1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ መልሶ ግንባታ ዕቅድ በአንዳንድ አካባቢዎች “ሰላም መደፍረስ መስተጓጎል” ገጥሞታል

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ግንቦት 21 2016

የኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ብድር 65 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ተናግረዋል። ወደ 1.2 ትሪሊዮን ብር ያሻቀበው የሀገር ውስጥ ብድር ጫና እና ክምችት እየከፋ ሊሔድ እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል። ኢትዮጵያ በጦርነት የወደመውን መልሶ ለመገንባት የተጀመረችው ጥረት በታቀደው ፍጥነት ተግባራዊ አልሆነም።

https://p.dw.com/p/4gPmb
የገንዘብ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት
“በአንዳንድ አካባቢዎች“ ባለ ”የሰላም መደፍረስ” የገንዘብ ሚኒስቴር በበላይነት የሚመራውን በጦርነት የወደመውን መልሶ የመገንባት ዕቅድ “የማስተጓጎል ነገር” መኖሩን አቶ አሕመድ ሽዴ ተናግረዋል። ምስል Eshete Bekele/DW

የኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ብድር 65 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል

የገንዘብ ሚኒስቴር በበላይነት የሚመራው የኢትዮጵያ በጦርነት የወደመውን መልሶ የመገንባት ዕቅድ አተገባበር ባለፈው ሣምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን በጀት እና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጥያቄ ተነስቶበታል። ኮሚቴው እና አባላቱ በዕቅዱ ላይ ጥያቄ ያቀረቡት አቶ አሕመድ ሽዴ የገንዘብ ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ይዘው ወደ ምክር ቤቱ ብቅ ባሉበት ወቅት ነው።

የመሥሪያ ቤቱን የዘጠኝ ወራት ሪፖርት የተመለከተው ቋሚ ኮሚቴ “በሪፖርቱ የተመላከተው እስካሁን የተሠራው የመልሶ ግንባታ ሥራ ከችግሩ አስከፊነት አኳያ በቂ ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም” በማለት ተችቷል።

አቶ አሕመድ ገንዘብ ሚኒስቴር ያቋቋመው የመልሶ ግንባታ ቡድን ሥራ መጀመሩን፤ ግጭት በነበረባቸው በአብዛኞቹ ክልሎች የመልሶ ማቋቋም ተቋሞች ተመስርተው በመሥሪያ ቤታቸው አስተባባሪነት “አቅማቸውን የመገንባት ሥራ” እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በአምስት ክልሎች በተመረጡ ወረዳዎች በዓለም ባንክ 328 ሚሊዮን ዶላር በጀት የመልሶ ግንባታ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። በግጭት ለተጎዱ አነስተኛ እና ጥቃቅን ተቋማት መልሶ ማቋቋሚያ የተመደበውን ጨምሮ ጀርመን ለሁለት ፕሮጀክቶች የሰጠችውን 47 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ በማሳያነት አንስተዋል።

በ2016 የመጨረሻ ወራት ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ አስፈትቶ በመበተን ወደ መደበኛ ሕይወት እንዲመለሱ የማድረግ ዕቅድ ለመልሶ ግንባታ በተመደበው በጀት የሚከናወን ነው።

“ከዚሁ በጀት 75,000 የሚሆኑ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ ሰላማዊ ሁኔታ የሚመለሱበትን ሥራ ለመጀመር የሚያስችል የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ በእኛ በኩል ዝግጅት እያደረግን ነው የሚገኘው” ያሉት የገንዘብ ሚኒስትሩ ከልማት አጋሮች ከ45 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ለተሐድሶ ኮሚሽን መሰብሰቡን አስረድተዋል።

የትግራይ ተዋጊዎች
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ እንዳሉት 75,000 የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ አስፈትቶ በመበተን ወደ መደበኛ ሕይወት እንዲመለሱ ለማድረግ የተያዘው ዕቅድ በጦርነት የወደመውን መልሶ ለመገንባት በተመደበው በጀት የሚከናወን ነው። ምስል YASUYOSHI CHIBA/AFP

የኢትዮጵያ መንግሥት ፊቱን ወደ መልሶ ግንባታ በይፋ ያዞረው ደም አፋሳሹን ጦርነት ያቆመ ሥምምነት በደቡብ አፍሪካ በተፈረመ በሰባተኛ ወሩ ገደማ ነው። በሰኔ 2015 የገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው ሰነድ ሀገሪቱ በጦርነት ምክንያት የ28.7 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ እንደደረሰባት ይፋ አድርጓል። በጦርነት የወደመውን መልሶ ለመገንባት በወቅቱ ስሌት መሠረት 19 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተገምቷል።

