1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ድልና የፖለቲከኛዋ ዘረኛ አስተያየት

ሐሙስ፣ ሰኔ 13 2016

የጎርጎሪዮሳዊው 2024 ዓ,ም የአውሮጳ እግር ኳስ ሻምፕዮን አስተናጋጅ ጀርመን እስካሁን ባካሄደችው ሁለት ግጥሚያ ተሳክቶላታል። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ሃንጋሪን ሁለት ለባዶ ማሸነፉን ተከትሎ አንድ የታኅታይ ምክር ቤት አባል የሰጡት ዘረኛ አስተያየት ጠንካራ ትችት አስከትሏል።

https://p.dw.com/p/4hJrO
የእግር ኳስ አፍሪቃሪዎች
የጀርመን እግር ኳስ አፍቃሪዎች ደስታምስል Dennis Duddek/Eibner Pressefoto/picture alliance

የአውሮጳ ሻምፒዮና

የጎርጎሪዮሳዊው 2024 ዓ,ም የአውሮጳ እግር ኳስ ሻምፕዮን አስተናጋጅ ጀርመን እስካሁን ባካሄደችው ሁለት ግጥሚያ ተሳክቶላታል። ትናንት ከሃንጋሪ ጋር በነበረው ጨዋታ የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ሁለት ለባዶ ማሸነፉ ተቀዛቅዞ የከረመውን የእግር ኳስ አፍቃሪ ስሜት አነቃቅቷል። ከሁለት ሳምንታት በፊት ከዩክሬን ቡድን ጋር እኩል ለእኩል ከዚያም ከግሪክ ብሔራዊ ቡድን ጋር ሁለት ለአንድ መውጣቱ ግብ ጠባቂው ማኑዌል ኖየር እና ኢልካይ ጉንዱኻን በዘንድሮው የአውሮጳ ሻምፒዮን መሰለፍ አለባቸው ወይ የሚል ጥያቄ እንዲነሳባቸው አድርጎ ነበር። ሆኖም ጨዋታዊ ከተጀመረ አንስቶ እስከ ትናንት ያሳዩት ንቃትና የነበራቸው አስተዋጽኦ የእግር ኳስ ተንታኝና ተቺዎችን ውርጅብኝ ወደ አድናቆት ለውጦላቸው ታይቷል። በትናንቱ የጀርመን ሃንጋሪ የእግር ኳስ ጨዋታ የ33 ዓመቱ ኢልካይ ጉንዱኻን አንዷን ጎል እራሱ ሲያስቆጥር ሌላኛዋን ጎል ለ22 ዓመቱ ጀማል ሙሲያላ አመቻችቶ በማቀበል የኳስ አፍቃሪዎችን አስፈንድቋል። የትናንቱን ውጤት ተከትሎም ከወዲሁ ጀርመናውያን ለፍጻሜው ጨዋታ ቡድናቸው ደርሶ የማየት ተስፋ መሰነቃቸው ነው የተገለጸው። የቡድኑ አሰልጣኝ ጁሊያን ናግልስማንም የብዙዎችን አድናቆት አትርፏል።

የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች
የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በከፊል ምስል Angelika Warmuth/REUTERS

የፖለቲከኛዋ ዘረኛ አስተያየት እና የጀርመን ድል

የጀርመን የታችኛው ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት የአገራቸውን የትናንት ድል ተከትሎ በኤክስ (የቀድሞው ቲውተር) ገጻቸው ላይ በለጠፉት ዘረኛ አስተያየት ውግዘት ደረሰባቸው። የአውሮጳ ዋንጫ አዘጋጇ ጀርመን ትናንት ምሽት ሃንጋሪን 2 ለ 1 ማሸነፏን ተከትሎ የግሪን ፓርቲ አባሏ እና የጀርመን የታችኛው ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ካትሪን ጉሪግ-ኤካርድት በኤክስ ገጻቸው ላይ «ይህ ቡድን በእውነቱ የተለየ ነው። አስቡት እስኪ ሁሉም ተጫዋቾች ነጮች ቢሆኑ ደግሞ» የሚል አስተያየት ነበር የለጠፉት።

ፖለቲከኛዋ ከቆይታ በኋላ ልጥፋቸውን አጥፍተው ለድርጊታቸው ይቅርታ ጠይቀዋል። ይሁን እንጂ የነጻ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኤፍ. ዲ. ፒ.) ሁለተኛ ሰው ዎልፍጋንግ ኩቢኪን ጨምሮ ከተለያዩ ወገኖች ውግዘት እየደረሰባቸው ነው።

ኩቢኪ በሰጡት አስተያየት፣ «በጀርመን የሰዎች የቆዳ ቀለም አሁንም ጉዳይ መሆኑ ያስፈራኛል።» ነው ያሉት።

መቀመጫውን ኮሎኝ፣ ጀርመን ያደረገው ደብሊው. ዲ. አር. (WDR) የተባለ የመገናኛ ብዙሃን ተቋም የአውሮጳ ዋንጫ ከመጀመሩ በፊት አካሄድኩ ባለው ጥናት፣ 21 በመቶ የሚሆኑ ጀርመናዊያን በብሔራዊ ቡድናቸው ውስጥ የበዙ ነጭ ተጫዋቾችን ማየት እንደሚፈለጉ አረጋግጫለሁ ብሎ ነበር። ፖለቲከኛዋም በዚህ የጥናት ውጤት ቅር መሰኘታቸውን ለመግለጽ ያንን አስተያየት መጻፋቸውን ገልጸው፣ በብሔራዊ ቡድናችንም እኮራለሁ ብለዋል።

