1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮጳ ኅብረት የድንበር ቁጥጥርን ለማጠናከር መስማማቱ

ማክሰኞ፣ የካቲት 7 2015

የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት መሪዎች ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ብራሰል ቤልጅየም ውስጥ ባካሄዱት ልዩ ጉባኤ ሕገ ወጥ ያሉትን ስደት መከላከል ያስችላሉ ያሏቸውን ጠንከር ያሉ እርምጃዎች ተግባራዊ ለማድረግ ተስማምተዋል። የመሪዎቹ ውሳኔ ስደተኞችን በሚረዱ ድርጅቶች ተተችቷል።

https://p.dw.com/p/4NU0o
Belgien Brüssel | EU-Gipfel
ምስል John Thys/AFP/Getty Images

የአውሮጳ ኅብረት የድንበር ቁጥጥርን ለማጠናከር መስማማቱ

የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት መሪዎች ባለፈው ሐሙስና አርብ ብራሰልስ ቤልጅየም ባካሄዱት ጉባኤ፣ ሕገ ወጥ የሚሏቸውን ስደተኞች ለመከላከል የየሀገሮቻቸውን የድንበር ጥበቃ ከማጠናከር አንስቶ ችግሩን ለማቃለል ይረዳሉ ባሏቸው ሌሎች እርምጃዎች ላይ ተስማምተዋል። ጉዳዩ የመነጋገሪያ አጀንዳ ለመሆን የበቃው ወደ ኅብረቱ አባል ሀገራት የገቡ ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ መሄዱን መነሻ በማድረግ ነበር። በጎርጎሮሳዊው 2022 ድንበር አቋርጠው የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት የደረሱ ስደተኞች ቁጥር ወደ 330 ሺህ አሻቅቧል። 
የአውሮጳ ኅብረት ወደ አባል ሀገራት የሚገቡ ስደተኞችን ቁጥር መቀነስ የሚያስችሉ የተባሉ ሕጎችን ተግባራዊ ለማድረግ ሲሞክር ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል። የኅብረቱ ኮሚሽን ስደተኞችን በሚመለከት ብዙ ደንቦችንና ውሎችን ቢያወጣም  አባል ሀገራት እስካሁን መስማማት አልቻሉም።የኅብረቱ ድንበር የሆኑት ግሪክ ጣልያን ክሮኤሽያ ቡልጋሪያ ማልታና ቆጵሮስ የስደተኞችን ጫናን መቋቋም አቅቶናል ሲሉ በተደጋጋሚ ስሞታቸው ያቀርባሉ።በአንጻሩ የስደተኞች ምርጫ የሆኑት ጀርመን ኦስትሪያና ፈረንሳይ ደግሞ የስደተኞች የተገን ጥያቄ መጀመሪያ በገቡበት አገር ፍፃሜ ያገኝ በሚለው አቋማቸው ለዓመታት ጸንተው ቆይተዋል። ከዚህ ሌላ ስደተኞችን ማስተናገድ ከአቅማችን በላይ ሆኗል የሚሉትን የኅብረቱን አባል ሀገራት ጫና ለማቃለል አባል ሀገራት በኮታም ይሁን በቀፈቃደኝነት ስደተኞችን እንዲከፋፈሉ የደረሱበት ስምምነትም በተደጋጋሚ ሳይሳካ ቀርቷል። የስደተኞችን ሲያደርግ የቆየው የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ባለፈው ሳምንቱ ጉባኤው ችግሩን ለመፍታት የአውሮጳ ኅብረት የውጭ ድንበር ጥበቃን ለማጠናከር ይረዳል ያለውን አዲስ አሰራር አቅርቧል። የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርዙላ ፎን ዴር ላየን በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ እንደተናሩት ኮሚሽናቸው የኅብረቱን አባል ሀገራት ድንበሮች ጥበቃ ለማጠናከር የተለያዩ ድጋፎችን ያቀርባል። 
«ድንበሮች በአግባቡ መያዝ አለባቸው። የኅብረቱን የውጭ ድንበሮች በማጠናከር ሕገ ወጥ ፍልሰትን ለመከላከል እንሰራለን። ይህን ተግባራዊ ለማድረግም ሁለት ዋና ዋና ፕሮጀክቶች ላይ እናተኩራለን። በሌላ አባባል ከመኪና አንስቶ እስከ ካሜራዎችና መቆጣጠሪያ ማማዎች እንዲሁም የኤሌክትሮኒክስ የቅኝት መሣሪያዎች ድረስ የተቀናጀ ተንቀሳቃሽና ቋሚ መሰረተ ልማቶችን እናቀርባለን።»
ኅብረቱ የድንበር ጥበቃን ከማጠናከር በተጨማሪ ችግሩን ሊከላከሉ ይችላሉ ያላቸውን ሌሎች ውሳኔዎችም አሳልፏል። የጉባኤውን ሂደት የተከታተለው የብራሰልሱ ዘጋቢያችን ገበያው ንጉሴ እንዳለው ከመካከላቸው የተገን ጥያቄአቸው ተቀባይነት ያላገኘ ስደተኞችን ወደ መጡበት መጠረዝ እና የስደተኞች መነሻ ለሆኑ ሀገራትም ድጋፍ መስጠት የሚሉት ውሳኔዎችም ይገኙበታል።
የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት መሪዎች ያስተላለፏቸው እነዚህ ውሳኔዎች ከሰደተኞች መብት ተሟጋቾችና ከረድኤት ድርጅቶች በኩል ትችቶች ቀርበውባቸዋል። እነዚህ ወገኖች የመሪዎቹን ውሳኔ የኅብረቱን መርሆዎችን የሚጻረሩና የስደተኞችን ሰብዓዊ መብቶች የሚጋፉ  ክብራቸውንም ዝቅ የሚያደርጉ ናቸው ሲሉ ይሞግታሉ። እንደገና ገበያው 
ከኅብረቱ ውሳኔዎች አስቀድሞ በተለይ የኅብረቱ ድንበር ከሆኑ ሀገራት አንዳንዶቹ ደጋግመው ያነሱት የነበረው ጥያቄ ድንበራችን ላይ አጥር እንሰራ የሚል ነበር።ይህን ካሉት ውስጥ በስደተኞች የተጨናነቀችው ግሪክ ትገኝበታለች።የግሪክ ጠቅላይ ሚኒስትር ክርያኮስ ሚትሶታኪስ ኅብረቱ ለድንበር አጥር ግንባታ የሚውል ገንዘብ እንዲሰጥ ነበር ፍላጎታቸው። ይህ ሆነም አልሆነ ሀገራቸው ድንበርዋን ማጠሯ አይቀርም ብለዋል።