አቶ አሕመድ ግን “አንዳንድ በወቅቱ በደንብ ተደራሽ ያልነበሩ አካባቢዎች” በመኖራቸው የደረሰው ኪሳራ እና ለመልሶ ግንባታ የሚያስፈልገውን ገንዘብ በተመለከተ የተሠራው ግምገማ በመከለስ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል። መንግሥታቸው ለመልሶ ግንባታ የተነሳው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ቆሞ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች በግጭት በሚታመሱበት ወቅት ነው።

አቶ አሕመድ በዝርዝር ከመናገር ቢቆጠቡም “በአንዳንድ አካባቢዎች” ባለ “የሰላም መደፍረስ” የመልሶ ግንባታ ሥራውን “የማስተጓጎል ነገር” መኖሩን ጠቁመዋል። አቶ አሕመድ በመልሶ ግንባታ ረገድ የተከናወኑ ሥራዎችን ቢጠቃቅሱም መልሳቸው ግን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ለሆኑት አቶ ደበበ አድማሱ “የሚያረካ” አልነበረም።

“ይኸ 20 ቢሊዮን ብር በጀት ሲያዝ በዚህ በመንግሥት በጀት የሚሠሩ ሥራዎች ቀድመው ተለይተው ነው ብዬ አስባለሁ። አምናም ተያዘ አልተጠቀምንበትም፤ ዘንድሮም ተያዘ አልተዘቀምንበትም“ ያሉት አቶ ደበበ አድማሱ “ይኸ ተገቢ ነወይ?” ሲሉ ጠይቀዋል። “በያዝናት በጀት ልክ የተወሰነውን አካባቢ ችግር መፍታት የሚቻልበትን ዕድል ለምን መጠቀም አልቻልንም?” ሲሉም አክለዋል።

የመልሶ ግንባታ ዕቅዱ ተጨማሪ በጀት እና የማጽፈጸም አቅም እንደሚፈልግ የተናገሩት አቶ አሕመድ በሚቀጥለው ዓመት “ወደ ሥራ የሚገባ ይሆናል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። “መዘግየት አለ የተባለውን የምንወስደው ነው” ያሉት የገንዘብ ሚኒስትሩ “የዘገየበት ምክንያት ግን የሐብት ማሰባሰብ እና የቅድመ ዝግጅት ሥራ በተሟላ መልኩ ማለቅ አለበት” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

አቶ አሕመድ ሽዴ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት ሪፖርት ባለፉት ዘጠኝ ወራት የሀገሪቱ ምጣኔ ሐብት የነበረውን አጠቃላይ ይዞታ የተመለከተ ጭምር ነው። በሪፖርቱ መሠረት በዘጠኝ ወራት የፌድራሉ መንግሥት 356.5 ቢሊዮን ብር ገቢ ሰብስቧል። ከዚህ ውስጥ 331 ቢሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ የተሰበሰበ ነው።

የኢትዮጵያ ብር ሽንኩርት እና ድንች ተራ
በዘጠኝ ወራት የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት 139.2 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት የገጠመው ሲሆን 57 ቢሊዮን ብር የቀጥታ ብድር ከብሔራዊ ባንክ ወስዷልምስል Eshete Bekele/DW

ከአንድ ዓመት በፊት በሥራ ላይ በዋለው የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ 15.3 ቢሊዮን ብር በዘጠኝ ወራት ውስጥ እንደተሰበሰበ አቶ አሕመድ ሪፖርት አድርገዋል። የፌድራል መንግሥቱ በዘጠኝ ወራት ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች 425.9 ቢሊዮን ብር ማሠራጨት የበረበት ቢሆንም የተሳካለት ግን 309 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው።

“የፌድራል መሥሪያ ቤቶች በተወሰነ ደረጃ ሙሉ በሙሉ የተመደበላቸውን በጀት እያስተላለፍን አይደለም” ያሉት አቶ አሕመድ “ገቢያችን አንዳንድ ጊዜ በሚቀንስበት ጊዜ ወጪ ያዝ የማድረግ ሥራ ስለምንሰራ ነው” ሲሉ ምክንያቱን ገልጸዋል።

የፌድራል መንግሥቱ በዘጠኙ ወራት 157.6 ቢሊዮን ብር ለክልል መንግሥታት የበጀት ድጋፍ እንዲሰጥ ቢታቀድም የተከፈለው ግን 163.1 ቢሊዮን ብር ሆኗል። ክፍያው ከታቀደው በ5 በመቶ ገደማ የጨመረው የበጀት ዕጥረት ላለባቸው ክልሎች ከቀጣይ ወር በሚሰጥ ብድር ምክንያት እንደሆነ አቶ አሕመድ አስረድተዋል።

በዘጠኝ ወራት የፌድራል መንግሥቱ 139.2 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት ገጥሞታል። በ2015 የመጀመሪያ ዘጠኝ ወራት መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ 147 ቢሊዮን ብር የቀጥታ ብድር መውሰዱን ያስታወሱት አቶ አሕመድ በተያዘው ዓመት ግን 57 ቢሊዮን ብር እንደሆነ አስረድተዋል።