ትናንት ምሽት በሽቱትጋርት ሜርሴዲስ ቤንዝ አሬና በተደረገው ጨዋታ ጀርመን ሀንጋሪን 2 ለ 0 ስታሸንፍ፣ ሁለቱንም ጎሎች ጀማል ሙሲያላ በ22ኛው ደቂቃ እና ኤልካይ ጉንዶጋን በ67ኛው ደቂቃ ከመረብ አሳርፈዋል። እነዚሁ ተጫዋቾች የናይጄሪያ እና የቱርክ ዝርያ ያላቸው መሆናቸው ይታወቃል። የመሐል ተከላካዮቹ አንቶኒዮ ሩድሪገር እና ጆናታን ታህ፣ እንዲሁም የመስመር ተጫዋቹ ሊሮይ ሳኔን ጨምሮ የሌላ አገር የዘር ሐረግ ያላቸው ተጫዋቾች በዘንድሮው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ይገኛሉ።

በጥናቱ ተገኘ ከተባለው እና ከፖለቲከኛዋ አስተያየት በተለየ፣ ይህንኑ ጨዋታ በትልልቅ ስክሪኖች ለመከታተል በፍራንክፈርት ማይን ወንዝ ዳርቻ ወደተዘጋጁት የደጋፊዎች የመዝናኛ ቦታዎች በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ የጀርመን ደጋፊዎች በመትመም ቡድናቸው ባስመዘገበው ድል ደስታቸውን በጋራ ሲገልጹ የዶቸ ቬለ ዘጋቢ ተመልክቷል።

ከጎርጎሪዮሳዊው 2006ቱ የዓለም ዋንጫ ወዲህ ውጤት ለራቀው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን የአውሮጳዋንጫው ጅማሮ ሰምሮለታል። ጀርመን በሁለት ጨዋታዎች በማሸነፍ ምድቧን በ6 ነጥብ እየመራች ወደ ጥሎ ማለፉ ስትሻገር፣ በመጀመሪያ ጨዋታዋ ሃንጋሪን ያሸነፈችው እና ትናንት ደግሞ ከስኮትላንድ ጋር አቻ የወጣችው ስዊዘርላንድ በ4 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተገኛለች። ስኮትላንድ በአንድ ነጥብ፣ ሃንጋሪ ደግሞ ካለምንም ነጥብ ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል።

ጀርመን የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዋን በሳምንቱ ማብቂያ እሑድ፣ በፍራንክፈርት ዶቼ ባንክ ፓርክ ከስዊዘርላንድ ጋር ታደርጋለች፤ ሃንጋሪ ደግሞ ስኮትላንድን ተገጥማለች።

የእግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎች
የጀርመን እና የሀንጋሪ የእግር ኳስ ቡድኖች ደጋፊዎች በሽቱትጋር ምስል Axel Schmidt/REUTERS

የአየር ሁኔታ ትንበያ ያስከተለው ችግር

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በጀርመን የአውሮጳ ዋንጫ ጨዋታዎችን ከሚያስተናግዱ 10 ከተሞች መካከል በአምስቱ የሚገኙ የደጋፊዎች የመዝናኛ ስፍራዎች (ፋን ዞን) በከባድ የአየር ጠባይ ሰበብ ከማክሰኞ ጀምሮ ተዘግተዋል። በዶርትመንድ፣ በበርሊን፣ በኮሎኝ፣ በዱሱልዶፍ እና በጌልሰንኪርቸን ከተሞች የሚገኙት የደጋፊዎች የመዝናኛ ስፍራዎች ናቸው የተዘጉት።  

የጀርመን የሜትሪዮሎጂ አገልግሎት ባወጣው ትንበያ ሳምንቱ በተለይ በምዕራብ እና ማዕከላዊ ጀርመን ነጎድጓድ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ እና አውሎ ንፋስ ይኖረዋል ማለቱን ተከትሎ ነው የውድድሩ አዘጋጆች እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት።

በተለይ ማክሰኞ በነበረው የቱርክዬ እና ጆርጂያ ጨዋታ በዶርትሙንድ የሚገኙ ከ80,000 በላይ የቱርክዬ ደጋፊዎች ጨዋታውን በከተማዋ ባሉ ሁለት የደጋፊዎች የመዝናኛ ቦታዎች ለመመልከት ቢያቅዱም በዚሁ ውሳኔ ሰበብ አልተሳካም። የጀርመን የሜትሪዮሎጂ አገልግሎት የአየር ሁኔታው እየታየ የመዝናኛ ቦታዎቹ ክፍት ሊሆኑ እንደሚችሉ አስታውቋል።

ከስታዲየሞች ውጪ የሚታየው የደጋፊዎች እንቅስቃሴ የአውሮጳ ዋንጫው ሌላው ድምቀት ሲሆን፣ በአየር ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ ግን ያንን እንዳያደበዝዘው ተሰግቷል።

መሳይ ወንድሜነህ

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