Afrikanische Migranten Immigranten illegale Einwanderer Italien Flash-Galerie
ምስል AP
Illegale Immigranten provisorische Unterkunft Italien Flash-Galerie
ምስል picture-alliance/dpa

«የአውሮጳ ኅብረት የድንበር አጥር ግንባታን በገንዘብ መደገፍን ተቃውሞ ሕገ ወጥ ፍልሰትን ለመከላከል የሚረዱ ድሮኖችን ወይም መቆጣጠሪያ መሣሪያዎችን ግዥን በገንዘብ እደግፋለሁ ማለቱ በበኩሌ ትርጉም ያለው አይመስልም ። የምንነጋገረው የውጭ ድንበርን ለመጠበቅ መወሰድ ስላለበት የተቀናጀ እርምጃ ነው። እናም የገንዘብ እርዳታው አጥር መገንባትን ማካተት ይኖርበታል።ያም ሆነ ይህ የአውሮጳ ገንዘብም ይኑር አይኑር ግሪክ የራስዋን አጥር መገንባትዋ አይቀርም ።»
በሌላ በኩል ድንበር እንጠር የሚለው ጥያቄ አጥብቀው የተቃወሙም አሉ። የሉክስምበርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዜቭያ ቤትል ከሀሳቡ ተቃዋሚዎች አንዱ ናቸው ። 

«ወርቃማ ኮከቦች ላሉት ሰማያዊ ባንዲራችን ዋጋ እንደመክፈላችን አጥርና ግምብ ለመገንባት ገንዘብ ማፍሰስ ስህተት ነው ብዬ አምናለሁ። በተለይ አንድ ቦታ ላይ ከጀመርነው ማቆሚያ አይኖረውም ምክንያቱም በአንድ ድንበር ይጀመራል ሌላው ይቀጥላል። ለጀርመናውያን ወዳጆቻችንም ነግሪያቸዋለሁ። አውሮጳ ሁለቱን ጀርመኖች የከፈለውን ግምብ ማንሳት ችሏል። ይህ ደግሞ የክፍለ ዓለማችን ታሪክ አካል ነው። »
ሌላው ኅብረቱ እንዲያተኩርበት  
በአውሮፓ ኅብረት መሪዎች ደረጃ የተካሄደው የአሁኑ ጉባኤ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች ባሻገር በአባል ሀገራት የተለያየ አቋም ምክንያት እስካሁን እልባት ያላገኘውን የስደተኞች ጉዳይ በጋራ የስደተኞች ፖሊሲ መፍትሄ ሊያገኝ ይችላል የሚል እምነት አለ።ይህም ቀጣዩ የኅብረቱ ትኩረት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