫል በማዘጋጀት፣ በመኻከላቸው አዎንታዊ   የሆነ አመለካከትን በማጎልበት ላይ የሚገኝ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ነው።

 

 ፌዴሬሽኑ በየዓመቱ በተለያዩ የአሜሪካ ክፍለ ግዛቶች፣የእግር ኳስ ውድድርና የባህል ፌስቲቫል እንዲሁም የኢትዮጵያ ቀን ዝግጅቶችን ያካሂዳል።

 ዘንድሮ በአርባኛው የፌድሬሽኑ ክብረ በዓል ከፊታችን ሐምሌ ሁለት እስከ ስምንት ቀን የሚቆይ ትልቅ ዝግጅት ይዘው እንደሚቀርቡ፣ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚደንት አቶ አብይ ኑርልኝ ለዶቼቬለ ተናግረዋል።

"ከእግር ኳስ ውድድሩ፣ ከስፖርት ዉድድሩ ከሩጫው በተጨማሪ የባህል ዝግጅቱ ነው በትልቁና በጉጉት የሚጠበቀው።ይህንን ዝግጅት ለማድመቅ ከአምስት ወራት በላይ እየተገናኙ፣በሳምንት ሁለትና ሦስት ቀናት ልምምድ እያደረጉ ጥሩ ጥሩ ዝግጅቶችን ለማዘጋጀት የደከሙበትን የሙዚቃ ባለሙያዎቻችንና የባህል ተጫዋቾቻችንን እናመሰግናለን።ለ40 ኛው ዓመት ደግሞ የተለየ ዝግጅት ነው የሚያቀርቡት ከሃገር ውስጥም ከአገር ውጭም ተሰባስበው ትልቅ ዝግጅት ይዘው የቀረቡት።"

እነዚህ መሰናዶዎች፣ኢትዮጵያዉያንን ከማቀራረብና በመኻከላቸው  አንድነት ከመፍጠር አኳያ ትልቅ ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው ነው የሚነገረው። 

ስፖርት የሰላም፣የአንድነትና የወዳጅነት መድረክ መሆኑን በማስመስከር ፌዴሬሽኑ አርአያነት ያለው ተግባር በማካሄድ ላይ መሆኑ በብዙዎች ዘንድ ይታመናል።

 ለኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ ምስረታ፣ በአሜሪካና በካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣የላቀ ድርሻ እንዳላቸው ይነግርላቸዋል።

 እዚህ አትላንታ፣ቦስተን፣ዳላስ፣ሂውስተን፣ሎስ አንጀለስና ዋሽንግተን ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የውድድሩ ፈር ቀዳጆች ሲሆኑ፣ የመጀመሪያው ዉድድርም ሂውስተን ውስጥ ነው የተካሂደው።

 የተነፋፈቁና የተጠፋፉ  ኢትዮጵያውያን የሚገናኙበትን ዓመታዊ ዝግጅት ስለማንነታቸው፣ባህላቸውና ሃገራቸው በጋራ ለመምከር መልካም አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል።

ስለሆነም በበርካታ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በዝግጅቱ ላይ ለመታደም ቀኑን በጉጉት ይጠብቁታል።

አቶ ዕያዩ ዘነበ የፌዴሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ናቸው።

"እዚህ ከተማችን ውስጥ እንግዲህ፣ሆቴሎቻችን እየሞሉ ነው ያሉት። ሦስት ሆቴልሎች ሞልተን አሁን አራተኛና አምስተኛ ደግሞ ሌላ ተስማምተን ድረ ገጻችን ላይ አውጥተናል።ሰው እዛ ላይ እየሄደ በቅናሽ የሚከራይበትን መንገድ ነው ያመቻቸነው።እና ትልቅ እንቅስቃሴ ነው ያለው ከዚህ ቀደም ተደርጎ በማያውቅ ደረጃ ብዙ አርቲስቶች እንደሚመጡ ነው ወደዚህ ወደ ዳላስ።"

ፌዴሬሽኑ አሰቃቂ በደል ደርሶባቸዋል ካላቸው ኢትዮጵያውያን ጎን እንደሚቆም ከዚህ ቀደም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

አሁንም ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዕርዳታ እንደሚያደርግ አቶ አብይ ይናገራሉ።

"በዚህ ዓመት ጠቅላላ  የቦርድ አባላትና የስራ አስኪያጅ ኮሚቴ ይነጋገሩና በየትኛው በኩል ዕርዳታ ማድረግ እንደሚገባን መክረን ዕርዳታ ለመስጠት ሁሌም ዝግጁ ነን።"

የዘንድሮው የፌዴሬሽኑ የክብር እንግዶች በመሆን ከኢትዮጵያ እንደሚመጡ የሚጠበቁት፣ከአስረኛው የአፍሪቃ ዋንጫ አንስቶ ለብሔራዊ ቡድን መሰለፍ የጀመረው በከሪ አደም፣ በአትሌቲክሱ ከተወዳዳሪነት እስከአሰልጣኝነት ስኬታማ የሆኑት ሻለቃ እሸቱ ቱራ እና ከልጅነቷ እግር ኳስ መጫወት ጀምራ ለፕሮፌሽናልነት የደረሰችው ሎዛ አበራ ናቸው።

ታሪኩ ኃይሉ

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