1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስዊዘርላንድ:- የአዉሮጳ የሙዚቃ ዉድድር 2024 አሸናፊ

ዓርብ፣ ግንቦት 9 2016

ስዊዘርላንድ የዘንድሮዉን የአዉሮጳ ሃገራት የሙዚቃ ዉድድር «ይሮቪዥን - 2024» አሸናፊ ሆናለች። በስዊድንዋ ከተማ ማሌሞ ዘንድሮ በተካሄደዉ 68ኛዉ የአዉሮጳዉ ሃገራት ግዙፍ የሙዚቃ ዉድድር ላይ በገዛ ፈቃድ ለቆ መዉጣት፤ በስርዓት ጉድለት ከዉድድሩ በባረር ብሎም የዓለም የፖለቲካ ዉጥረት ወላፈን ያጠላበት ነበር።

https://p.dw.com/p/4fxHd
የ24 ዓመቱ ስዊዘርላንዳዊ የይሮቪዥን 2024 አሸናፊ
የ24 ዓመቱ ስዊዘርላንዳዊ የይሮቪዥን 2024 አሸናፊ ምስል Jessica Gow/TT News Agency via AP/picture alliance

ስዊዘርላንድ:- የአዉሮጳ የሙዚቃ ዉድድር 2024 አሸናፊ

የአዉሮጳ የሙዚቃ ዉድድር 2024 አሸናፊ ስዊዘርላንድ

ስዊዘርላንድ የዘንድሮዉን የአዉሮጳ ሃገራት የሙዚቃ ዉድድር «ይሮቪዥን - 2024» አሸናፊ ሆናለች። ባለፈዉ ቅዳሜ ግንቦት ሦስት በስዊድንዋ ከተማ ማሌሞ ላይ በተካሄደዉ 68ኛዉ የአዉሮጳዉ ሃገራት ግዙፍ የሙዚቃ ዉድድርላይ በገዛ ፈቃድ ለቆ መዉጣት፤ በስርዓት ጉድለት ከዉድድሩ በባረር ብሎም የዓለም የፖለቲካ ዉጥረት ወላፈን ያጠላበት ነበር።  በሙዚቃ አንድነት አልያም በሙዚቃ ትስስር የሚል መርህን በያዘዉ በዚህ ውድድር ላይ በድምሩ ከ 37 አገሮች የመጡ ከያንያን እና ሙዚቀኞች ተሳትፈዋል ። ኔሞ የሚል የከያኒ መጠርያን የያዘዉ የስዊዘርላንዱ  ሙዚቀኛ “The code“ "ዘ ኮድ" በሚለዉ ዘፈኑ ማሸነፉ ቤተሰቦቻቸዉን ሳያስከትሉ ብቻቸዉን በሙዚቃዉ ዉድድር ላይ የተገኙትን የስዊድንዋን ልዕልት ቪክቶርያን  ጨምሮ በርካታ አዉሮጳዉያን ደጋፊዎቹን አስደስቷል። ሮዛ ቀለም ያለዉ ቀሚስ ብሎም ስቶኪንግ ማለት ረዘም ያለ ስስ ካልሲ ያጠለቀዉ እና ሮዛ ቀለም ብጤ የላባ መሰል ጃኬት መሳይ ያጠለቀዉ የስዊዘርላንዱ  የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ እንደተወዳደረበት ሙዚቃ መልክት ሁሉ አለባበሱ ወንድም ሴትም ያልሆንኩ ራስን የመቻል የንዑስ ሰው ጉዞ አይነት መልክት ያስተላፈበት ነበር። ከያኒዉ በመድረኩ ላይ ሙዚቃዉን ሲያቀርብ ያሳየዉ የእንቅስቃሴ ብቃት ከሙዚቃዉ ጋር ደጋፊዎቹ እንዲማረኩበት እና  እንዲመርጡት ብዙ አስተዋጽኦ እንዳደረገም ተነግሮለታል። 

