1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮጳ ኅብረትን ያሰጋው የስደተኞች ቀውስ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 25 2015

የኅብረቱ አባል ሀገራት በተለያየ መንገድ አውሮጳ የሚደርሱትን ስደተኞች ለማስተናገድ ከዚህ ቀደም የተስማሙባቸው አወዛጋቢ ደንቦች የኅብረቱ ድንበር በሚባሉ ሀገራት ላይ ባስከተሉት ጫና ተግባራዊ ሊሆኑ አልቻሉም። መጀመሪያ በረገጡዋቸው የአውሮጳ ሀገራት የሚገኙ ስደተኞችን በቃደኝነት እንዲከፋፈሉ የተዘረጋው ስርዓትም ሙሉ በሙሉ ገቢራዊ አልሆነም።

https://p.dw.com/p/4LhaL
Treffen der EU-Innenminister
ምስል Thierry Monasse/AP/picture alliance

የአውሮጳ ኅብረትን ያሰጋው የስደተኞች ቀውስ

የአውሮጳ ህብረት በጎርጎሮሳዊው 2023 ዓ.ም. የፖለቲካ መርህ ለውጥ ካላደረገ በአባል ሀገራት ውስጥ የስደተኞች ቀውስ ተባብሶ ይቀጥላል የሚል ስጋት አለ። የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት በተሰናበትነው በጎርጎሮሳዊው በ2022 ዓም ትኩረት ሰጥተው ሲነጋገሩባቸው ከቆዩት ጉዳዮች ውስጥ የተገን አሰጣጥና የስደተኞች አቀባበል ይገኝበታል። አባል ሀገራት አዲሱን 2023 ዓ.ም. የተቀበሉት ግን በስደተኞች ጉዳይ የሚታረቁ በማይመስሉ ሁለት ቡድኖች ተከፍለው ቢሆንም በአዲሱ ዓመት ትብብርን መሠረት ያደረገ የተገን አሰጣጥ መርህ ፍለጋ ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል ። የኅብረቱ ሀገር ውስጥ ጉዳዮች ኮሚሽነር ይልቫ ጆሀንሰን በጎርጎሮሳዊው 2022 መገባደጃ ላይ «አውሮጳ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ አይቶ የማያውቀው የስደተኞች ቀውስ ተጋርጦባታል» ሲሉ አስጠንቅቀው ነበር። ከማስጠንቀቂያው ጋር አውሮጳ በአንድነት ሰዎችን መደገፉን ይቀጥላል ሲሉም ተስፋቸውንም ገልጸዋል። ይሁንና አንዳንድ አባል ሀገራት በስደተኞች ተጨናንቀናል በማለት አቤቱታቸውን ሲያቀርቡ ቆይተዋል። ከአንድ ሚሊዮን ይበልጣሉ የሚባሉ የዩክሬን ስደተኞችን የተቀበለችው ጀርመንም ይህን ከሚሉት አንዷ ናት። የጀርመን የፌደራልና የየግዛቶች መንግሥታት በተለይ የስደተኞች ማቆያዎች  እጥረት እንደገጠማቸው ይናገራሉ። የዩክሬን ጦርነት በአውሮጳ ያስከተለው የስደተኞች ቀውስ
የተመ የስደተኞች ጉዳይ መስሪያ ቤት  እንደሚለው እስካለፈው ህዳር መጨረሻ ቁጥራቸው 4.8 ሚሊዮን የሚደርስ ሰዎች በፖላንድ ፣በጀርመን ፣በባልቲክ ሀገራት በሮማንያ እና ስሎቫክያ በጊዜያዊ ተገን ጠያቂነት ተመዝግበዋል። የዩክርኑ ጦርነት ከቀጠለ ደግሞ በ2023 የስደተኛው ቁጥሩ እጅግ ይጨምራል ተብሎ ነው የተፈራው። ይህም ለአውሮጳ ከባድ ፈተና ሆኖ መቀጠሉ እንደማይቀር ከወዲሁ እየተነገረ ነው። የዶቼቬለ የብራሰልስ ዘጋቢ ገበያው ንጉሴ  በአውሮጳ ከሰባት ዓመት በፊትም የስደተኞች ቀውስ ተከስቶ እንደነበር አስታውሶ የአሁኑ ቀውስ ግን ከበፊቱ በዓይነቱ የተለየና የባሰም ነው ይላል። ለዚህም ሶስት ጉዳዮችን በምክንያትነት ያነሳል። ኅብረቱ በ2022 ለዩክሬን ስደተኞች ልዩ ትኩረት መስጠቱ በደቡብ ምሥራቅ አውሮጳ በኩል የሚገቡ ስደተኞች ጉዳይ እንዲሸፈን አድርጓል እየተባለ ነው። ሕገ ወጥ በሚባል መንገድ የኅብረቱን አባል ሀገራት ድንበር አቋርጠው ከሶሪያ ከአፍጋኒስታን ከፓኪስታን እና ከግብጽ የገቡት ስደተኞች ቁጥር ከቀደሙት ዓመታት በጣም ከፍ ያለ መሆኑ ነው የተገለጸው።የኅብረቱ ድንበር ተቆጣጣሪ ድርጅት ፍሮንቴክስ እስካለፈው ጥቅምት ድረስ ሕገ ወጥ በሚባል ስደት የገቡ 280 ሺህ ስደተኞችን መዝግቧል። ይህም በ2021 ከገባው ስደተኛ በ77 በመቶ ይበልጣል  ተብሏል።

