1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአጎዋ እግድ እንዲነሳ መጠየቁና የአሜሪካ ምላሽ

ሰኞ፣ መስከረም 6 2017

ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት የተመረጡ ምርቶችን ከቀረጥ እና ከኮታ ነፃ ለአሜሪካ ገበያ እንዲያቀርቡ ዕድል በሚሰጠው በዚህ የአጎዋ ማዕቀፍ የኢትዮጵያ መንግሥት በጦርነትና ግጭት ወቅት ፈጽሞታል በተባለው የመብት ጥሰት ምክንያት እንደ ግሪጎረሲያን ከጥር 2022 ጀምሮ ከዚህ ዕድል ውጪ ተደርጋለች።

https://p.dw.com/p/4kgSu
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምበሳደር ማይክ ሐመር
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምበሳደር ማይክ ሐመር ምስል Seyoum Getu/DW

የአጎዋ እግድ እንዲነሳ መጠየቁና የአሜሪካ ምላሽ

አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ የጣለችውን የአፍሪካ ዕድገት እና ዕድል የቀረጥ ነፃ ወይም የአጎዋ ተጠቃሚ እገዳ እንድታነሳላት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጠየቀ።

ሰሞኑን በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምበሳደር ማይክ ሐመር ይህንን በተመለከተ አዲስ አበባ ውስጥ በጋዜጠኞች ተጠይቀው "አሁንም በመንግሥት ኃይሎች ጥሰቶች እና በደሎች እየተፈጸሙ ነው። ስለዚህ ይህ እስከቀጠለ ድረስ ኢትዮጵያ እንደገና ወደ አጎዋ እንድትዋሃድ እና እንድትቀላቀል ማድረግ አይቻልም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

መንግሥት የአጎዋ ዕድል ከተቋረጠ በኋላ በተለይ በማምረቻው ዘርፍ ያሉ ሌሎች አማራጭ የገበያ ዕድሎችን ለማየት ጥረት ማድረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስቀድሞ አስታውቋል።

የአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ ይህንን አስመልክቶ የሰጡት መልስ

ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት የተመረጡ ምርቶችን ከቀረጥ እና ከኮታ ነፃ ለአሜሪካ ገበያ እንዲያቀርቡ ዕድል በሚሰጠው በዚህ የአጎዋ ማዕቀፍ የኢትዮጵያ መንግሥት በጦርነትና ግጭት ወቅት ፈጽሞታል በተባለው የመብት ጥሰት ምክንያት እንደ ግሪጎረሲያን ከጥር 2022 ጀምሮ ከዚህ ዕድል ውጪ ተደርጋለች።

የአሜሪካ መንግሥት ኢትዮጵያ ዳግም ወደዚህ ዕድል እንድትመለስ የዴሞክራሲን እና የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃን በተመለከተ እንዲሻሻል የሚፈልገው ለውጥ መኖሩን ይሻል።

ሰሞኑን በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት አድርገው ከተመለሱት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ጋር የተወያዩት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ከተወያዩባቸው ነጥቦች አንዱ ይሄው የአጎዋ ጉዳይ ሲሆን "አሜሪካ የኢትዮጵያን የአጎዋ ተጠቃሚነት እገዳ በማንሳት ወደ ቀድሞው ትግበራ እንድትመልስ" ጥሪ ማቅረባቸው ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ሰሞኑ ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት "አሜሪካ የኢትዮጵያን የአጎዋ ተጠቃሚነት እገዳ በማንሳት ወደ ቀድሞው ትግበራ እንድትመልስ" ጥሪ አቅርቧል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ሰሞኑ ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት "አሜሪካ የኢትዮጵያን የአጎዋ ተጠቃሚነት እገዳ በማንሳት ወደ ቀድሞው ትግበራ እንድትመልስ" ጥሪ አቅርቧል።ምስል Eshete Bekele Tekle/DW

የዚህ እርምጃ መነሻ ጦርነት እና ግጭት ያስከተላቸው የመብት ጥሰቶች እና በዚህ ውስጥ የመንግሥት ተሳትፎ መሆኑን ያስታወሱት ልዩ መልዕክተኛው ማይክ ሐመር በሀገሪቱ አሁን ድረስ የቀጠሉት "ግጭቶች ወታደራዊ መፍትሔዎች የላቸውም፣ እነዚህ አስቸጋሪ ታሪካዊ ጉዳዮች በውይይት ነው መፈታት ያለባቸው"፤ በማለት የመንግሥት ኃይሎች በመብት ጥሰት ላይ ያላቸው ተሳትፎ እስካልቆመ ድረስ ኢትዮጵያ ተመልሳ የአጎዋ ዕድል ተጠቃሚ መሆኗ የሚታሰብ አለመሆኑን አዱስ አበባ ውስጥ ባለው የአሜሪካ ኤምባሲ ውስጥ ተናግረዋል።

"ኢትዮጵያ ወደ አጎዋ እንድትመለስ ከማድረግ ሌላ ምንም የምንፈልገው ነገር የለም። ነገር ግን በሕጋችን መሠረት በመንግሥት ኃይሎች የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳይኖር የሚጠበቅ ነገር አለ። እና የሚያሳዝነው ብዙዎቻችሁ እንደዘገባችሁት አሁንም ጥሰቶች እና በደሎች እየተፈጸሙ ነው። ስለዚህም ይህ እስከቀጠለ ድረስ ኢትዮጵያ እንደገና ወደ አጎዋ ልትዋሃድ እና እንድትቀላቀል ማድረግ አይቻልም። ነገር ግን ከዚህ የተሻለ ምንም የምንፈልገው ነገር የለም"። 

ኢትዮጵያ እግዱን ለማስነሳት የምታደርገው ጥረት

ኢትዮጵያ ይህን እግድ ለማስነሳት የምታደርገውን ጥረት በተመለከተ ከሳምንታት በፊት የተጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢዩ ተድላ በወቅቱ ሲመልሱ "የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በዚህ ማዕቀፍ ላይ ብቻ ተመስርቶ የሚቀጥል ስላልሆነ፣ ኢትዮጵያም ሌሎች ዕድሎች ስላላት አማራጮችን እያሰፋች ትሄዳለች" ብለው ነበር።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ኢትዮጵያ ባለፈችበት ጦርነት ምክንያት ይህንን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን የሚያሳጣ፣ የባለሥልጣናትን ጉዞ የሚገድበውን በኢትዮጵያ ላይ ተጥሎ የቆየውን ማዕቀብ ለማስቀጠል ሰሞኑን መፈረማቸው መገለፁ ይታወቃል።

ኢትዮጵያ በአጎዋ በኩል ለአሜሪካ ገበያ ከምትልካቸው ምርቶች አብላጫው ጨርቃ ጨርቅ የነበረ ሲሆን የቆዳ ውጤቶች፣ ጥራጥሬና ቡናንም እየላከች በዓመት 260 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ታስገባ ነበር።

እግዱ መጣሉን ተከትሎ ግን በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያሉ በተለይ አንዳንድ አምራቾች ፋብሪካዎቻቸውን ዘግተው ወጥተዋል፣ በዚሁ ምክንያትም ሥራቸውን ያጡ ሠራተኞች ቁጥር ጥቂት የሚባል አለመሆኑን የሰራተኞች ማህበራት ገልፀዋል።
ሰሎሞን ሙጬ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ፀሐይ ጫኔ