1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ሰላምና የአሜሪካ አቋም

ዓርብ፣ መስከረም 27 2015

አምባሳደር ማይክ ሐመር፣በኢትዮጵያ ተፋላሚ ኀይላት መኻከል የሰላም ድርድር እንዲጀመር ድጋፍ ለማድርግ በተገባደደው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ወደ ኬንያ፣ደቡብ አፍሪቃና ኢትዮጵያ መጓዛቸው ይታወቃል።

https://p.dw.com/p/4HuX2
National Security Council Spokesman Mike Hammer
ምስል ORLANDO SIERRA/AFP

የአምባሳደር ማይክ ሐመር ማብራሪያ ሥለ ኢትዮጵያ ጦርነት

          

ኢትዮጵያ ዉስጥ ሰላም እንዲሰፍን ዩናይትድ ስቴትስ አበክራ እየጣረች መሆኑን  በአፍሪቃ  ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ አስታወቁ።ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር የኢትዮጵያ ተፋላሚ ኃይላትን ለመሸምገል ባገባደድነዉ ሳምንት ዳግም ወደ አፍሪቃ  ተጉዘዋል።አምባሳደሩ ትናንት ከሚገኙበት ኬንያ የምስራቅ አፍሪቃ በዉጪ የሚኖሩ ሴቶች ባዘጋጁት የበይነ መረብ ዉይይት ላይ እንዳሉት የኢትዮጵያ ጦርነት ቆሞ ሕዝቡ በልማትና ብልጽግና ላይ እንዲያተኩሩ አሜሪካ ትሻለች ።

አምባሳደር ማይክ ሐመር፣በኢትዮጵያ ተፋላሚ ኀይላት መኻከል የሰላም ድርድር እንዲጀመር ድጋፍ ለማድርግ በተገባደደው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ወደ ኬንያ፣ደቡብ አፍሪቃና ኢትዮጵያ መጓዛቸው ይታወቃል።ልዮ መልዕክተኛው ትናንት ከሚገኙበት ኬንያ፣ሴቶች ለሰላም በሚል መርዕ፣ በኢትዮጵያና አፍሪቃ ቀንድ ሰላም ላይ ያተኮረ በውጭ የሚገኙ ሴቶች የበይነ መረብ ውይይት ላይ ተጋብዘው ንግግር አድርገዋል።በዚሁ ወቅት አምባሳደሩ፣ሴቶች የዐለም ሕዝብ ቁጥር እኩሌታውን የመያዛቸውን ያህል ሠላም ለማስፈን የሚኖራቸው ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የሰላም ለሴቶች ውይይት ተሳታፊዎች፣የተለያየ አመለካከቶችን በማንሸራሸር ችግሮች የሚፈቱበት መንገድ ላይ የንግግር መድረክ ማካሄደቸውን ልዩ ልዑኩ አድንቀው በቀጣይም አብረዋቸው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸውላቸዋል።የጆሴፍ ባይደን አስተዳደር፣በኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት ቆሞ፣ሰላም ለማስፈን ቁርጠኛ አቋም ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን እና ለዚህም አሜሪካ በአፍሪቃ ህብረት ጥላ ስር የሚካሄደውን ሂደት እንደምትደግፍ ፣አምባሳደር ሐመር በድጋሚ አረጋግጠዋል።"ዮናይትድ ስቴትስ አፍሪቃ ህብረት መራሹን ሂደት ትደግፋለች።ይህ ውይይት ዘላቂ ሰላም እንደሚያስገኝም ተስፋ እናደርጋለን።"የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ መግለጫ

አሜሪካ ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ በሚለውን መርሕ ላይ የተመሠረት ትብብር፣ከአህጉሩ ጋር እንዲኖራት እንደምትፈልግም አመልክተዋል።ኢትዮጵያን በተመለከተ ዩናይትድ ስቴትስ የምትከተለውን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በተመለከተም ሲናገሩ፣"አሜሪካ የኢትዮጵያን አንድነት፣የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊነት ትደግፋለች።" የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በተለይ በሴቶችና ህጻናት ላይ እያደረሰ ባለው ጉዳት ላይ አትኩሮ በተካሄደው ውይይት ላይ ኢትዮጵያውያን ጥላቻን አርቀው በውይይት ችግሮቻቸውን መፍታት አለባቸው ያሉት አምባሳደር ሐመር ወታደራዊ እርምጃ መፍትሔ እንደማያመጣ አስገንዝበዋል።

"በሰሜን ኢትዮጵያ በሚካሄደው ጦርነት ወታደራዊ መፍትሔ የለም።ስቃይን የሚያባብሰው ሁከት በአስቸኳይ መቆም ይኖርበታል::"አለመግባባትን ለማስወገድ በመከባበር ላይ የተመሠረተ ውይይት ጠቃሚ ነው ያሉት ልዩ ልዑኩ በዚህ መንፈስ የተለያዩ አመለካከት ያላቸው አካላትን ለመስማትና ለማስተናገድ ምንጊዜም ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።የምስራቅ አፍሪቃው ልዮ ልዑክ፣በቀጣናው የሠላም ጥረት አሜሪካን ወክለው በመሣተፋቸው በግላቸው ክብር እንደሚሰማቸው ገልጸው በየዕለቱ ያላቸውን ጊዜ ይህንኑ ጥረት ለማሳካት እየተጠቀሙበት እንደሆነ አመልክተዋል።ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከንን ጨምሮ በየደረጃው ያሉ የአስዳደሩ ባለስልጣናት፣በኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት ቆሞ ሕዝቡ በልማትና ብልጽግና ላይ እንዲያተኩር ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ እንደሆኑም አረጋግጠዋል።የአሜሪካ የአፍሪቃ ልዩ መልክተኛ ከኢትዮጵያዉያን ጋር ተወያዩ

በውጭ ሃገር የሚኖሩ የምስራቅ አፍሪቃ ሴቶች ህብረት ባዘጋጀው በዚሁ ውይይት ላይ ከተለያዩ ተቋማት የተወከሉ ሴቶች ተሳትፈውበታል።ከእነዚሁ መኻከል የአዲስ ስታንዳርድ መጽሔት ዋና አርታዒ ፀዳለ ለማ፣በኢትዮጵያ በቀጠለው ጦርነት ዋነኛ ሰለባ እና ገፈት ቀማሽ ሴቶችና ህጻናት መሆናቸውን ገልጻለች።የምስራቅ አፍሪቃ በውጭ የሚኖሩ ሴቶች ህብረት፣በቀጣናው ሰላም፣መረጋጋት፣ፍትሕ፣ አንድነት እንዲሁም ኢኮኖሚ ላይ የሚሰራ መሆኑ በውይይቱ ላይ ተነስቷል።

ታሪኩ ኃይሉ

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