በሙዚቃ ዉድድሩ ሁለተኛ የሆኑት የክሮየሽያ ዘፋኞች
በሙዚቃ ዉድድሩ ሁለተኛ የሆኑት የክሮየሽያ ዘፋኞችምስል Jens Büttner/dpa/picture alliance

የ24 ዓመቱ ስዊዘርላንዳዊ የዉድድሩ አሸናፊ ኔሞ፤ የአውሮጳ ብሮድካስቲንግ ህብረት የሚያዘጋጀዉን ዉድድር ሽልማት በክብር ከፍ ስያደርግ ወጣቱ ከያኒ ለስዊዘርላንድ ከጎርጎረሳዉያኑ 1988 በኋላ ያሸነፈ ሁለተኛዉ ዜጋም ያደርገዋል።   በዓለም የሙዚቃ መድረክ ዝናን ያተረፈችዉ ሲሊንዲዮን በጎርጎረሳዉያኑ 1988 ዓ.ም በዚህ መድረክ የስዊዘርላንድን ሰንደቅ ዓላማን ይዛ ተወዳድራ ማሸነፏ አይዘነጋም። ሲሊንዲዮን በዚህ መድረክ ካሸነፈች በኋላ እስከዛሬ ድረስ ሙዚቃዋ ከአዉሮጳ አልፋ በዓለም ህዝብ ዘንድ ቀዳሚ ከተባሉት አቀንቃኞች መካከል ዝናን ያተረፈች ሆናለች።

የሙዚቃ ዉድድር መድረኩ አሸናፊ የሆነዉ የስዊዘርላንዱ ከያኒ ኔሞ አሸናፊነቱን ካረጋገጠ በኋላ በሰጠዉ መግለጫ "ራሳቸው ለመሆን የሚደፍሩ፤ መሰማት እና እንዲረድዋቸዉ ለሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ" በኩራት ዋንጫውን እቀበላለሁ ሲል ተናግሯል። "የበለጠ ርህራሄ ፤ የሌላዉን ችግር እንደራስ መመልከት ያስፈልገናልም" ሲል ከያኒዉ አክሏል። በአዉሮጳዉ ግዙፍ የሙዚቃ ዉድድር ላይ ሁለተኛ ሆኖ ያሸነፈዉ እና ቤቢ ላዛኛ የሚል የከያኒ መጠርያ ያለዉ የክሮየሽያ  አቀንቃኝ ነው። ከዩክሬይን የመጡት እና ለሁለት በመድረክ ላይ የራፕ እና ፖፕ ሙዚቃን አጣምረዉ ያቀረቡት ዩክሬናዉያን ሃገራቸዉን  በሦስተኛነ አስጠርተዋል።   

ይሮቪዥን የአዉሮጳዉ የሙዚቃ ውድድር አሸናፊነት የሚወሰነው ዉድድሩን በቀጥታ የተከታተሉ በአውሮጳና በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የቴሌቪዥን ተመልካቾች በስልክ ድምፅ ከሰጡ እና በ37ቱ የዉድድሩ ተሳታፊ ሃገራት ዉስጥ የሚገኙ የሙዚቃ ባለሙያ ዳኞች ከሰጡት ድምፅ ጋር ተደምሮ ነዉ። በሙዚቃ ዉድድሩ ለፍፃሜ ዉድድሩ ከቀረቡት 25 ተወዳዳሪዎች መካከል፤ ጀርመን ኢሳክ የተባለዉ ወጣት  አቀንቃኝ  12ኛ ደረጃን አግኝቷል።    

ስዊድን ያስተናገደችዉ የ2024 ይሮቪዝን

በየዓመቱ ለየት ያለ ርዕሰ ዜና የሚሰማት የአዉሮጳ ግዙፍ የሙዚቃ ዉድድር መድረክ«ይሮቪዥን» ከአለፉት የ70 ዓመታት ግድም የዝግጅት ታሪኩ በዘንድሮዉ ለየት ያለ እና እስከዛሬ ያልታዩ ጉዳዮች የታዩበት ነበር። ለፍጻሜ ዉድድሩ በመድረኩ የሚቀርቡ ሃገራት ከያኒዎች የማጣርያ ዉድድሮችን ማካሄድ ከጀመሩበት ከባለፉት ሳምንት ጀምሮ ዉድድሩ በተካሄደበት ከተማ በአብዛኛው በጋዛ ከቀጠለዉ ጦርነት ጋር በተያያዘ ሰፊ ተቃውሞ ፤ ቁጣና የውጥረት ስሜት ታይቷል።

