1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለኦሮሚያው የጸጥታ ችግር የሦስተኛ ዙር ድርድር እድል

ሰኞ፣ ጥር 20 2016

በኢትዮጵያ መንግሥትና መንግስት ‘ሸኔ’ በሚል ስም በሽብርተኝነነት በፈረጀው እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) ባለው ታጣቂ ቡድን መካከል ተጀምሮ ያለ ስምምነት የተቋጨውን የሰላም ንግግር ለመቀጠል መንግሥት ዝግጁ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡

https://p.dw.com/p/4bnyW
ኦሮሚያ ክልል ያለ መንገድ
ኦሮሚያ ክልል ያለ መንገድምስል Seyoum Getu/DW

የሦስተኛ ዙር ድርድር እድል

“የህብረተሰቡን ባህል፣ ታሪክና እምነት ማዕከል ባደረገ መልኩ የሰላም ስራዎች በደንብ እንዲሰሩ የተጀመሩ የሰላም በሮች ክፍት ሆነው እንዲቀሩ አቅጣጫ ተቀምጦለታል፡፡”
ሰላማዊ ድርድር እንደ ቀዳሚ አማራጭ
በሳምንቱ መጨረሻ በብሔራዊው የኢትዮጵያ ቴሌቬዢን ጣቢያ ቀርበው በኦሮሚያ ክልል ስላለው የጸጥታው መደፍረስ እና እልባቱን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ ከዚህ ቀደም በታንዛኒያ በመንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል ተጀምሮ ያለ ስምምነት የተጠናቀቀውን የሰላም ንግግር ለመቀጠል በመንግሥት በኩል አሁንም ዝግጁነት መኖሩን አስረድተዋል።
ለመንግሥት ሰላም የማስፈን ስራ ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው ያሉት አቶ ሽመልስ፤ የሰላም እጦት መንግሥት ለመልካም አስተዳደር እና ለልማት መረጋገጥ ሊያውለው የሚገባውን ጊዜ፣ ሀብት እና የሰው ኃይል በእጅጉ እንደሚጎዳውም አልሸሸጉም።
“መንግስት ሰላም የማስፈን ጉዳይን ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የመሚሰጠው ነው፡፡ ሰላም ከሌለ መንግስት ለልማት እና ለመልካም አስተዳደር ያለውን ሃብትና ጊዜ ስለሚሻማበት ጎታች ይሆናል፡፡ ስለዚህ መንግስት ለሰላም ያለው ቁርጠኝነት የማያወላዳ ነው ማለት ነው፡፡ ከታጠቁ አካላት ጋር የሚደረግ ድርድር ከዚህ ቀደም በከፊል ውጤት አምጥተዋል፡፡ ከሸነ ጋር የተጀመረውን ድርድርም በህገመንግስቱ መሰረት መንግስት ችግሩን ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው፡፡ ሂደቱ በተንጸባረቀው ኢ-ህገመንግስታዊ ፍላጎት ተገቷል፡፡ ነገር ግን አሁንም የሚዘጋ ጉዳይ ነው ማለት አይቻልም፡፡ አሁንም መንግስት ለመደራደር ዝግጁ ነው፡፡ ይህን ነገር መንግስት አደራዳሪዎቹም ባሉበት ግልጽ አድርጓል፡፡ ታጣቂዎቹ አልባለ ፍላጎታቸውን ገትተው ወደ ድርድሩ እንዲመጡ መንግስት ዝግጁ መሆኑንና ይህንኑን ጥሪ ማቅረብ እፈልጋለሁ” ብለዋል አቶ ሽመልስ በሰጡት ሰፊ ማብራሪያ፡፡
በዚሁ በርዕሰመስተዳድሩ አስተያየት ላይ በሽምቅ ውጊ መንግስትን ከሚወጋው እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ካለው ታጣቂ ቡድን የተሰጠ አስተያየት አልተሰማም፡፡ በኢትዮጵያ መንግስት እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል ለሁለት ዙር በታንዛንያ የተካሄደው የሰላም ድርድር መደናቀፉን ተከትሎ ከዚህ ቀድም የአገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላም ተመሳሳይ ይዘት ያለውን ማብራሪያ መስጠታቸው ግን አይዘነጋም፡፡ 

ጉጂ ዞን
ጉጂ ዞንምስል Private

የሰላም እጦቱ መዘዝ

በኦሮሚያ ክልል እልባት አልባ ሆኖ ለአምስት ዓመታት ገደማ የቀጠለው እና በጉልህ የተስፋፋው የሰላም እጦት ግን መዘዙ እየከፋ ነው በሚል ከማህበረሰቡ ዘንድ በጉልህ ይንጸባረቃል፡፡ በሰላም ላይ የሚሰራውን ኢኒሼቲቭ ፎር ቼንጅ የተባለውን ተቋም የሚመሩት አቶ ገረሱ ቱፋ ለዶቼ ቬለ በሰጡት አስተያየትም ያሉትን መሰረታዊ የሰላም እጦቶች ለመፍታት ሂደቱ ከዚህ በላይ መግፋቱ መመለሻውን አስቸጋሪ ሊያደርግ እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ፡፡
“ግጭቱ ባለፉት አምስት ዓመታት በህዝቦች ትስስር ላይ ይሁን በኢኮኖሚው ላይ አልባሌ ተጽእኖ አሳርፏል፡፡ ሰዎች ከቦታ ቦታ ሄደው መማር፣ ማረስ፣ ህክምና ማግኘት እና መነገድ አዳጋች ሆኗል፡፡ በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ደግሞ ማህበረሰብ እየቆየ ሲሄድ ወንጀልና የሚሞት፤ የሚሰቃይ ሰው እየበዛ ነገሮች እየተበላሹ ስለሚሄዱ ከዚህ ግጭት በፍጹም ትርፍ አይገኝም፡፡ አሁን በሁለቱም በኩል ያሉ ወገኖች፤ ለህዝብ እንቆረቆራለን ካሉ ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ነው ማድረግ ያለባቸው፡፡ የህዝቡን ሁኔታ በደንብ ነው ማየት ያለባቸው” ብለዋል፡፡
“የህግ የበላይነት” የማስከበር ውጥን
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በሰሞነኛው ቃለምልልሳቸው እንዳብራሩት በክልላቸው ሰላምን ለማስፈን ተከፍቷል ካሉት የሰላም በር ባሻገር፤ በክልል ደረጃ ፖሊስ በብቁ ሁኔታ እንዲደራጅ የማድረግ እና የማጠናከር ስራ መሰራቱን ነው ያመለከቱት።

“የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የጸጥታ አካላት አስደናቂ ስራ እየሰሩ ነው” ያሉት ርዕሰመስተዳድር ሽመልስ፤ በጸጥታ ዘርፉ እየተከናወነ ያለውን ይህን ተግባር በፖለቲካ የመደገፍ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ውሳኔ ተላልፏል በማለት ሃሳባቸውን አክለዋልም።
ብልጽግና ፓርቲ ካለፈው ሳምንት መጀመሪያ እስከ አርብ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ ያካሄዳቸውን የስራ አስፈጻሚ እና የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባዎችን ሲያጠናቂቅ ባወጣው መግለጫም፤ “ዓላማቸው በነፍጥ ፍላጎታቸውን ማስፈጸም የሆኑ” ያላቸው አካላት ላይ፣ “ህግን የማስከበር ስራ በተጠናከረ መንገድ እንዲካሄድ” ውሳኔ ማስተላለፉን አሳውቆ ነበር። 
ሥዩም ጌቱ

ልደት አበበ

አዜብ ታደሰ