Deutsches Boot rettet weitere 135 Migranten im Mittelmeer
የጀርመን መርከብ ከሜዴትራንያን ባህር ያተረፋቸው የጀልባ ስደተኞችምስል Max Cavallari/dpa/SOS Humanity/picture alliance
Flüchtlinge Griechenland Grenze zu Nordmazedonien
ተገን ጠያቂዎች ግሪክ ድንበር አቅራቢያ በሚገኝ ባቡር ጣቢያ ምስል Nicolas Economou/NurPhoto/picture alliance

የኅብረቱ አባል ሀገራት በተለያየ መንገድ አውሮጳ የሚደርሱትን ስደተኞች ለማስተናገድ ከዚህ ቀደም የተስማሙባቸው አወዛጋቢ ደንቦች የኅብረቱ ድንበር በሚባሉ ሀገራት ላይ ባስከተሉት ጫና መንስኤ ተግባራዊ እየሆኑ አይደለም። ከመካከላቸው አንዱ የደብሊኑ ስምምነት ነው ።ከዚህ ሌላ መጀመሪያ በረገጡዋቸው የአውሮጳ ሀገራት የሚገኙ ስደተኞችን፣አባል ሀገራት  በፈቃደኝነት እንዲከፋፈሉ የተዘረጋው ስርዓትም እንዲሁ ሙሉ በሙሉ እየተተገበረ አይደለም ። የስደተኞችን ጉዳይ «የአውሮጳ ኅብረት ያልተስማማበት ቋሚ ችግር ሲል የሚጠራው ገበያው  አባል ሀገራትን ከሚያወዛግቡት ጉዳዮች አንዱ የደብሊኑ ስምምነት ተግባራዊ አለመሆን ነው ይላል።ስደተኞችን በፈቃደኝነት አለመከፋፈልም ሌላ አሁንም መላ ሳይገኝለት የዘለቀ የኅብረቱ ችግር ነው።በዚህ መካከል ስደተኞች ለእንግልት መዳረጋቸው ከኅብረቱ መርሆዎች አንዱ የሆነውን የሰብዓዊ መብት ጥበቃ የሚጻረር ሆኗል።
በጉዳዩ ላይ ባለፈው ወር  የመከሩት የኅብረቱ አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በ2023 ዓም ችግሩን ለማቃለል ጥረታቸውን አጠናክረው ለመቀጠል ቃል ገብተዋል። ኅብረቱ በአባል ሀገራት መካከል የአንድነት መንፈስን ማስረጽ የአዲሱ የ2023 ፈተና እንደሚሆንም ይጠበቃል። ገበያው እንደሚለው በዙር የሚደርሰውን የኅብረቱን ፕሬዝዳንት ከ 3 ቀናት በፊት የተቀበለችው ስዊድን ለዓመታት የአባል ሀገራት የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ሳያስማማ የቆየው የተገን አሰጣጥ ደንብ እንዲሻሻል የድንበር አስተዳደርም እንዲስተካከል ግፊት ታደርጋለች ተብሎ ይጠበቃል። በባልካን የስደት መስመር ወደምዕራብ አውሮጳ የሚጎርፉትን ስደተኞችን ማስቆምም ሌላው ኅብረቱ ትኩረት ሰጥቶ የሚንቀሳቀስበት ጉዳይ ይሆናል ።ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ ተንታኞች ፣ ኅብረቱ የስደት መነሻ ከሆኑት ሀገራት ጋር ሰዉ ሕገ ወጥና ተስፋ የሌለው ስደትን እንዳይጀምር የሚያደርጉ ተጨማሪ ስምምነቶች ላይ እንዲያተኩርም ይመክራሉም።

Infografik Flüchtlingsrouten über den Balkan EN
የባልካን የስደት መስመር

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