በዩሮቪዥን ዘፈን ውድድር ላይ የእስራኤል ተሳትፎን በመቃወም በርካታ ተቃውሞዎች ነበሩ።
በዩሮቪዥን ዘፈን ውድድር ላይ የእስራኤል ተሳትፎን በመቃወም በርካታ ተቃውሞዎች ነበሩ።ምስል Martin Meissner/AP/picture alliance

ዉድድሩን የሚያዘጋጀዉ የአውሮጳ ብሮድካስቲንግ ህብረት (EBU) መድረኩ ለፖለቲካ ቦታ የሌለው ባህላዊ ክስተት ብቻ የሚታዩበት እና በደንቦቹ መሰረት ፖለቲካዊ መግለጫዎች ወይም መፈክሮች በዉድድሩ መድረክ እንደማይፈቀዱ በግልጽ በተደጋጋሚ ማስታወቁ ይታወቃል። የዉድድር መድረኩ ባለፈዉ ቅዳሜ ምሽት ለመካሄድ ዝግጅቱ ተጠናቆ ሳለ እለቱን ይኸዉ ዝግጅት በሚካሄድበት በስዊድንዋ ማልሞ ከተማ ዉስጥ በሽዎች የሚቆጠሩ የፍልስጤም ደጋፊ እና ፀረ-እስራኤል ተቃዋሚዎች፣ ከእስራኤል የመጣችዉ ወጣት ዘፋኝ ኤደን ጎላን  በመድረኩ ለዉድድር ለመቅረብ ዝግጁ በመሆንዋ በከፍተኛ ተቃዉሞ አካሂደዋል። በሳምንቱ መጀመርያ እንዲሁ እስራኤልን የወከለችዉ ዘፋኝ ለማጣርያ ዉድድር ቀርባ ለፍጻሜ ማለፍዋን ተከትሎ ቡ የሚል የተቃዉሞ ድምፅ በመድረኩ ተላልፎባታል፤ ተመሳሳይ ተቃዉሞዉ በከተማዋ ዉስጥ ተካሂዶ ነበር። 

ኤደን ጎላን የእስራኤልዋ የይሮቪዥን 2024 ተሳታፊ
ኤደን ጎላን የእስራኤልዋ የይሮቪዥን 2024 ተሳታፊ ምስል Martin Meissner/AP Photo/picture alliance

ዝግጅቱን በጋራ የሚደግፉ የአገራት ስብስብ ያለበት የአውሮጳ ብሮድካስቲንግ ህብረት (EBU) በበኩሉ "የብሮድካስቲንግ ሕብረቱ በዚህ ዓመት ዉድድር ላይ በመካከለኛው ምስራቅ ውስጥ የሚካሄደዉ አሰቃቂ ጦርነትን ተከትሎ የተፈጠረዉን ስሜት እና አስተያየት ይረዳልል" ሲል መግለጫ አውጥቷል። በመድረኩ የእስራኤልዋ ተወካይ ተወዳዳሪ ኤደን ጎላን በልዩ ጥበቃ ሥር ሆና ዉድድሩ እንደሚያከናውን ህብረቱ ገልጾም ነበር።  የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ የከያኒዋን በመድረክ አቀራረብ  ካዩ በኋላ እንደተናገሩት፤  ኤደን ጎላን "ከአስከፊ ፀረ-ሴማዊነት ማዕበል ጋር ብትታገልም ፤ " ባቀረበችዉ ሙዚቃ የድል እድሏ ከፍ ብሏል ሲሉ ተናግረዋል። 

