1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ዕድገትና እና ተግዳሮቱ

ዓርብ፣ ሰኔ 30 2015

የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ከስድስት በመቶ በላይ እደገት እያስመዘገበ መሆኑን ይገልጻል። ይሁንና ኢኮኖሚው ግጭትና አለመረጋጋቱ እንዲሁም ሙስና እና ሥራ አጥነቱ በተንሰራፋበት ሁኔታ በከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ችግር እየተፈተነም ይገኛል።

https://p.dw.com/p/4Tb41
Äthiopien landwirtschaftliche Erzeugnisse auf einem Markt
ምስል DW/M. Haileselassie

የኤኮኖሚ ተንታኝ አስተያየት

የኢትዮጵያ የቀጣይ ዓመት በጀት በጸደቀበት በትናንትናው ዕለት በተካሄደው የኢትዮጵያ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በጉልህ የመሟገቻ ሃሳብ ሆነው ከተነሱ ነጥቦች አንደኛው ስለ ኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብታዊ እድገትና ውስንነቶቹ ነው። በዚህ የፓርላማ ውሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከአምስት ዓመታት በፊት ከነበረበት ደረጃ አንጻር አሁን አመርቂ እመርታ እያሳየ ነው በማለት የእድገት ምጣኔውም ከስድስት በመቶ በላይ መሆኑን አንስተው ሞግተዋል። ቁጥራዊ አሃዞችንም ጠቃቅሰው በማስረጃነት ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከምሥራቅ አፍሪቃ ቀዳሚ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪቃ ሃገራት ደግሞ ከደቡብ አፍሪካ እና ናይጀሪያ በመቀጠል ሦሥተኛ ግዙፍ ኢኮኖሚ ለመሆን መብቃቱንም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ይበሉ እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የዋጋ ግሽበትን ጨምሮ በኢኮኖሚው ላይ ያሉ ተግዳሮቶች ሰፊውን ማኅበረሰብ ሲያስመርር ይስተዋላል። እያደገ ነው የተባለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ስለምን የእድገቱ ተቋዳሽ ሊሆን የሚገባውን ዜጎቹን ፈተነ የተባሉት የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኝ አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን፤ ሦሥት መሠረታዊ ምክንያቶችን አንስተዋል። «የህዝብ ቁጥር መጨመር፣ ከህዝብ ቁጥሩ የተነሳ የፍላጎት መናር እና ይህ የህዝብን ቁጥር የሚመጥን አቅርቦት አለመኖር ነው ፈተናው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥታቸው አመጣ ያሉት ቁጥሮች ላይ ብቻ ያተኮሩ ይመስላል።»

Äthiopien Hawassa Industrial Park
የኢትዮጵያ ኢንደስትሪ ፤ የሀዋሳ ኢንደስትሪ ፓርክምስል AFP/E. Jiregna

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በርግጥ ምጣኔ ሃብታዊ እድገቱ በዋጋ ግሽበት ክፉኛ መታወኩን አልሸሸጉም። ለዚህ ደግሞ እንደ ዋናው ምክንያት ያነሱት ዓለም አቀፋዊ ወቅታዊ ሁኔታን ነው። ከዋጋ ግሽበቱ በተጨማሪ ሙስና እና ብልሹ አሰራሮች ሌላው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የኢ-ፍትሃዊነት ምንጭ ሆኖ ይጠቀሳል። የፖሊቲካል ኢኮኖሚ ተንታኙ አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን ግን ጤነኛ የእድገት ሞዴልን የሚከተል ኢኮኖሚ አጠቃላይ ማኅበረሰቡ ላይ በተለይም በሰፊው ህዝብ ላይ ተጨባች ለውጥን የሚያሳይ ነው ይላሉ።

«የኢኮኖሚ እድገት መጣ የሚባለው ሲሆን ሲሆን ህዝብ ከሚጠቀመው ተርፎለት ለአቅመ ቁጠባ ሲበቃ ነው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ግን ወጪ ገቢው ሚዛናዊ ሲሆን ነው፡፡ አለዚያ ግን ውስን ሰዎች ሃብታም አብዛኛው ህዝብ ደሃ ሲሆን መጥፎ የኢኮኖሚ እድገት ይባላል።» በማኅበረሰቡ ሕይወት ላይ ትክክለኛ ለውጥን የሚያመጣ ለአገሪቱ ትክከለኛው የኢኮኖሚ ሞዴል የትኛ ይሆን፤ ኢትዮጵያስ የትኛውን የኢኮኖሚ መስመር እየተከተለች ነው የተባሉት የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኙ፤ አገሪቱ እየተከተለች ያለው የኢኮኖሚያዊ እድገት ሞዴል ጥርት ተደርጎ መገለጹን ይጠራጠራሉ።

Äthiopien Währung Birr
የኢትዮጵያ መገበያያ ሸርፍ፤ ብርምስል DW/Eshete Bekele Tekle

«ኢትዮጵያ በእርግጥ የትኛውን የኢኮኖሚ ሞዴል እንደምትከተል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጽሐፋቸው ከገለጹት ሌላ በውል የሚታወቅ አይመስለኝም። ግን ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር የኢኮኖሚ ልዩነቱ በመስፋት ቀውስ እንዳያስከትል ቅይጥ የኢኮኖሚ እድገት ሞዴል መከተሉ ሳያስፈልግ አይቀርም።» በኢትዮጵያ አለመረጋጋት በሚስተዋልበት ባሁኑ ወቅት በየዓመቱ አዲስ ሥራ ፈላጊ ሆኖ ብቅ የሚለውን ሦሥት ሚሊየን ገደማ ወጣትን ወደ ሥራ ማስገባት በሚቻልበትና በሥራ እጦት ምክንያት የወጣቱ የግጭት ተሳትፎ እንዳይባባስ መንግሥታቸው ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በትናንቱ የምክር ቤት ውሎ ጠቁመዋል።

ሥዩም ጌቱ 

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