“ግሽበት እንዳይባባስ ከመንግሥት የግምዣ ቤት ሰነድ እና ከትሬዠሪ ቢል ወደ 88.7 ቢሊዮን ብር ለበጀት ጉድለት መሸፈኛ ተጠቅመናል” ብለዋል።

“አጠቃላይ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ብድር 65.7 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ጥምርታ 40.2 በመቶ ነው” ያሉት አቶ አሕመድ “በሀገራችን ያለው ዋና ሥጋት የዕዳ ክፍያ ከኤክስፖርት ጋ ሲነጻጸር የተፈጠረ እንጂ የዕዳ መጠኑ ከአጠቃላይ ሀገራዊ የምርት መጠን አኳያ እየቀነሰ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው” ሲሉ ተደምጠዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተወሰነ ደረጃ የሀገር ውስጥ ብድር እያደገ” መሆኑን ተናግረዋል። ለሀገር ውስጥ ብድር ዕድገት ዋናው ምክንያት መንግሥት የበጀት ጉድለት ለመሙላት የተከተለው መንገድ ነው።

“የሀገር ውስጥ ብድር ሪፖርቱ ላይ ለማየት ሞክረናል፤ ወደ 1.2 ትሪሊዮን ብር ነው እየደረሰ ያለው” ያሉት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አብርሃም ዓለማየሁ “ጫናው፣ ክምችቱ እየጨመረ፣ እየከፋ የሚሔድ ይመስለኛል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ
አቶ አሕመድ ሽዴ “አጠቃላይ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ብድር 65.7 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ጥምርታ 40.2 በመቶ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የኢትዮጵያ የውጭ ብድር 28.4 ቢሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 20 ቢሊዮን ዶላር የፌድራል መንግሥት ድርሻ ነው። የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በአንጻሩ 8.4 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ዕዳ አለባቸው። የመንግሥት የልማት ድርጅቶች “በመልሶ ማበደር” ከወሰዱት 41 በመቶ መልሰዋል። በትርፍ ክፍፍል መንግሥት ከልማት ድርጅቶቹ ያገኘው ከሚጠበቀው 27 በመቶ ብቻ ነው።

የትርፍ ክፍፍልን በተመለከተ “አንዳንድ ተቋማት” ዘንድ “ማመንታት” መኖሩን አቶ አሕመድ አምነዋል። በሚኒስትሩ ማብራሪያ መሠረት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ባለፉት አምስት ዓመታት “ምንም አይነት” የውጭ ብድር በተለይም፤ የንግድ ብድር እንዳይበደሩ ተከልክለዋል። ሥራቸውም “ነባር ፕሮጀክቶችን መጨረስ ብቻ” እንዲሆን ተደርጓል።

ከሦስት ዓመታት ገደማ በፊት የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ብድር ወደ የዕዳ እና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን በማዛወር መፍትሔ ለማበጀት የተደረገው ሙከራም እንዳልሰመረ አቶ አሕመድ ተናግረዋል።

“የመንግሥት ድርጅቶችን ወደ ግል በማዛወር ከሚገኝ ገቢ ነበር ብድሩን ለመክፈል ታስቦ የነበረው” ያሉት የገንዘብ ሚኒስትሩ “በተለያዩ ጫናዎች ምክንያት ፕራይቬታይዜሽን በተቀመጠው ዕቅድ ገቢው ባለመሳካቱ እና ሥራው ባለመሳለጡ ንግድ ባንክ ላይ ጫና አምጥቷል” ሲሉ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በዘጠኝ ወራት 111 ቢሊዮን ብር ብድር ለመክፈል ዕቅድ ነበረው። ይሁንና ኢትዮጵያ ቻይናን ጨምሮ ከአበዳሪዎቿ ባገኘችው እፎይታ ምክንያት ለብድር የተከፈለው 65 ቢሊዮን ብር ብቻ እንደሆነ የገንዘብ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። በሚኒስትሩ ሪፖርት መሠረት ለሁለት ዓመታት በሚዘልቀው እፎይታ እስካሁን 1.4 ቢሊዮን ዶላር የዕዳ ክፍያ የተራዘመ ሲሆን ተጨማሪ 49 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ላይ ድርድር እየተደረገ ነው።

ከስድስት ዓመታት ገደማ በፊት ከፍተኛ የዕዳ ጫና ሥጋት ካለባቸው ሀገራት ጎራ የተመደበችው ኢትዮጵያ በቡድን 20 ሀገራት የጋራ ማዕቀፍ በኩል የጀመረችው ድርድር ሲጠናቀቅ የዕዳ ጫናው ወደ ሞደሬት (moderate) ዝቅ ይላል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ አሕመድ ሽዴ ተናግረዋል። 

እሸቴ በቀለ