የኖርዌይ ተወካይ እራሱን አግልሏል፤ አየርላንድ ትርኢት አላሳየም፣ የፊንላንዳውያን ተቃዉሞ በቀጥታ ስርጭት ስቱድዮ 

የሙዚቃ ዉድድር መድረኩ አዘጋጆች መድረኩ ፖለቲካዊ እንዳልሆነ ቢያውጁም ብሎም ፤ መድርኩ ዘንድሮ "በሙዚቃ መተሳሰር/መጣመር" የሚል መርህ ቢይዝም ፤ በጋዛ የሚታየዉ  ጦርነት ጥላዉን አጥሎበት ነዉ ያለፈዉ።

ዘንድሮ ከኖርዌይ የሚገኝ ነጥብን ለመናገር ተመርጣ የነበረችዉ እና ባለፈው ዓመት በይሮቪዥን የሙዚቃ ዉድድር ላይ አምስተኛ ደረጃን አግኝታ የነበረችዉ የኖርዌ ከያኒ አሌሳንድራ ሜሌ በኢንስተግራም ላይ ባስተላለፈችዉ መልክት መድረኩ "ባዶ ቃላት" ከመሆን ያለፈ ፋይዳ ስለሌለዉ ከኖርዌ ነጥብን ለመናገር አልፈልግም። እስራኤል "የዘር ማጥፋት ወንጀል" ፈፅማለች ፤  "ነፃ ለፍልስጤም" ስትል  ሃሳብዋን አጋርታለች። 

የአየርላንዷ ባምቢ ቱግ የፍልስጤም ደጋፊ ስሜቶችን ለመጠቆም ያሳየችዉ ርምጃ
የአየርላንዷ ባምቢ ቱግ የፍልስጤም ደጋፊ ስሜቶችን ለመጠቆም ያሳየችዉ ርምጃምስል Jessica Gow/TT/picture alliance

አየርላንዳዊዋ ከያኒ ባምቢ ቱግም በዝግጅቱ ለመቅረብ ከተካሄዱት የመጨረሻ ላይ ራሳቸዉን ካገለሉ በርካታ ተወዳዳሪዎች መካከል አንዷ ነች። በውል ባልገለፀችዉ ሁኔታ " የአውሮጳ ብሮድካስቲንግ ህብረት አስቸኳይ ትኩረት እንደሚያስፈልገኝ ተሰምቶኛል" ስትል መናገርዋ ተዘግቧል።  ዉድድሩ በተካሄደበት ሳምንት መጀመርያ ከከያኒዋና ልብስ ላይ ባለስልጣናት "ጦርነቱ ይቁም" "ለፍልስጤም ነጻነት" የሚሉ ጽሁፎችን ነቅለዉ ወስደዋል፤ ተብሏል። አየርላንዳዊዋ ከያኒ ባምቢ ቱግ እስራኤል በውድድሩ ውስጥ መካተትዋን ነቅፋም ነበር። ከስዊዘርላንድና ከግሪክ የመጡ ከያንያን ዉድድሩ ከመካሄዱ በፊት በነበሩት ቀናት ዉስጥ በተካሄደዉ የፍልስጤም ባንዲራ ሰልፍ ላይ አየርላንዳዊትዋን ከያኒ ተቀላቀለዉም ነበር።  

እስራኤል በዉድድሩ መካተትዋን ተከትሎ በፊንላንድ 40 ያህል ተቃዋሚዎች ከስዊድን የሚሰራጨዉን የሙዚቃ መድረክ የሚያሰራጭ ጣብያ ጋር  ሄደዉ እስራኤል ከዉድድሩ እራስዋን እንድታገል መጠየቃቸዉም ተዘግቧል። በዚህ የሙዚቃ ዉድድር ፈረንሳይ አራተኛ ደረጃን ይዛለች።

በአዉሮጳ ሙዚቃ ዉድድር ላይ እስራኤልn ወክላ የቀረበችዉን ወጣት ሊደግፉ የወጡ ሰልፈኞች
በአዉሮጳ ሙዚቃ ዉድድር ላይ እስራኤልn ወክላ የቀረበችዉን ወጣት ሊደግፉ የወጡ ሰልፈኞች ምስል Johan Nilsson/TT/AFP

 

