የኢሰመኮ መግለጫ
እሑድ፣ መስከረም 8 2015ከትግራይ ክልልና አዋሳኝ የአማራ ክልል አካባቢዎች ተፈናቅለው በአዋሽ ሰባት የተያዙ 2800 ያህል ሰዎች የመንቀሳቀስ መብታቸው በአፋጣኝ እንዲከበርላቸው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጠየቀ።
ሰዎቹ ከሌሎች የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች በተለየ መልኩ ከሕግ አግባብ ውጪ እና የመንቀሳቀስ መብታቸው ተነፍጎ፣ የሰብአዊ ድጋፍ በበቂ ሁኔታ ሳይቀርብላቸው በጃሬ መጠለያ ጣቢያ ለበርካታ ወራት ተይዘው የቆዩ ናቸው ያለው ኮሚሽኑ ተፈናቃዮቹ የሚገኙበትን ሁኔታ ለመመልከት ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም ከመንግሥት አካላት አፋጣኝ ምላሽ አለማግኘቱን ተናግሯል።
ይህንኑ በተመልከተ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “በአዋሽ ሰባት የፌዴራል ፖሊስ ማሰልጠኛ ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮች የመጡባቸውን የትግራይ ክልል አካባቢዎች ብቻ መሰረት በማድረግ ለተራዘመ ጊዜ የመንቀሳቀስ ነጻነታቸውን ተነፍገው እንዲቆዩ መደረጉ የአስፈላጊነት፣ ምክንያታዊነት እና የተመጣጣኝነት መርሆዎችን የሚቃረን ነው” ማለታቸውን ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ ጠቅሶ እርምት እንዲደረግ ጠይቋል።
በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን ከጃሬ የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያ ወደ አዋሽ ሰባት የፌዴራል ፖሊስ ማሰልጠኛ እንዲዘዋወሩየተደረጉ ተፈናቃዮቹ የሚገኙበትን መጠለያ ከግንቦት ወር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን የተናገረው ኢሰመኮ በአብዛኛው የትግራይ ተወላጆች የሆኑ እና ከመሀል ትግራይ ከመቀሌ፣ አዲግራት፣ አክሱም፣ ሽሬ እና አካባቢው ተፈናቅለው የመጡ እና 2800 ያህል ናቸው ብሏል።
ኮሚሽኑ በክትትል ወቅት “የጸጥታ ሥጋት ሁኔታ እስከሚጣራ ድረስ" በሚል እንዲቆዩ የተደረጉ መሆናቸው የተነገራቸው ቢሆንም፤ ማጣራት ሳይደረግ ለረዥም ወራት በቂየሰብአዊ ድጋፍ በሌለበት እና ከእስራት ጋር በሚመሳሰልና ከቤተሰብ ለመገናኘት በማይቻልበት እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዲቆዩ መደረጋቸውን ተመልክቷል ሲሉ በኮሚሽኑ የሰብዓዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራ ክፍል ከፍተኛ ዳይሬክተር አቶ ይበቃል ግዛው ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
"ለተፈናቃዮች የምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሰብአዊ ድጋፎችን ለማቅረብ ጥረት ሲያደርግ የቆየው የፌዴራል አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ባለሙያዎች በአካባቢው የጸጥታ ኃይሎች እና ታጣቂዎች በደረሰባቸው ተጽዕኖ ሥራቸውን ለማቋረጥ መገደዳቸውንም" የኮሚሽኑ ሪፖርት ያሳያል።
በተጨማሪም "በወቅቱ መጠለያ ጣቢያው በመከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ሥር የነበረ በመሆኑ አጋር የሰብአዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች ድጋፍ ለማድረግ ተነሳሽነት ባለማሳየታቸው ተፈናቃዮች ለከፍተኛ የምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች እጥረት መዳረጋቸውን፣ እንዲሁም በመጠለያ ጣቢያው የሕክምና አገልግሎት ያልነበረ በመሆኑ የሕክምና እርዳታ ለማግኘት ጭምር በመጠለያ ጣቢያው የጸጥታ አካላት የበላይ ኃላፊዎች በሚሰጥ ፍቃድ ብቻ እና በክፍያ በሚደረግ እጀባ ለመንቀሳቀስ ተገድደው የነበረ መሆኑን" ኮሚሽኑ ባከናወነው ክትትል አረጋግጧል።
ኢሰመኮ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የፌዴራል እና የክልል መንግሥት ተቋማት የሁኔታውን አሳሳቢነት በመግለጽ "ተፈናቃዮቹ በሕግ አግባብ በቁጥጥር ስር የዋሉ ባለመሆናቸው የመንቀሳቀስ መብታቸው ሊረጋገጥላቸው የሚገባ መሆኑን፤ ከመካከላቸው የጸጥታ ሥጋት ናቸው በሚል በምክንያታዊነት የሚጠረጠሩ ሰዎች ካሉ የመለየት፣ የመመርመር እና በሕግ አግባብ ተጠያቂ የማድረግ ሥራው ግልጽ እና ሕጋዊ በሆነ መንገድ እንዲፈጸም ሲጠይቅ ቆይቷል" ያለው የኮሚሽኑ መግለጫ ይሁንና በተፈናቃዮች ሁኔታ ላይ ተጨባጭ መሻሻል ሳይታይ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በቅርቡ በድጋሚ መቀስቀሱን ተከትሎ አዋሽ ሰባት ወደሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ ማሰልጠኛ ተቋም እንዲዘዋወሩ መደረጋቸውን ኮሚሽኑ አረጋግጧል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “በአዋሽ ሰባት የፌዴራል ፖሊስ ማሰልጠኛ ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮች የመጡባቸውን የትግራይ ክልል አካባቢዎች ብቻ መሰረት በማድረግ ለተራዘመ ጊዜ የመንቀሳቀስ ነጻነታቸውን ተነፍገው እንዲቆዩ መደረጉ የአስፈላጊነት፣ ምክንያታዊነት እና የተመጣጣኝነት መርሆዎችን የሚቃረን ነው” ብለዋል ሲል ኮሚሽኑ በመግለጫው ጠቅሷል።
ሰሎሞን ሙጬ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር