1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዲሱ ዓመት የወጣቶች ዕቅድና ተስፋ 

ዓርብ፣ መስከረም 1 2013

አሮጌው 2012 ዓመት ተሸኝቶ አዲሱን አመት 2013ን አንድ ብለን ዛሬ ተቀብለነዋል። ዓመት አልፎ አመት ሲተካ ደግሞ አዳዲስ ዕቅዶችን መትለም እንዲሁም አዲስ ምኞትና ተስፋ መሰነቅም በአብዛኛው ሰው ዘንድ የተለመደ ነው። 

https://p.dw.com/p/3iLSH
Neujahrfest 2011 Äthiopien
ምስል Mekeit Teka

ወጣቶች፦ «የአዲስ ዓመት ተስፋና ዕቅድ»

አሮጌው 2012 ዓመት ተሸኝቶ አዲሱን አመት 2013ን አንድ ብለን ዛሬ ተቀብለነዋል። ዓመት አልፎ አመት ሲተካ ደግሞ አዳዲስ ዕቅዶችን መትለም እንዲሁም አዲስ ምኞትና ተስፋ መሰነቅም በአብዛኛው ሰው ዘንድ የተለመደ ነው። የዓዲስ ዓመት ዕቅድና ምኞታቸውን እንዲካፍሉን ካነጋገርናቸው ወጣቶች መካከል የሥነ-ህንፃና የምጣኔ ሀብት ባለሙያዋ ሳሮን ላቀው አንዷ ነች። ሳሮን በ20ዎቹ መጨረሻ የምትገኝ ወጣት ስትሆን በገንዘብና ኢኮኖሚ ሚንስቴር በውጭ ንግድ ዘርፍ የሚንስትር ድኤታ አማካሪ ሆና በመሥራት ላይ ትገኛለች። 
«ያለፈው ዓመት ዕቅዴ የነበረው ለትምህርት ከሀገር ወጥቼ ነበር ። ልክ ከትምህርት ቤት ስመለስ ነበር ይህንን ሥራ ያገኘሁት። እና ወደ ዚህ ስራ ስገባ በፊት የባለሙያ «ሮል»ነው የነበረኝ እና ከዚያ ሀላፊነትን ወደ መውሰድ መምራትን ወደ መለማመድ የሚያሻግረኝን ስራ ለመስራት የ«ፖሊሲ ዲዛይን» ላይ «ኢንቮልቭ»የሚያደርገኝን ስራ ለመስራት አቅጄ ነበር ዓመቱን የጀመርኩት። እሱን ነው ስሰራ የነበረው ።ጥሩ ዓመት ነው ያሳለፍኩት ራሴን ወደ «ሊደር ሽፕ»ማምጣት ሀላፊነት መውሰድ እነዚህን ነገሮች ነበር ስሰራ የቆየሁት።ከዓለም አቀፉ ሁኔታና ከሀገራዊ ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ ደስ የማያሰኙ ተግዳሮቶች ውጭ «ፕሮፌሽናሊ»ጥሩ ዓመት ነበር።» ብላለች። 
ወጣቷ በተሰማራችበት ሙያ ውጤታማ መሆንና ማኅበረሰቡን በታማኝነት ማገልገል ደግሞ የዚህ ዓመት ዕቅዷ ነው።« ይሄኛው ዓመት ላይ የ«ሊደርሽፕ ስኪሌ«ን ማዳበር እፈልጋለሁ።በምሰራበት ዘርፍ ደግሞ በደንብ ለውጥ የሚያመጡ ነገሮችን ለይቶ እነሱን አውጥቶ ጥሩ አቅጣጫ እንዲቀመጥባቸው አድርጎ ለ«ፕራቬት ሴክተሩም»ለማኅበረሰቡም ጥሩ ነገር ማበርከት።»የውጭ ንግድ ከውጭ ምንዛሬ ጋር ተያይዞ አንዱ የኢኮኖሚ ማነቆ ስለሆነ እሱ ላይ በደንብ የሚጨበጡ ለውጦች ማምጣት አንዱ አላማዬ ነው።እንደባለሙያ እዛ መኖሬ ልዩነት ማምጣት አለበት ብዬ አስባለሁ። እንዲያመጣም መስራት የምፈልገው።» ሀላፊነት መውሰድን፣ በታማኝነት ማገልገልን እነዚህን መለማመድ እፈልጋለሁ።»በማለት ነበር የገለፀችዉ። 
የተገባደደው 2012 ዓ/ም ለሳሮን በግሏ ወደ አመራር የመጣችበት ዓመት ቢሆንም በሀገር ደረጃ በርካታ ችግሮች የታዩበት ዓመትም ነበር።ሆኖም ግን ከችግሮቹ መሀል ተስፋ የሚሰጡና ወደ አዲሱ ዓመት ሊሻገሩ የሚገባቸው መልካም ነገሮች መመልከቷ አዲሱን ዓመት በተስፋ እንትቀበለው አድርጓታል። 
«ቀላል ጊዜ ይጠብቀናል ብዬ አላስብም። ከመንግስት በኩል እንደ መንግስት ሰራተኛ ሆኔ ሳየው የተለያዩ ነገሮች እየተሞከሩ ነው።ኢኮኖሚው ብዙ እንዳይጎዳ፣ማኃበረሰቡ በሚመጣው ነገር እንዳይጎዳ። አዲስ አበባ ውስጥ ደግሞ በየቦታው የምናያቸው የበጎ አድራጎት ነገሮች፤እኔ በተለይ ይሄ አመት ነክቶኝ ያለፈው እሱ ነው። በተለያዬ መንገድ ሰዎች ተደራጅተው እየተረዳዱ ያሉበት መንገድ ክፉ ቀንን ለካ እንዲህ መሻገር ይቻላል።ጥሩነት አሁንም መሃላችን አለ። የሚለው፤ እነዚህ ነገሮች ተስፋ ይሰጡኛል።» ስትል ገልጻለች። 
ሌላዋ ያነጋገርናት ወጣት ቤዛዊት ተስፋሁን ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ከአንድ ዓመት በፊት በሥነ-ተግባቦትና በጋዜጠኝነት ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪዋን አግኝታለች።ያም ሆኖ በተመረቀችበት ሙያ እስካሁን ስራ መያዝ አልቻለችም።ያለፈውን ዓንድ አመት ያለ ስራ የቆየችው ቤዛዊት ፤በአዲሱ ዓመት ግን የተሻለ ነገር ተስፋ ታደርጋለች። «የተሻለ ስራ አግኝቼ ራሴንና ቤተሰቤንና ሀገሬን ማገዝና ሀገራችን ሰላም እንድትሆን በተለያዬ ደረጃ ያው የሥነ-ተግባቦትና የጋዜጠኝነት ተመራቂ እንደመሆኔ መጠን በሚዲያው ዘርፍ ለሀገሬ የተሻለ ነገር ሰላምን በመፍጠር ፣ሰዎች እርስበርስ የማግባባትና የተለያዩ ስራዎችን ባራሴ ዘርፍ ለመስራት እያሰብኩ ነው።በአዲሱ ዓመት።» 
የሀገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፋንታ በወጣቶች እጅ መሆኑን የምትናገረው ቤዛዊት፤ የእሷና እሷን መሰል ወጣቶች ዕቅድና ተስፋ ዕውን እንዲሆን የኮሮና ወረርሽኝ እንዲሁም በሀገሪቱ የሚታየው የሰላም ዕጦት መፍትሄ ማግኘት አለበት።ከዚህ በተጨማሪ በመንግስት በኩል የስራ ፈጠራ ዕድልን ማመቻቸት በወጣቶች ዘንድ ደግሞ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄን በአግባቡ ማቅረብ ያስፈልጋል ባይ ነች።«መንግስት የተለያዩ የስራ ፈጠራዎችና ወጣቶችን የሚያበረታታ ነገር በመንግስት ደረጃ መፍጠር አለበት።።ታሰብ አለበት።ምክንያቱም የወደፊቱ የኢትዮጵያ እጣ ፋንታ በወጣቶች ዕጅ ያለ ስለሆነ።ወጣቶች ላይ ትልቅ ነገር መሰራት አለበት ብዬ አስባለሁ።ከዚያም በተጨማሪ የወጣቶችን ጥያቄ መንግስት ተቀብሎና አዳምጦ በሚፈልጉት መንገድ ምላሽ መስጠት አለበት።ወጣቱም በጣም ሰከን ብሎ ማሰብ ጥያቄ እንኳን ቢኖር በተረጋጋ ሁኔታ መጠየቅና መልስ ማግኜት ይቻላል። ነገር ግን ጥያቄአችን የምናቀርብበት መንገድ ሰላማዊና አግባብ ያለው መሆን አለበት።ምክንያቱም ስንጠይቅ ሰላማችንን የሚያሳጣ ከሆነ ለኛም ለሀገራችንም መልካም ያልሆነ ነገር ነው የሚፈጠረው ማለት ነው።» በማለት አብራርታለች። 
በወሎ ዩንቨርሲቲ የሶስተኛ አመት ተማሪ የሆነው ወጣት ኤርሚያስ ተገኝ በበኩሉ በአዲሱ ዓመት የመጀመሪያ ዲግሪውን ለመያዝ ምረቃውን በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።ኤርሚያስ ያለፈውን የትምህርት አመት መለስ ብሎ ሲያስታውሰው በተማሪዎች ግጭት እንዲሁም በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ የዩንቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሂደት እክል ገጥሞት ነበር።በአዲሱ ዓመት ግን ወጣቶች በተለይም የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች ከስሜት ይልቅ በማስተዋል እንዲጓዙ ይመኛል።«እኔ ለወጣቶች ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት ቢኖረኝ አስተዋይ እንሁን በተለይ ባልተረጋገጡ በፈጠራ ወሬዎች በስሜት ተነሳስተን ይችን ትልቅ ሀገር ወደኃላ አንጎትታት። እና እናስተውል ያስተዋለ ሰው ነው ነገን ማየት የሚችለው። »ብሏል። 
ከግማሽ በላይ ህዝቧ ወጣት መሆኑ የሚነገርላት ኢትዮጵያ የሀገሪቱ ጥፋትም ይሁን ልማት በዚህ ሀይል የሚወሰን ነው።ዘመን ሰውን ይመስላል እንዲሉ፤አዲሱ ዓመት የተሳካ እንዲሆንም በእነዚህ ወጣቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል። ዛሬ አንድ ብለን የጀመርነው 2013 ዓ/ም የሰላምና የስኬት ዓመት እንዲሆን ከመመኜት ባለፈ መሥራትን ይጠይቃልና አዲሱ ዓመት የሰላም የጥረትና የስኬት እንዲሆን እንመኛለን። መልካም አዲስ ዓመት። 

Young Flower Adey Abeba Blumen Äthiopien
ምስል Yohannes Geberegziabeher

ፀሐይ ጫኔ 
ሽዋዬ ለገሠ