ከውድድር የታገደዉ የሆላንዳዊ ከያኒ

በሌላ በኩል ብዙ አድናቂዎች ያሉት የኔዘርላንድ የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ጆስት ክላይን ቅዳሜ ምሽት ከነበረዉ ዉድድር መድረክ በአለቀ ሰዓት ታግዶዋል። ሆላንዳዊዉ ዘፋኝ የታገደበት ምክንያት ስርዓት ባለመክበር እና ጋጠወጥ ሥነ-ምግባር ከማሳየት ጋር የተያያዘ እንደነበር ተዘግቧል።  ቆየት ብለዉ በወጡ  መረጃዎች መሰረት ሆላንድን ሊወከል ዉድድር መድረኩ ጫፍ ላይ ደርሶ የነበረዉ ከያኒ በአንዲት የ,ድረኩ አስተባባሪ ሴት ከፍተኛ ክስ ተመስርቶበታል ተብሏል። 

ጋጠወጥ ስነ-ምግባር ፈጽሟል ተብሎ ከዝግጅቱ የታገደዉ ሆላንዳዊ
ጋጠወጥ ስነ-ምግባር ፈጽሟል ተብሎ ከዝግጅቱ የታገደዉ ሆላንዳዊ ምስል Andreas Brenner/DW

ዘንድሮ ለ68ኛ ጊዜ የተካሄደዉ የአዉሮጳ ሃገራት የሙዚቃ ዉድድር መድረክ ይሮቪዥን 2024፤ በአውሮጳ ብሮድካስቲንግ ህብረት ተቋቋሞ የዉድድር መድረኩን አንድ ብሎ የጀመረዉ ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት በተጠናቀቀ፤ አስራ ሁለተኛ ዓመት ላይ እንደ አዉሮጳዉያን አቆጣጠር 1956 ዓ.ም ነበር። ነገሩ የአዉሮጳዉያን የሙዚቃ ዉድድር መድረክ ይሮቪዥን ተብሎ ተሰየመ እንጂ፤ በአዉሮጳ ድንበር ክልል ዉስጥ የማይገኙ፤ የራድዮ ማህበሩ አባል ሀገሮች ሁሉ የሚሳተፉበት ነዉ። የማህበሩ አባላት ደግሞ እስራኤልን፤ የእስያ ሀገሮችን፤ አዉስትራልያን ብሎም የሰሜን አፍሪቃ ሀገራትን ሁሉ ያጠቃልላል። በዚህ ዉድድር ላይ ከአፍሪቃ ሃገራት ሞሮኮ እንደ ጎርጎረሳዊዉ አቆጣጠር በ1980 ዓ.ም በዚህ መድረክ ተሳትፋለች። በአውሮጳ ብሮድካስቲንግ ህብረት አባል  ከሆኑ ሃገራት መካከል  በሙዚቃ ዉድድሩ እስከ ዛሪ ያልተሳተፉ ከአፍሪቃ እና መካከለኛ ምስራቅ ሃገራት የማህበሩ አባላት መካከል ፤ አልጀርያ፤ ቱኒዚያ፤ ሊቢያ፤ ግብጽ፤ ዮርዳኖስ እና ሊባኖስ ይገኙበታል። ዋና መቀመጫዉን ጄኔቭ ስዊዘርላንድ ያደረገዉ የአዉሮጳ የብሮድካስቲንግ  ማኅበር ሦስት የታገዱ አባል ሃገራትም አሉት።  እነሱም ሩስያ፤ ቤላሩስያ እና ሊቢያ ናቸዉ። 

ስዊድን ያለፈዉን ዓመት ዉድድር በማሸነፍዋ የዘንድሮዉን ዉድድር በማልሞ ከተማ ላይ አዘጋጅታለች። የመጭዉን 2025 ዓመት የአዉሮጳ ሃገራት የሙዚቃ ዉድድርን የዘንድሮ አሸናፊ አገር ስዊዘርላንድ ተረክባ ዝግጅቷን ከወዲሁ ጀምራለች። 

አዜብ ታደሰ

ታምራት ዲንሳ